ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራነቸስኮስ “በቤተ ክርስቲያን ችግሮች ቢኖርም ከጨለማ ይልቅ የተስፋ ብርሃን ይበረታል”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እ.አ.አ በአመቱ ማብቂያ ላይ የዓለማቀፋዊቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና በቫቲካን የእርሳቸው የቅርብ የሥራ ተባባሪ ለሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቀሳውስት የቤተ ክርስቲያኗን አመታዊ ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ የሥራ ክንውኖችን በመገምገም እና እነዚህን ክንውኖች ከግምት ባስገባ መልኩ ንግግር እንደ ምያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 12/2011 ዓ.ም ለእነዚህ የዓለማቀፋዊቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና በቫቲካን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪ ለሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቀሳውስት በቫቲካን ባደረጉት ንግግር ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት አሁንም ቢሆን በዓለም ደረጃ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ምግባር ችግሮች እየተነጸባረቁ እንደ ሚገኙ የገለጹት ቅዱስነታቸው ምንም እንኳን ከፍተኛ የሆኑ ችግሮች ቢታዩም ካሉት ጨለማ የሆኑ ነገሮች ይልቅ የሚታየው የተስፋ ብርሃን በከፍተኛ ሁኔታ የሚልቅ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዓለማቀፋዊቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና በቫቲካን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪ ለሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቀሳውስት የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማኅበርሰብ ክፍሎች ዘንድ በቅርቡ የሚከበረውን የገናን በዓል አስመልክተው የቤተ ክርስቲያኗን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመገምገም ባደርጉት ንግግር፣ የገናን በዓል መከበር አጋጣሚውን በመጠቀም በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ውስጥ እየተከሰቱ የሚገኙትን ደስታዎች፣ እንዲሁም ስቃይ እና ተግዳሮቶችን ለመመርመር ይህ የገና በዓል የሚሰጠንን እድል ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያን በለውጥ ጎዳና ላይ ናት
“የገና በዓል በደስታ እንድንሞላ የሚያደርገን እና ምንም ዓይነት ኅጢያት ከእግዚአብሔር ምሕረት በላይ እንዳልሆነ የምያረጋግጥልን በዓል” እንደ ሆነ በንግግራቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በምዕራፍ 13፡12 ላይ የተጠቀሰውን “ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ” ብሎ እንደ ጻፈ አስታውሰው በዚህ የገና በዓል የጨለማ ሥራዎች የሆኑትን ሁሉ አውልቀን በመጣል የብርሃን ልጆች የሚያደርገንን መልካም ሥራዎች መፈጸም ይኖርብናል ብለዋል።
ክርስቲያን መሆን ማለት "እግዚአብሔር በኪሳቸው ውስጥ አለ ብለው የሚያስቡ ምርጥ የማኅበርሰብ ቡድን አባል መሆን ማለት እንዳልሆነ” መገንዘብ እንደ ሚገባ በአጽኖት የገለጹት ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያኗ ሁልጊዜ የንስሐ እና የእድሳት ጉዞን እየተከተለች የምትሄድ እና "ቅድስት የሆነች እና ሁል ጊዜ የመንፃት አስፈላጊነትን በመገንዘብ" ወደ ፊት የምትጓዝ መሆኑዋን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።
መከራዎች
በቤተክርስቲያኗን የገጠማትን መከራዎች በተመለከተ የተናገሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ "በዚህ በመገባደድ ላይ ባለው 2018 ዓ.ም ኃይለኛ የሆነ አውሎ ነፋስ እና ተግዳሮት ቤተ ክርስቲያኗን እንዳጋጠማት” ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። አንዳንድ ሰዎች ይህንን በተመለከተ በቀረቡ የዜና ዘገባዎች ምክንያት ተስፋ ቆርጠው ቤተክርስቲያኑን ትተው ሂደዋል፣ ሌሎች ደግሞ ከፍርሃት ወይም ከግል ፍላጎታቸው የተነሳ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፣ ሌሎች ደግሞ "ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብታ ስትንገላታ ለማየት በጉጉት በመጠባበቅ ላይ እንደ ሆኑ” አንዳንዶቹ ደግሞ እምነታቸውን ጠብቀው ታማኝ ሆነው መቆየትን መምረጣቸውን ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገልጸዋል።
በቅድሚያ ስደተኞች የምያጋጥማቸው መከራ እና ስቃይ፣ ድህነት፣ ግጭቶች፣ ስደተኞች በሚፈልሱባቸው ሀገራት ውስጥ የሚፈጸሙ በጭካኔ የተሞሉ ተግባሮች እንዲሁም ስደተኞችን ተቀብለው በምያስተናግዱ ሀገራት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚታየው ፍርሃትና ጭፍን ጥላቻን ጨምሮ ስደተኞች የሚገጥማቸው ህገ ወጥ የሆኑ ተግባራት በቀዳሚነት እንደ ሚጠቀሱ በንግግራቸው ወቅት ያወሱት ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ሌሎች ብዙ ክርስቲያኖችም ስደት እንደ ሚደርስባቸው ሆኖም "ክርስቶስን ከመካድ ይልቅ ሞትን በድፍረት መቀበል እንደ መረጡ” ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።
ታማኝ ያለመሆን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን በቀጠሉበት ወቅት እንደ ገለጹት “ለጥሪያቸው ታማኝ ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች መልካም መስለው እና ገንቢ የሆነ አመለካከት ያላቸው ሰዎች መስለው በመቅረብ በጀርባ ግን የወንድሞቻቸውን እና የእህቶቻቸውን ስም በማጠልሸት እና አረም በመዝራት፣ መከፋፈልን እና አለመተማመንን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲፈጠር በማድረግ ሂደት የተጠመዱ፣ ለጥሪያቸው ታማኝ ያልሆኑ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንደ ሚገኙ ያወሱት ቅዱስነታቸው ይህ ተግባራቸው ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ የሰጠውን አስቆርታዊው ይሁዳ ባሕሪ ጋር እንደ ሚመሳሰል ገልጸው አእምሮአዊ ክህሎታቸውን ተጠቅመው በጥፋት መንገዳቸው ላይ መጓዛቸውን እንዳላቋረጡ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸው ሁላችንም ቢሆን የዚህን ዓይነቱን መንፈሳዊ ዝቅጠት የመዋጋት ግዴታ አለብን ብለዋል።
ጾታዊ ጥቃት
በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሚፈጸሙ ማነኛውም ጾታዊ ጥቃቶች በፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው እና አረመኔያዊ ተግባሮች በመሆናቸው የተነሳ በግልጽ መወገዝ የሚገባቸው ተግባሮች እንደ ሆኑ በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው የዚህን ዓይነት ተግባር እየፈጸሙ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ተመጣጣኝ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው በአጽኖት ገልጸዋል። በተጨማሪም ማነኛውንም ዓይነት የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚደብቅ አካል የእዚህ አረመኔያዊ የሆነ ጥቃት ተባባሪ እንደ ሆነ በግልጽ የሚያሳይ በመሆኑ የተነሳ ጥብቅ የሆነ ሕጋዊ ቅጣት እንደ ሚጠብቀው የገለጹት ቅዱስነታቸው በማነኛው ሁኔታ እና መስፈርት ጾታዊ ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብለዋል።
ደስታዎች
አሁን በመገባደድ ላይ ባለው የአውሮፓዊያኑ 2018 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያን በጣም ብዙ አስደሳች የሚባሉ ተግባራትን መፈጸሟን በንግግራቸው ያወሱት ቅዱስነታቸው ለምሳሌም በቅርቡ በወጣቶች ጉዳይ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የተካሄደውን ሲኖዶስ ውጤታማ በመሆኑ የተነሳ ይህ ውጤት እንዲመዘገብ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉትን አካላት በሙሉ ቅዱስነታቸው ማመስገናቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። በተጨማሪም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና በቫቲካን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪ የሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቀሳውስት የቫቲካንን በተለይም ደግሞ የፋይናንስ አስተዳደር ግልጽ እና የተጠያቂነት መንፈስ በተላበሰው መልክ እንዲካሄድ የተጀመረውን ታድሶ ወይም የለውጥ ጎዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ላደርጉት ከፍተኛ አስተዋጾ ቅዱስነታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ማመስገናቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።
በቅርቡ በአልጄሪያ የብጽዕና ማዕረግ የተሰጣቸው 19 ሰማዕታት ታሪክ የክርስትናን እምነት የምያበረታታ ገድል እንደ ሆነ፣ በምስጢረ ጥምቀት አማካይነት በእየዕለቱ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የሚቀላቀሉ አዳዲስ መዕመናን እየተበራከቱ መሄዳቸው፣ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ ራሳቸውን ለክህነት እንዲሁም ለመንፈሳዊ ሕይወት አገልግሎት ሕይወታቸውን እየሰጡ የሚገኙ ወንድ እና ሴት ወጣቶች በቁጥር እየተበራከቱ መሂዳቸው ከፍተኛ ተስፋ የሚሰጥ ክስተት በመሆኑ ደስታን እንደ ፈጠረባቸው ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ገልጸዋል።
በመቀጠል ቅዱስነታቸው እንደ ገለጹት በየቀኑ የጋብቻ ጥሪቸውን በታማኝነት፣ መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በዝምታ፣ በቅድስና እና እራስን በመካድ እየኖሩ የሚገኙ ምዕመናንን” አድንቀው በተለይም ደግሞ መልካም የሆኑ ሐዋርያዊ ተግባራትን በማከናውን ላይ የሚገኙ፣ ነገር ግን የሚዲያ ሽፋን ያላገኙ በርካታ ቆመሳት መኖራቸውን አውስተው እኛ ተግባራችንን የምናከናውነው በስውር ለምያየን እግዚኣብሔር በመሆኑ የተነሳ ለዚህ ጉዳይ መጨነቅ አይኖርብንም ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዓለማቀፋዊቷ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር የበላይ የመስተዳድር አካላት እና በቫቲካን የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ የሥራ ተባባሪ ለሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቀሳውስት የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማኅበርሰብ ክፍሎች ዘንድ በቅርቡ የሚከበረውን የገናን በዓል አስመልክተው የቤተ ክርስቲያኗን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመገምገም ባደርጉት ንግግር ማጠቃለያ ላይ እንደ ግለጹት “ክፉ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ የሚያሸንፍ የመልካም ብርሃን” ሁሉ ምንጭ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል ልባችንን መክፈት የይገባል ካሉ በኋላ የገና በዓል "ምንም እንኳን ሰብአዊ የሆኑ ሥቃዮች ቢኖርም የእግዚአብሔር ብርሀን ብሩህ ሆኖ እንደሚቀጥል" እና "ቤተክርስቲያኗ ከነዚህ አሁን ካለችበት ሁሉ ይበልጥ ቆንጆ፣ የጸዳች እና የምታበራ” ሆና እንድትቀጥል ያደርጋታል ብለው መልካም የገና በዓል ለሁሉም እንዲሆን ከተመኙ በኋላ ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
 

22 December 2018, 18:06