ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ዩኒቨርሲቲዎች የጦርነት መንስኤዎችን በማጥናት መፍትሄ መስጠት ይኖርባቸዋል

ዓለማችን ከጦርነት ነጻ ሆና እንደ ማታውቅ ከታሪክ መዛግብት ለመረዳት ይቻላል። ባለፈው ሕዳር 02/2011 ዓ.ም 15 ሚልዮን የሚሆኑ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው የመጀመርያው የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበት 100ኛ ዓመት ተዘክሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ይህ መቶኛ ዓመት በተዘከረበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ሁኔታውን አስመልክተው እንደ ገለጹት “የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ታሪካዊ ገጽታ ሁሉም የሰው ልጆች የጦርነትን ባህል እንዲያስወግዱ  እና በአሁኑ ወቅት በብዙ የዓለማችን ክፍሎች እየተከሰቱ የሚገኙ ግጭቶችን ለማስቆም ህጋዊ የሆኑ መፍትሄዎችን እንዲፈጉ የሚያስጠነቅቅ  እና የሚያስታውስ ክስተት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው “እኛ ግን ከእዚያ አስቃቂ ክስተት የተማርነው ነገር ያለ አይመስለኝም” ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህንን የተናገሩበት ምክንያት አሁንም ቢሆን ከመቶ አመታት በኋላ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ውስጥ የተለያዩ አሰቃቂ የሚባሉ ጦርነቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን በዋቢነት በመጥቀስ ሲሆን በተለይም ደግሞ ንጹዕ ውሃ እና በቂ የተመጣጠነ ምግብ የማያገኙ፣ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል የሚረዳ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማካሄድ የሚረዳ በቂ የኢኮኖሚ አቅም “የለንም”  የሚሉ ሀገራት አስገራሚ በሆነ መልኩ በተቃራኒው የጦር መሳሪያዎችን እና ጥይቶቻቸውን ለመግዛት ገንዘብ አጥተው አለማወቃቸው እንደ ምያስገርማቸው ቅዱስነታቸው በአጽኖት መግለጻቸውን ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ጦርነትን እና ግጭቶችን ከዓለማችን ለመቀነስ ከተቻለም ለማስወገድ ይረዳ ዘንድ ችግሮችን እና ግጭቶችን የሚፈጥሩ ነገሮችን አስቀድሞ ለይቶ በማወቅ ግጭቶች ሳይፈጠሩ በፊት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይችላ ዘንድ የሚረዳ የትምሕርት ዘርፍ እንዲቋቋም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሕዳር 03/2011 ዓ.ም በሮም ከተማ የሚገኘውን ላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲን መጠየቃቸው ተገልጹዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህ በሕዳር 03/2011 ዓ.ም ለላቴራን ዩኒቬርስቲ ያቀርቡት ጥሪ ዩኒቬርስቲው የጦርነት መንስሄ የሆኑ ግጭቶችን አስቀድሞ በመለየት ግጭቶ እና ጦርነቶች ሳይከሰቱ በፊት ለይቶ በማወቅ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚያስችል ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለዚህ ዝግጅት የሚረዳ ትምሕርት መስጠት እንደ ሚገባ፣ “የሰላም ሳይንስ” በመባል የሚጠራ የትምህርት ዘርፍ እንዲኖር ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጹዋል። በዚህ “የሰላም ሳይንስ” በተሰኘው የትምህርት ዘርፍ የሰላም ፍሬ ማፍራት የሚችሉ፣ በማሕበረሰቡ ውስጥ እርቅ መፍጠር የሚያስችሉ የሕነጻ የትምህርት ዘርፎችን በማቋቋም ካህናት፣ ደናግላንን እና እንዲሁም ምዕመኑን ባካተተ መልኩ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ግጭቶችን እንዴ ማስወገድ እንደ ሚችላ የሚረዳ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ሰላምን እንዴት ማስፈን እንደ ሚቻል ማወቅ የሚያስችሉ ሁለገብ የሕነጻ ትምህርቶችን መስጠት እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው አሳስበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በሕዳር 03/2011 ዓ.ም ለላቴራን ጳጳሳዊ ዮኒቨርሲቲ ዋና ዳይሬክተር በጻፉት መልእክት እንደ ገለጹት “በአሁኑ ወቅት እና ለሚመጣው ጊዜ ሳይቀር” ሰላምን ማስፈን የሚችሉ በቂ የሆነ ሳይንሳዊ እውቀት ያላቸው ሰዎችን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደ ሚገባ መግለጻቸው ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት ጥላችን ያስወግዳል

“ግጭቶች እና ጥላቻዎች በተስፋፉበት በአሁኑ ዘመን” ከምንጊዜ በላይ ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን መፈለግ እንደ ሚገባ በመልእክታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ወንጌል ብርሃን በመታገዝ በታሪክ ውስጥ በተከሰቱ እና እየተከሰቱ በሚገኙ ጦርነቶች ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙትን ሰዎች ለመርዳት እና ለማገዝ ከፍተኛ ጥረት ከማድረጓም ባሻገር የጦርነት ምክንያት የሆኑ ነገሮች በሙሉ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት በውይይት ይወገዱ ዘንድ የበኩሉዋን አስተዋጾ ስታደርግ እንደ ቆየች ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው አስታውሰዋል። "ጥላቻን ለማጥፋት፣ ራስ ወዳድነት ስሜት ለማሸነፍ፣ ስልጣንን ከመመኘት፣ በአቅመ ደካሞች ራስ ላይ ለመረማመድ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ስሜቶችን ለማስወገድ እውነተኛ የሆነ ውይይት ማድረግ የሰላም መንገድ እንደ ሚከፍት” ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው አጽኖት ሰጥተው ገልጸዋል።

ለዓመጽ እና ለጥፋት ተነሳሽ የሚሆኑ ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑት፣ ግጭቶችን የሚያነሳሱ የመገለል ስሜቶችን ማስወገድ የሚችል ስነ-አመክንዮን በጠበቀ መልኩ የሚሰጡ ትምህርቶችን፣ የግጭቶች እና የጦርነት ባህሪይ አመላካችን የሆኑ እውቅት እና በቂ ዝግጅት ማስጨበጥ የሚችሉ እነዚህን እና ከእነዚህ ጋር ተያያዥ የሆኑ  የትምሕርት ዘርፎችን በመስጠት በአጠቃላይ ለማዳመጥ እና ለመረዳት የሚያስችል የትምህርት ዘርፎችን መስጠት እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገለጸዋል።

በዲፕሎማሲ አማካይነት ግጭቶችን ማስወገድ ይቻላል

በዓለማቀፍ ማኅበርሰብ ፊት ቤተ ክርስቲያን “ተኣማኒነት ያለው እርቅ ለማውረድ” ያስችላት ዘንድ ቤተ ክርስቲያን “ሰላምን ለሚነሱ ችግሮች መፍትሄ ለማስገኘት፣ ስምምነት እንዲኖር ለማድረግ፣ ለአከባቢ ጥበቃ ማድረግ እንደ ሚገባ፣ ማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር በመሆኑ የተነሳ ከጽንስ ጀመሮ ያሉ የሰው ልጅ ነፍስ ጠበቃ እንዲደረግለት፣ የሰው ልጅ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ መብቱ እንዲጠበቅ” ቤተ ክርስቲያን ድምጿን ማሰማት መቀጠል እንደ ሚገባት ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው በአጽኖት ገለጸዋል።

ይህንን ገቢራዊ ለማድረግ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት መንበር አማካይነት በሚደርጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የበኩሉዋን ጥረት እያደርገች እንደ ምትገኝ የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህም ተግባሯ ቤተ ክርስቲያን ከዓለማቀፉ ማኅበርሰብ ጋር በመወያየት የጥላቻ እና የግጭቶች መንስሄ የሆኑ ጉዳዮች በእንጭጩ ይቀረፉ ዘንድ፣ የሰው ልጅ ስብዓዊ እና መስረታዊ መብቶች ይከበሩ ዘንድ፣ ሁለንተናዊ የሆነ የሕዝብ እና የሀገር ልማት በተቀናጀ መልኩ ማካሄድ እንደ ሚገባ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማሳሰብ ላይ እንደ ምትገኝ ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 November 2018, 14:50