ፈልግ

1ኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ሕዳር 08/2010 ዓ.ም በቫቲካን በተከበረበት ወቅት 1ኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ሕዳር 08/2010 ዓ.ም በቫቲካን በተከበረበት ወቅት  

“ይህ ደሃ ሰው ጮኸ እግዚኣብሔርም ሰማው”

ሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ሕዳር 09/2011 ዓ.ም

“ይህ ደሃ ሰው ጮኸ እግዚኣብሔርም ሰማው”

 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እሁድ ሕዳር 09/2011 ዓ.ም ለሚከበረው ሁለተኛ ዓለማቀፍ የድኾች ቀን ዝግጅት ይሆን ዘንድ ባለፈው ዓመት ሰኔ 06/2010 ዓ.ም ለአስተንትኖ የሚሆን መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል። እንደ ሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ የድኾች ቀን እንዲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ የወሰኑት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ እንደ ሆኑ የሚታወስ ሲሆን የመጀመሪያው ዓለማቀፍ የድኾች ቀን በሕዳር 08/2010 ዓ.ም “በቃላት ሳይሆን በተግባር እንውደድ” በሚል መሪ ቃል ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ መሪ ቃል የተወሰደው “ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ” (1ዮሐ. 3፡18)  ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደ ተወስደ በወቅቱ መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን ይህ 1ኛው ዓለማቀፍ የድኾች ቀን ቫቲካንን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

1ኛው ዓለማቀፍ የድኾች ቀን በሕዳር 08/2010 ዓ.ም  በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በተካሄደ መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “አባታችን ሆይ!” የሚለው ጸሎት የድኾች ጸሎት እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ገልጸው እኛ ሁላችን አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት “አባታችን ሆይ” በማለት ሁላችንም የአንዱ የእግዚኣብሔር ልጆች መሆናችንን  በመግለጽ አባት ለልጁ እንደ ሚያደርገው ሁሉ “‘የዕለት እንጀራችንን ስጠን’ ብለን እንደ ምንጠይቀው እና እርሱም እንደ ሚሰጠን ሁሉ እኛም በየጎረቤቶቻችን እና በእየአከባቢዎቻችን የሚገኙ  ርዳታ ፈላጊ ድኾች  የእኛን እገዛ ፈልገው በሚማጸኑን ወቅት ሁሉ ካለን ማካፈል ይገባናል፣ በቃላት ብቻ ሳይሆን እምነታችንን በተግባር መግለጽ ይኖርብናል” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱ በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊክ ከተካሄደው መስዋዕተ ቅዳሴ በመቀጠል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለበርካታ ድሆች እና የእኔ ቢጤዎች የምሳ ግብዣ ተደርጎላቸው እንደ ነበር የሚታወስ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ በሮም ከተማ እና በአከባቢው የሚገኙ የምግብ ቤቶች ሳይቀር በገዛ ፈቃዳቸው ለድሆች የነጻ የምሳ ግብዣ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  በሕዳር 09/2011 ዓ.ም ለሚከበረው ሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ይሆን ዘንድ የመረጡት መሪ ቃል “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤  እግዚአብሔርም   ሰማው (መዝሙር 34፡7) የተሰኘው ሐረግ እንደ ሆነ ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን የእዚህን መልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል፣ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

“ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም  ሰማው” (መዝሙር 34፡7)

1.     “ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም  ሰማው” (መዝሙር 34፡7)፣ እነዚህ የመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ጸሐፊ  ቃላት የእኛ ቃላት ሊሆኑ የሚችሉት እኛ ራሳችን በተለምዶ ስማቸው “ድሆች" ተብለው የተፈረጁ ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ያጋጠሟቸውን የተለያዩ መከራዎች እና መገለሎች መቋቋም  እንዲችሉ ስናደርግ ብቻ ነው።  የመዝሙረ ዳዊት ጸሐፊ የሚናገረው ስለመከራ ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን የሚናገረው በተቃራኒው ነው። ዘማሪው ዳዊት ቀጥተኛ የሆነ የድህነት ተመክሮ የነበረው ሰው ሲሆን ይህንን የድህነት ተመክሮ እግዚኣብሔርን ማመሰገኛ ወደ ሆነ መዝሙር ይቀይረዋል። ይህ መዝሙር ዛሬ ብዙ ዓይነት ድህነት ተጠናውቶን ለምንገኝ ለእኛ እውነተኛ ድሃ ማን እንደሆነ ለመረዳት እና የእነሱን ጩኸት ለመስማት እና የእነሱን ፍላጎት ለማወቅ እንደ ተጠራን እንድንገነዘብ እድሉን ይሰጠናል።

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ወደ እሱ የሚጮኹ ድሆችን ድምጽ ይሰማልና ይህም እርሱን የሚጠባበቁ ድሆች፣ በሐዘን እና በብቸኝነት መንፈስ የተነሳ ልባቸው የተሰበረ ሰዎች፣ እንዲሁም በመገለል ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች መልካም ነገር ነው። ሰብዓዊ ክብራቸው በግፍ የተገፈፈ፣ ነገር ግን ብርሃን ለማየት እና መፅናናትን ለማግኘት ጥንካሬ ያላቸው ሰዎች ጩኽት ጌታ ይሰማል። በሐሰት ተፈርዶባቸው የሚሰቃዩ ሰዎችን እና ያልተገባ መጠሪያ ተሰጥቱዋቸው በጨቋኝ መዋቅሮች እና በህውከት ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ሰዎችን ድምጽ ያዳምጣል። ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሰዎች ደህንነታቸው በእግዚአብሔር ዘንድ እንዳለ ያውቃሉ። ከሁሉም በላይ ደገሞ ከዚህ ጸሎት የሚወጣው መንፈስ የምያቅፈን፣ የምሰማን፣ የምንከባከበን እና የምቀበለን አባት እንዳለን እንድንገነዘብ ያደርገናል። እነዚህን ቃላት ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የበለጠ ለመረዳት ያስችለን ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ላይ በሰበከው ስብከት ውስጥ የምገኙትን “በመንፈስ  ድሆች የሆኑ ሰዎች ሁሉ የተባረኩ ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” (ማቴ 5፡3) ጋር ማመሳከር ይቻላል።

እንደዚህ ዓይነት ልዩ አጋጣሚዎች በተለያዩ መንገዶች ለመግለጽ የሚያዳግቱ እና የማይቻሉ ነገሮች ሲሆኑ ነገር ግን እኛ ለሌሎች በተለይም እንደ ዘማሪው ዳዊት ለድሆች፣ ለተጠሉ እና ለተገለሉ ሰዎች ሁሉ እኛ ይህንን ለመመስከር መሻታችንን መግለጽ ይኖርብናል። በተለይም ብዙ ጊዜ ሀብትን እንደ ዋነኛ ዓላማ ወይም ግብ አድርጎ በምቆጥረው ዓለማችን የተነሳ ሰዎች ይገለሉ ይሆናል እንጂ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ማንም ሰው ከአብ ፍቅር የተገለለ ሊሆን አይችልም።

2.     ዘማሪው ዳዊት በምዕራፍ 34 ላይ የድሆችን አቋም እና ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማመላከት በማሰብ ሦስት ግሦችን ይጠቀማል። በቅድሚያ “መጮኸ” የሚለውን እናገኛለን። የድህነት ሁኔታ በአንድ ቃል ሊገለጽ አይቻልም፣ ግን ሰማያትን አቋርጦ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል። የአንድ ድሃ ጩኸት ስቃዩን እና ብቸኝነቱን፣ እንዲሁም ጥርጣሬውን እና ተስፋውን የማያስተገባ ከሆነ ታዲያ የተለየ ሌላ ነገር እንዴት ያስተጋባ? ይህ  ወደ እግዚኣብሔር የተደረገ እና በእግዚኣብሔር ፊት የቀረበ ጩኸት የእኛን በእዚህ ምድር ያለነው ሰዎች ልብ  ዘልቆ እንዳይገባ የከለከለው፣ ግድዬለሽ እንድንሆን እና ምንም ነገር እንዳልተከሰተ አድርገን እንድንቆጥር ያደርገው ነገር ምንድን ነው? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። በእንዲህ ዓይነቱ ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በሚከበርበት ወቅት  በእርግጥ የእንዲህ ዓይነቱን ድምጽ መስማት እንደምንችል ወይም እንደማንችል መረዳት እንድንችል አእምሮዎቻችንን በጥልቀት እንድንመረምር ተጠርተናል።

የእነርሱን ድምጽ ለይተን ለማወቅ የምንችለው በጸጥታ ውስጥ ያንን ድምጽ በመፈለግ ብቻ ነው። እኛ ራሳችን ብዙ የምንናገር ከሆንን ግን ያንን ድምጽ ለይተን መስማት አንችልም። ብዙን ጊዜ ያንን ጩኸት ለመስማት የምያስችሉ የተለያዩ አነሳሽ የሆኑ ሐስቦች እንደ ሚቀርቡ የሚታወቅ ሲሆን እነርሱም ተገቢ እና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ቢሆኑም ቅሉ ነገር ግን ብዙን ጊዜ እንደ ምናየው ይህ ነገር የድሆችን ጩኸት ትክክለኛነት ከማረጋገጥ እና ከመቀበል ይልቅ ይህንን አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎችን ለማስደሰት የሚደርግ ተግባር ሆን እንዳይቀር እሰጋለሁ። ይህ ከሆነ እና ድሆች ለቅሶዋቸውን በምያሰሙበት ወቅት የእኛ ምላሽ ተመጣጣኝ ካልሆነ የእነርሱን ሁኔታ እና ችግር በአግባቡ ማስተግባት አንችልም ማለት ነው። በመስታወት ውስጥ አሻግሮ የመመልከት እና እኛ በራስ ወዳድነት መንፈስ ውስጥ እንደ ገባን በማሰብ ራሳችን የመውቀስ ባሕል ውስጥ ማስገባት በራሱ ጥቅም የሌለው እና በቂ የሆነ ነገር ባለመሆኑ የተነሳ ተጨባጭ የሆኑ ሁኔታዎችን በቀጥታ ለመጋፈጥ መነሳት ይኖርብናል።

3.     “መልስ መስጠት” የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ቃል ነው። ዘማሪዊ ዳዊት እንደ ሚለው እግዚኣብሔር የድሃውን ጩኽት ከማዳመጥ ባሻገር መልስ እንደ ሚሰጥ ይናገራል። በደህንነት ታሪክ ውስጥ እንደ ተረጋገጠው ለድሆች ፍቅራዊ በሆነ መልኩ ምላሽ ሰጥቱዋል። አብራሃም እና ሚስቱ ሣራ ዕድሜያቸው በገፋበት ወቅት ልጅ ለማግኘት የነበራቸውን ጉጉት ለእግዚኣብሔር በገለጹበት ወቅት እግዚኣብሔር ተገቢውን ምላሽ ሰጥቶዋቸው ነበር (ኦ.ዘፍጥረት 15:1-6)። ሙሴ የሚቃጠል በምመስል ቁጥቋጦ ውስጥ የእዚኣብሔር መልኮታዊ ስም በተገለጸበት እና የእርሱን ሕዝብ ከግብፅ ባርነት ለማውጣት ተልዕኮ በተቀበለበት ወቅት ይህ ነገር ተፈጽሙዋል (ዘ. ጸዕት 3፡1-15)። የእስራኤል ሕዝብ በምድረበዳ ውስጥ በነበሩበት ወቅት በረሃብ እና በጥማት በሚሰቃዩበት ወቅት (ዘ.ጸዕት 16፡1-6,17-1-7) እና ሕዝቡ ጣዖት ማምልክ በጀመረበት ፈታኛ ወቅት እንኳን ሳይቀር እግዚኣብሔር በበቂ ሁኔታ ለሕዝቡ ምላሽ ሰጥቱዋል (ዘ. ጸዕት 32፡1-14)።

እግዚኣብሔር በደህንነት ታሪክ ውስጥ በአካልዊ እና በመንፈሳዊ ቁስሎች የሚሰቃዩትን ድሆች ጩኸት ለመመለስ ጣልቃ መግባቱ የሚታወቅ ሲሆን ያጡትን ፍትህ መልሰው እንዲጎናጸፉ በማድረግ እና አዲስ በክብር የተሞላ ሕይወ እንዲጀምሩ እንደ ረዳቸውም ይታወቃል። እግዚአብሔር የሰጠው መልስ በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ ምንም እንኳን ሰብዓዊ የሆነ ውስንነት ቢኖርባቸውም እግዚኣብሔር የሰጠውን ዓይነት ምላሽ በዋቢነት በመጠቀም ድሆች ለምያቀርቡት ጩኸት የተቻላቸውን ያህል ምላሽ ሊሰጡ ይገባል። በዚህ ዓለማቀፍ የድኾች ቀን በተቻለ መጠን በመላው ዓለም ከምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ጋር በጋራ በመሆን በየተኛውም ስፍራ የሚገኙ ያልተሰሙ የድሆች ጩኸቶች ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል። ምንአልባትም ይህ የምናደርገው ጥረት  በድህነት ምድረ በዳ ውስጥ አንድ ጠብታ ውሃ እንደ ማንጠባጠብ መስሎ ይታይ ይሆናል፣ ይሁን እንጂ ይህ ጥረት  ርዳታ ለምያስፈልጋቸው ሰዎች ካለን በማካፈል በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ሕይወት ውስጥ በንቃት ተሳትፎ የምናደርግበት፣ ካለን የምናካፍልበት ምልክት ሆኖ ሊታይ ይችላል። ድሆች የሚያስፈልጋቸው አንድ ሥልጣን ያለው ኃይል እንዲያግዛቸው ሳይሆን፣ ነገር ግን ጮኸታቸውን የሚሰሙ የብዙ ሰዎች ግላዊ ተሳትፎ ይሻሉ። በእዚህ ረገድ አማኞች ለድሆች የምያደርጉት ድጋፍ፣ እንዲሁ ጊዜያዊ የሆነ ድጋፍ ማድርግ ቢቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ግላዊ ተሳትፎ በታከለበት መልኩ በፍቅር ኃይል በተሞላ መልኩ ልያከናውኑ ይግባቸዋል፣ ይህም ድሆች እንዲከበሩ ያደርጋቸዋል።

4.     ሦስተኛው ቃል “ነጻ ማውጣት” የሚለው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ድሆች እግዚአብሔር ክብራቸውን እንደሚመልስላቸው እና እንደ ሚቀበላቸው እርግጠኞች ነበሩ። ድህነት በራሱ ጊዜ የሚመጣ ነገር ብቻ ሳይሆን በራስ ወዳድነት፣ በኩራት፣ በስግብግብነት እና በፍትህ መጓደል የተነሳ የሚፈጠር ነገር ነው። እነዚህ ነገሮች ከሰው ልጅ እድሜ እኩል ያስቆጠሩ ዘመን የተሻገሩ ክፉ ነገሮች ሲሆኑ ንጹህ የሆኑ ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ገብተው የሚሰቃዩ ሲሆን በእዚህም የተነሳ በሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወት ላይ አስደንጋጭ ውጤት አስከትሉዋል። የእግዚአብሄር ነጻ የማውጣት ተግባር ለእርሱ ሐዘናቸውን እና ጭንቀታቸውን ለሚገልጹት ሰዎች ደግሞ የደህንነት  ድርጊት ነው። የእግዚብሔር ጣልቃ ገብነት የደህነት እስር ቤት በር ይከፍታል። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የሚገኙ ብዙ መዝሙሮች የሚተርኩት እና የሚያከብሩት ይህንኑ የግል ሕይወት ውስጥ የተንጸባረቀውን የደህንነትን ታሪክ ያውጁሉ ያከብሩታልም እንዲህ ይላሉ “እርሱ የተጨነቀውን ሰው ጭንቀት፣ አልናቀም፤ ቸልም አላለምና፤ ፊቱንም ከእርሱ አልሰወረም፤ ነገር ግን ድረስልኝ ብሎ ሲጮኽ ሰማው” (መዝ. 22፡24) በማለት ይዘምራሉ። የእግዚአብሔርን ፊት ማሰላሰል ማለት የእርሱን ወዳጅነት፣ የእርሱን ቅርበት እንዲሰማን በማድረግ የደህንነታችን ምልክት ይሆናል ማለት ነው። “መከራዬን አይተሃልና፤ የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል. . . ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው” (መዝሙር 31፡7-8)። የድሆችን እግር በስፊ ቦታ ላይ እንዲቆም በማድረግ እነርሱን “ከአዳኝ ወጥመድ” ማዳን እና በመንገዳቸው ውስጥ ከተሰወረ ወጥመድ በመታደግ በፍጥነት ወደ ፊት እንዲጓዙ እና ሕይወትን በንፅህና እንዲመለከቱ ማድረግ ማለት ነው። የእግዚአብሄር ደኅንነት መልካም አቀባበል ላደረጉ ድሆች የሚያገለግል ሲሆን ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ የእርሱን ጓደኝነት እንዲለማመዱ ያስችላቸዋል። ይህም በተጨባጭ እና በሚታይ መልኩ ትክክለኛ የሆነ የደህንነት መንገድ እየመጣ መሆኑን ያሳየናል። “እያንዳንዱ ክርስቲያን እና እያንዳንዱ ማኅበረሰብ ድሆችን ነፃ ለማውጣት፣ ለማብቃት እና የመላው ማኅበርሰብ አካል እንዲሆኑ በመርዳት የእግዚአብሔር መሣሪያ እንዲሆኑ ተጠርቷል። በተጨማሪም ለድሆች ጩኸት እና ድሆችን ለመርዳት ትኩረት እንድንሰጥ ይረዳናል።

5.     ብዙዎቹ ድሆች በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ከተገለጸው ከበርቴሌሜውስ ታሪክ ውስጥ ተደብቀ ይገኛሉ። በርቴሌሜዎስ ዐይነ ስውር የነበረ ሰው ሲሆን “በመንገድ ዳር ቁጭ ብሎ ምጽዋዕት ይለምን ነበር” አንድ ቀን ኢየሱስ በእዚያ እያለፈ መሆኑን በተረዳ ጊዜ “በታላቅ ድምጽ የዳዊት ልጅ የሆንክ ኢየሱስ ሆይ ማረኝ” እያለ ጮኸ። “ብዙዎቹ ግን ዝም በል አትጩኽ ብለው ገሰጹት፣ ነገር ግን እርሱ አብዝቶ ጮኸ”። የእግዚኣብሔር ልጅ ግን የእርሱን ጩኸት ሰማ፡ “ምን እንዳደርግልህ ተፈልጋልህ?” በማለት ጠየቀው። ዐይነ ስውር የነበረው ሰውም “መምህር ሆይ መልሼ እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የተገለጸው ጩኸት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ይፋ ሲሆን እናያለን። በርቴሌሜዎስ በጣም ድሃ የነበረ፣ በዐይኑ ማየት የማይችል እና በእዚህም ምክንያት ሥራ መሥራት የማይችል ሰው በመሆኑ አቅም የለሽ እንዲሆን አድርጎት ነበረ። ዛሬም ቢሆን የእዚህ ዓይነት የኑሮ አካሄድ የሚከተሉ ሰዎች ብዙ ናቸው። በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የተደረጉ ማሻሻያዎች ቢኖሩም መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ባለመሟላታቸው የተነሳ፣ በተለያዩ የማህበራዊ ባርነት ስራዎች ምክንያት ከእዚህ ውስጥ ለመውጣት አዳጋች በመሆኑ የተነሳ ብዙ ሰዎች መሰረታዊ የሚባሉ ነገሮች ሳይሟሉላቸው በመኖር ላይ የገኛሉ። ዛሬም ቢሆን እንደ በርቴሌሜውስ በመንገድ ዳር ቁጭ ብለው የሚለምኑ ለሕይወታቸው ትጉም አጥተው ሕልውናቸውን እስከ መጠራጠር የደረሱ ስንት ሰዎች አሉ? አንድ ሰው ወደ እነርሱ መጥቶ "አይዞህ/ሺ! ተነስ/ሺ እሱ እየጠራህ/ሺ ነው” የሚለውን ጥሪ እየተጠባበቁ የሚገኙ ብዙ ድሆች አሉ። በሚያሳዝን መንገድ በተቃራኒው እየተከሰተ ይገኛል፣ ድሆች ድምጻቸው እንዳይሰማ እየተደረገ፣ ጸጥ ብለው እንዲኖር እየተገደዱ እየተጨቆኑ ይገኛሉ። ድምጻቸው እንዳይሰማ ይደረጋል፣ ድኾችን ከመፍራት የተነሳ እነርሱን እንደ ደሃ አድርጎ ከመቁጠር ባሻገር በመሄድ የጸጥታ፣ የደህንነት እና ያለመረጋጋት ይፈጥራሉ በሚል ህሳቤ የተነሳ ከዕለት ተዕለት የሕይወት ልምዳችው ተነጥለው እና ተገልለው በሩቁ እንዲኖሩ ይደረጋሉ። አዝማሚያው በእኛ እና በእነርሱ መካከል ርቀት መፍጠር ይመስላል፣ ይህንንም በማድረጋችን በግንዛቤ እጥረት ይሁን በሌላ ምክንያት. . . እነራኡን በምናገልበት ወቅት ሁሉ ድሆችን የማያገል እና ሁል ጊዜ ለድሆች ቅርብ የሆነውን፣ ወደ እርሱ የሚጠራቸው እና የሚያጽናናቸውን  ጌታ እየራቅን መሆናችንን እንዘነጋለን። ነብዩ ኢሳያስ በምዕራፍ 58፡6-7 ላይ “የጭቈናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ድኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቈተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሣው አይደለምን?” በማለት በቃሉ በአማኞች ሕይወት ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው የአኗኗር ዘይቤ ይናገራል። እንደ እነዚህ ያሉ መልካም ተግባራት ደግሞ ኃጢኣትህ ይቅር እንዲባልልህ እና “የዚያን ጊዜ ትጣራለህ፤ እግዚአብሔርም ይመልስልሃል፤ ለርዳታ ትጮኻለህ፤ እርሱም፣ ‘አለሁልህ’ ይልሃል። “የጭቈና ቀንበር፣ የክፋትን ንግግርና ጣት መቀሰርን ከአንተ ብታርቅ፣ በምትጠራኝ ጊዜያት ሁሉ እኔ እሰማሃለው ያል እግዚኣብሔር” (ኢሳ. 58፡9)።

6.     የእግዚኣብሔርን መኖር በቅድሚያ ያወቁትና እርሱ ለሕይወታቸው ቅርብ መሆኑን በቅድሚያ የመሰከሩት ድሆች ነበሩ። እግዚአብሔር የገባውን ቃል በታማኝነት ይጠብቃል፣ በጨለማ ውስጥ ብንሆንም እንኳን የእርሱ ፍቅርና መጽናኛ ሁሌም ከእኛ ጋር ነው። ይሁን እንጂ ድህነትን የሚያስወግድ ሁኔታ ለመቋቋም ይችሉ ዘንድ ድሆች ለእነርሱ የሚያስቡ፣ ልባቸውን እና የሕይወታቸውን በር በመክፈት እነሱን እንደ ጓደኛ እና ቤተሰብ አድርገው የሚቀበሉ ወንድሞች እና እህቶች መኖራቸውን ማወቁ ይፈልጋሉ። በዚህ መንገድ ብቻ ነው "በሕይወታቸው ውስጥ ያለው የመዳን አቅም" እና "በቤ ተክርስቲያኗ መንፈሳዊ የንግደት መንገድ ውስጥ በርትተን መጓዝ የምንችለው በእዚሁ መልኩ ብቻ ነው”።

በዚህ የዓለም የድኾች ቀን በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ “የተጎሳቆሉት ይበላሉ ይጠግባሉ” (መዝ. 22፡27) የሚሉትን ቃላት ተጨባች በሆነ መልኩ ለመመስከር ተጋብዘናል። በኢየሩሳሌም ቤተመቅደስ ውስጥ ከመሥዋዕት ሥነ ሥርዓት በኋላ የምግብ ግብዣ እንደ ሚደረግ እናውቃለን። ይህም ባለፈው አመት ዓለማቀፍ የድኾች ቀን በተከበረበት ወቅት በአብዛኞቹ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ በተግባር የታየ ጥሩ የሚባል ተመክሮ ነበር። ብዙ ሰዎች (ድሆች) የሞቀ መኖሪያ መግኘት ችለዋል፣ የአንድ ክብረ በዓል ደስታ ተካፋይ በመሆን የቀረበውን ምግብ በመቋደስ በቀላሉ በወንድማማችነት መንፈስ ለመካፈል ችለዋል። በዚህም ዓመት ይህ ዓለማቀፍ የድኾች ቀን በሚከበርበት ወቅት በተመሳሳይ መንገድ ከድሆች ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን የምንቀጥልበት አጋጣሚ እንዲሆን ያስፈልጋል። አንድ ማህበረሰብ አንድ ላይ በመጸለይ፣  በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውና በጥንት ጊዜ የነበሩ ክርስቲያኖች ያደርጉት እንደ ነበረው ምግባችንን አብረን በዕለተ ሰንበት አብረን መቋደስ ይኖርብናል፡ “እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቍረስና በጸሎት ይተጉ ነበር።ያመኑት ሁሉ በአንድነት ነበሩ፤ ያላቸውንም ሁሉ የጋራ አደረጉ። ሀብታቸውንና ንብረታቸውንም እየሸጡ ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልገውን ያህል ይሰጡት ነበር” (የሐዋሪያት ሥራ 2፡42,44-45)።

7.     ብዙ ዓይነት የድህነት ዓይነቶችን ለመዋጋት የክርስቲያን ማኅበርሰቡ በእየቀኑ የተለያየ ዓይነት ተነሳሽነት እየወሰደ ቢሆንም አሁንም ቢሆን በዓይኖቻችን በእየለቱ በየጎሬቤቶቻችን የምናያቸው ብዙ ዓይነት ድህነቶች ይገኛሉ። በከፍተኛ ድህነት በሚሰቃየው ዓለማችን ይህንን ችግር ለመቅረፍ የምናደርገው እርምጃ በጣም ውስን፣ ደካማ እና በቂ አለመሆኑን ተገንዝበን በተቻለ መጠን ትብብር በመፍጠር ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ለመድረስ እንድንችል መትጋት ይኖርብናል። እኛ በእምነታችን ምክንያት እና በልግስና መንፈስ ተነሳስተናል ቢሆንም ሌላ ዓይነት ተመሳሳይ በሆነ ዓላማዎች የተመሰረቱ  ርዳታ እና ትብብር የሚያደጉ ተመሳሳይ ዓላም ያላቸው ሰዎች እንዳሉም እናውቃለን፣ እኛ ግን የምናደገው ነገር ሁሉ ሰዎችን ወደ እግዚኣብሔር እና ወደ ቅድስና የሚመራ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። እኛ የተጠራነው የተለያዩ ተመክሮዎቻችንን በማንሳት ውይይት በማድረግ እና በትህትና አገልግሎታችንን ለሌሎች በመስጠት እና በመተባበር፣ ምንም ዓይነት ክብር እና ዝና ሳንፈልግ ተመጣጣኝ የሆነ ወንጌላዊ አገልግሎት ለሁሉም እንድንሰጥ ነው።

8.    ለድሆች አገልግሎት ለመስጠት የምናደርገው ጥረት በማኅበርሰቡ ውስጥ ቀዳሚ የሆነ ስፍራ ለማግኘት የምናደርገው ግብግብ አንዱ አካል ሊሆን በፍጹም አይገባም። ይልቁኑ ይህንን አገልግሎት በትህትና በመፈጸም ይህ መልካም ተግባር የመነጨው ከመንፈስ ቅዱስ መሆኑን በመገንዘብ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ምላሽ እና እግዚኣብሔር ለእኛ ቅርብ እንደሆነ የሚያሳዩን ድርጊቶች መሆን ይኖርባቸዋል። ድሆችን የመቅረቢያ መንገድ ስንፈልግ የመጀመሪያ ተግባር ሊሆን የሚገባው ዓይናችንን እና ልባችንን ለእነርሱ መክፈት ነው። የሕይወታችን እውነተኛዎቹ ተዋናዮች ጌታ እና ድሆች ናቸው። ልያገለግል የሚፈልግ ሰው እግዚኣብሔር መኖሩን ይሚገልጽ የእርሱ አዳኝ መሆኑን  ለማሳወቅ የሚሰራ የእግዚአብሔር እጅ መሳሪያ ነው። “እውነት እላችኋለሁ ከሁሉም ለሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል” (ማቴ፡ 25፡40)።

 

8. ሐብትን እና ሀብታም የሆኑትን ሰዎች ብቻ የሚያወድስ፣ ስልጣን እና ገነዘብ ያላቸውን ሰዎች ለመምሰል እና ለመከተል የሚደረግ ሙከራ በሚስተዋልባት ዓለማችን እኛ ለተገለሉት ድሃ የሆኑ ሰዎች እና እንደ ቆሻሻ የሚቆጠሩ እና የኃፍረት መገለጫ የሆኑ ቁሶች ተደርገው ለሚታዩ ድሆች የምንሰጠው አገልግሎት የእኛ መንገድ ከዓለም መንገድ ምን ያህል ለየት ያለ እንደ ሆነ ያሳየናል። የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላቶች ወንጌላዊ ሙላት ያለው ምስክርነት ደካማ የሆኑ እና እድለኛ ያልሆኑ ሰዎችን ከክርስቶስ አካል ክፍሎች ጋር አንድነት እንዲፈጥሩ ማገዝ እንደ ሚገባ ጥሪ ያቀርባል፡ “አንድ የአካል ክፍል ሲሰቃይ ሌላውም አብሮ ይሰቃያል፡ አንዱ የአካል ክፍል ሲከበር ሁሉም አብረው ይደሰታሉ” (1 ቆሮ 12፡26) በማለት ይገልጻል። በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ሮም ሰዎች በጻፈው መልእክቱ “ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ።  እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ” (ሮሜ 12፡15-16)። ይህ አንድ የኢየሱስ ሐዋሪያ የሆነ ሰው ጥሪ ነው፡ እኛም ዘወትር ጥረት ማድረግ የሚገባን ይህንን “የክርስቶስ አስተሳሰብ ለመላበስ ነው”።

9. የተስፋ ቃል እምነት የሚያመጣው ተፈጥሯዊ የሆነ ተግባር ነው። የድሆች ጩኸት ነጻ ለመውጣት የሚደርገ የተስፋ ለቅሶ ነው። ይህ ተስፋ ደግሞ የተመሰረተው በእርሱ የሚታመኑትን ሰዎች ሁሉ ቸል በማይለው በእግዚኣብሔር ላይ ነው።

10. ድሆችን ለማገልገል ኃላፊነቱ የተጣለባቸውን ውንድሞቼ ጳጳሳትን፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን፣ እንዲሁም ገዳማዊያን ገድማዊያትን እና ምዕመናንን፣ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ወንድ እና ሴቶችን ሁሉ በቁምስና፣ በማኅበራት እና በቤተ ክርስቲያን ንቅናቄዎች ሁሉ ለድሆች ለቅሶ ተመጣጣኝ እና ተጨባጭ የሆነ ምላሽ በመስጠት በተለይም ደግሞ ይህ ዓለማቀፍ የድሆች ቀን በሚከበርበት ቀን በዚህ መልኩ ለየት ባለ እና በአዲስ መልክ ስብከተ ወንጌልን የምናደርገበት ቀን ይሆን ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ድሆች በእየቀኑ ስብከተ ወንጌልን ያደርጉልናል፣ በእየቀኑ የቅዱስ ወንጌል ውበት እንድንመለከት ይረዱናል። ይህ የጸጋ እድል እንዳያመልጠን። እያንዳንዳችን ለድሆች መክፈል ይገባናል ምክንያቱም እጆቻችንን አንዱ ለሌላኛው በመዘርጋታችን የእኛን እምነት የሚያጠናክር የልግስና እንቅስቃሴያችን  ወደ እኛ በመምጣት ላይ የሚገኘውን ጌታ ለመገናኘት ያስችለን ዘንድ በሕይወት ጉዞ ላይ በተስፋ ተሞልተን መንገዳችንን መጓዝ እንድንቀጥል ያስችለናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

 

 

17 November 2018, 17:30