ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “በቅድሚያ በጸሎት ወደ እግዚ/ር ቀጥሎ ወደ ተቸገሩ ሰዎች መሄድ ይኖርብናል”

“ኢፍትሃዊነት የድህነት ሁሉ ምንጭ ነው፡ የድሆችን ጩኸት ማዳመጥ ተገቢ ነው”

“ይህ ችግረኛ  ጮኸ፤ እግዚአብሔርም  ሰማው” (መዝሙር 34፡7) በሚል መሪ ቃል ሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን በሕዳር 09/2011 ዓ.ም ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል። ይህ ሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን በሕዳር 09/2011 ዓ.ም ረፋዱ ላይ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መሪነት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  በተካሄድ መስዋዕተ ቅዳሴ ተከብሮ ማለፉን ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በሮም ከተማ የሚገኙ በርካት ድሆች መሳተፋቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። በወቅቱ በእርሳቸው መሪነት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “ኢፍትሃዊነት የድህነት ሁሉ ምንጭ ነው፡ የድሆችን ጩኸት ማዳመጥ ተገቢ ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ - ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍርንቸስኮስ “ይህ ችግረኛ   ጮኸ ፤  እግዚአብሔርም   ሰማው (መዝሙር 34፡7) በሚል መሪ ቃል በሕዳር 09/2011 ዓ.ም በተከበረው ሁለተኛው ዓለማቀፍ የድሆች ቀን ላይ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያሰሙትን ስብከት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማቴ. 14፡22-) ኢየሱስ የፈጸማቸውን ሦስት ዋና ዋና ተግባራትን  እንመለከታለን። በመጀመሪያ ዕለቱ ገና ሳይመሽ በፊት ኢየሱስ መሄዱን” እንመለከታለን። ኢየሱስ በአምስት እንጀራ እና በሁለት ዓሳ በጣም ብዙ ሕዝብ በመመገቡ የተነሳ ይህንን የእርሱን ድርጊት በማድነቅ በዚህም የተነሳ እርሱን ይከተሉ የነበሩ ሰዎችን ጥሎ ሲሄድ እናያለን። ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ተዓምራዊ ስኬት የተነሳ መኩራራት ፈልገው የነበረ ሲሆን ኢየሱስ ግን “ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው (ማቴ. 14፡22-23)። ምንም እንኳን ሕዝቡ ኢየሱስን አብዝቶ ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡን አሰናብቶ ብቻውን ይሄዳል፣ የሕዝቡ ደስታ እየጨመረ በመጣበት ወቅት ኢየሱስ እነርሱን ተሰናብቶ ልጸልይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። መዐበሉ ውሃውን በከፍተኛ ሁኔታ ያናውጥ በነበረበት በውድቅት ሌሊት ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። በእነዚህ ሁሉ ድርጊቶቹ ኢየሱስ ከተጽኖ ነጻ በሆነ መልኩ ሲንቀሳቀስ እናያለን፣ በቅድሚያ ተዓምራዊ የሆነ ስኬት ወደ ኋላ ትቶ ሲሄድ እናያለን፣ ከዚያም ባሕሩን ጸጥ ሲያደርገው እናያለን። ኢየሱስ ጥሎ የመሄድ ብርታት እንዲኖረን ያስተምረናል፡ ልብን የሚያማልል ስኬት እና ነፍስን ሊገድል የሚችል መረጋጋት ጥለን ወደ ፊት መሄድ እንዳለብን ያስተምረናል።

የት ለመሄድ? በጸሎት ወደ እግዚኣብሔር፣ ከዚያም በኋላ ደግሞ ወደ ተቸገሩ ሰዎች በፍቅር እንድንሄድ ያስተምረናል። እውነተኛ የሆነ የሕይወት ሐብት ሊሆኑን  የሚገባው እግዚአብሔር እና ባልንጀራዎቻችን ብቻ ናቸው። ኢየሱስ ያስተማረን በቅድሚያ ወደ እግዚኣብሔር የሚወስደውን ከዚያም በኋላ ደግሞ ወደ ወንድም እና እህቶቻችን መመለስ የምያስችለን ጎዳና ላይ እንድንራመድ ነው። በእለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ በምናገኛቸው ጥቂት ደስታዎች ምክንያት የተፈጥረውን የተደላደለ እና ምቹ የሆነ ሕይወት፣ እንዲሁም ምቹ የሆነውን የግጦሽ መስክ በመተው ከእነዚህ ነገሮች ተለይተን እንድንሄድ ኢየሱስ የፈልጋል። የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሥራ ፈት ሆነው እንዲሁ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ አልፈለገም። ልክ እንደ ኢየሱስ በቅጽበት በመጓዝ፣ ግዜያዊ የሆኑ ክብሮችን ወደ ኋላ አሽቀንጥሮ በመጣል፣ በቁሳቁስ ነገሮች ላለመሳብ ጥንቃቄ በማድረግ ወደ ፊት እንዲጓዙ ይፈልጋል። ዛሬ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን በጻፈው እና በሁለተኛነት በተነበበው የምጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ “እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ” (ኤፌ 2፡19) በማለት ሲናገር አዳምጠናል። እነርሱ ተጓዢ እንዲሆኑ ተጠርተዋል። ነገሮችን ለማጋበስ መኖር የለብንም፣ እኛ ክብርን የምናገኘው አላፊ የሆኑ ነገሮችን ወደ ኋዋላ አሽቀንጥረን በመተው በማያልፉ ዘለዓለማዊ በሆኑ ነግሮች ነው። በሐዋርያት ሥራ (28፡11-14) ላይ እንደ ተጠቀሰው ሁል ጊዜ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳለች፣ ጥላ በመሄዷ ምቾት የተሰማት እና ታማኝ እንደ ሆነች ቤተ ክርስቲያን እንዲያደርገን እግዚኣብሔርን እንልመነው። ጌታ ሆይ ሥራ ፈቶ ከመረጋጋት፣ ምቹ እና የተረጋጋ ከሆነ ሥፍራ ውስጥ መውጣት እንድንችል እርዳን። በሕይወታችን ላይ ጫና ከሚፈጥሩ ነገሮች ሁሉ ነጻ ሆነን እንኖር ዘንድ እርዳን፣ ሁልጊዜ ቀጣይነት ባለው መልኩ ክብር በመሻት እንዳንኖር እርዳን። ጌታ ሆይ “ጥለን” በመሄድ አንተ ባሳየህን መንገድ ላይ ብቻ መጓዝ እንችል ዘንድ ወደ እግዚኣብሔር እና ወደ ባልንጀሮቻችን በሚመራን መንገድ ላይ ብቻ መጓዝ እንችል ዘንድ አስተምረን።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማቴ. 14፡22-) ኢየሱስ ከፈጸማቸው ሦስት ዋና ዋና ተግባሮች መካከል ሁለተኛው በውድቅት ሌሊት እንኳን ሳይቀር ኢየሱስ በዚያ እንደ ሚኖር ያረጋግጥልናል። በውድቅት ሌሊት በባሕሩ ላይ እየተራመደ ወደ ደቀ-መዛሙርቱ ሲሄድ እናያለን (ማቴ 14፡25)። በዚህ ሁኔታ "ባሕር" የሚለው ቃል በእርግጥ “ሐይቅ” የሚለውን ሐሳብ የምያስተጋባ ሲሆን ነገር ግን በጣም በከፍተኛ ደረጃ ጥልቀት ያለው በመሆኑ የተነሳ “ባሕር” የሚለው ሐሳብ ክፉ መንፈስ የሚለውን ሃሳብ ያስተጋባል። በዚህ አረዳድ ኢየሱስ ወደ ደቀ-መዛሙርቱ በባሕር ላይ በመራመድ መሄዱ የሚያሳየው የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት በሆነው ክፉ በሆነ መንፈስ ላይ መረማመዱን ያሳያል። እናም ይህ እውነተኛ ትርጉሙ ነው- በኃይሉ ድል ማድረጉን የሚያሳይ ትዕይንት ሳይሆን ይልቁንም ኢየሱስ ከመጀመሪያው አንስቶ በጠላቶቹ ላይ ማለትም ሰይጣንን፣ ኃጥያትን፣ ሞትን፣ ፍርድን፣ ዓለማዊነትን ድል ማድረጉን የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ማረጋገጫ ነው። ኢየሱስ ዛሬ ለእኛ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” (ማቴ 14፡27) ይለናል።

አብዛኛውን ጊዜ የሕይወታችን ጀልባ በንፋስ አማካይነት ሲወዛወዝ ሲገፋ እናያለን። አንዳንዴ ምንም እንኳን ባሕሩ ጸጥ ያለ ቢሆንም የእኛ ጀልባ ግን መናወጧን ትቀጥላለች። እኛ በእንደነዚህ ዓይነት መዐበል በምንናወጥበት ወቅት ይህ ችግር የእኛ ችግር ብቻ አድርገን እንቆጥር ይሆናል። ነገር ግን እኛን ልያሳስበን የሚገባው ቁምነገር በጊዜያዊ መልኩ እያጋጠመን ያለው መዐበል ሳይሆን ነገር ግን በሕይወት ሂደት ውስጥ እንዴት እየቀዘፍን መሄድ እንዳለብን ማሰብ ያስፈልጋል። በሕይወት ሂደት ውስጥ በሚገባ እና ተገቢ በሆነ ሁኔታ እየቀዘፍን መሂድ እንችል ዘንድ በጀላባችን ውስጥ ኢየሱስን ማስገባት ይኖርብናል። የጉዞ ሂደታችንን በሚገባ ይቆጠጠርልን ዘንድ የሕይወታችንን አቅጣጫ መጠቆሚያ ለእርሱ ማስረከብ ይኖርብናል። ከሞት ወደ ሕይወት ከስቃይ ወደ ተስፋ የሚያሻግረን እርሱ ብቻ ነው፣ በይቅርታው አማካይነት ልባችንን የሚፈውሰው እርሱ ብቻ ነው፣ ከፍርሃት በመላቀቅ በራስ የመተማመን መንፈስ የሚሰጠን እርሱ ብቻ ነው። ዛሬ ኢየሱስ በሕይወታችን ጀልባ ላይ ይሳፈር ዘንድ እንጋብዘው። ዛሬ ደቀ መዛሙርቱ እንደ ተገነዘቡት እኛም ኢየሱስ በሕይወታችን ጀልባ ላይ በሚሳፈርበት ወቅት ሁሉ ማዕበሉ ጸጥ እንደ ሚል እና ጀልባችን እንደ ማይሰምጥ እንገነዘባለን። እርሱ በእኛ የሕይወት ጀልባ ላይ አብሮን ከተሳፈረ ጀልባችን በፍጹም ልትሰጥም አትችልም። እርግጠኞች መሆን የምንችለው ኢየሱስ ሲኖር ብቻ ነው። በቃላቸው ሳይሆን በሕይወት ተጨባጭ በሆነ መልኩ ተግብራቸውን የሚያስዩ ሰዎች ትልቅ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ሌሎች እውነተኛ የሆነ መጽናናት እንዲያገኙ ማድረግ የምንችለው በኢየሱስ ስም ብቻ ነው። ከንቱ በሆኑ ቃላት ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ከእኛ ጋር ካለ ትክክለኛ የሆነ የማበረታቻ ቃላትን እንድንለግስ ጥንካሬውን ይሰጠናል። ጌታ ሆይ በአንተ ተጽናንተን ሌሎችን ማጽናናት እንችል ዘንድ ማረጋገጫህን ስጠን።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ማቴ. 14፡) ኢየሱስ ከፈጸማቸው ሦስት ዋና ዋና ተግባሮች መካከል ሦስተኛው እና የመጨረሻው ባሕሩ በከፍተኛ አውሎ ንፋስ በተናወጠ ጊዜ ኢየሱስ እጁን መዘርጋቱ ነው። በፍርሃት እና በጥርጣሬ የተነሳ እየሰመጠ የነበረው ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ አድነኝ” በማለት ሲማጸነው ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ስያድነው እናያለን። ራሳችንን በጴጥሮስ ቦታ ማስቀመጥ እንችላለን፣ እኛ እመነታችን ትንሽ የሆነ፣ መዳን የምያስፈልገን ሰዎች ነን። እኛ እውነተኛ የሆነ ሕይወት እንዲኖረን እንፈልጋለን፣ በዚህም ምክንያት ከክፉ መንፈስ እንርቅ ዘንድ እንዲረዳን ኢየሱስ እጁን እንዲዘረጋልን ልንጠይቀው ይገባል። ይህም የእመንት መጀመርያ ነው፣ ራሳችን ለራሳችን ሙሉ እንደ ሆንን አድርገን እንድንቆጥር የሚያደርገንን የእብሪት መንፈስ አስወግደን ደህንነት እንደ ሚያስፈልገን ተገንዝበን የእርሱ እገዛ እንደ ምያስፈልገን ማወቅ ይገባል። እምነት የሚያድገው በዚህ ሁኔታ ነው፣።

ኢየሱስ የጴጥሮስን ጩኸት ሰማ። እኛም የሌሎች ሰዎች ለቅሶ ለመስማት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እንለምነው። የድሆችን ጩኸት፣ በማሕጸን ውስጥ ያሉ ልጆችን ጩኸት፣ የተራቡ ሕጻናት ጩኸት፣ በተለያዩ ጦርነቶች ምክንያት እየተሰቃዩ ያሉ የወጣቶችን ጩኸት መስማት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን እንለምነው። በጓደኛ እጦት ምክንያት እያለቀሱ፣ እየጮኹ የሚገኙ ሰዎችን ጩኸት ለመስማት እንችል ዘንድ ጸጋውን እንጠይቅ። ከቀን ወደ ቀን የድኾች ጩኸት እየበረታ እየጨመረ ቢገኝም ነገር ግን በተቃራኒው ከቀን ወደ ቀን የድሆች ድምጽ መሰማቱ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ይገኛል። በእየቀኑ ጩኸታቸው እየበረታ ቢሄድም ነገር ግን ቀን በቀን ጩኸታቸው ትንሽ ትንሽ ብቻ ነው እየተሰማ የሚገኘው።

እኛ አማኞች እንደ መሆናችን መጠን ኢየሱስ ለእኛ እጁን እንደ ሚዘረጋልን ሁሉ እኛም ለድሆች እጃችንን መዘርጋት ይኖርብናል። የድሆችን ጩኸት እግዚኣብሔር ይሰማል።

ጌታ ሆይ እጅህን ዘርግተህ ያዘን። እንተ እንደ ወደድከን እኛም እንድንዋደድ እርዳን። አላፊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ወደ ኋላ አሽቀንጥረን እንጥል ዘንድ እርዳን፣ በነጻ የተቀበልነውን በነጻ ለመስጠት እንችል ዘንድእርዳን። አሜን!!

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 November 2018, 17:18