ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በላውሬንትኖ የመካነ መቃብር ስፍራ ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በላውሬንትኖ የመካነ መቃብር ስፍራ  

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ “ማህደረ ትውስታ እና ተስፋ በፍጹም ማጣት የለብንም”

በመላው ዓለም በምትገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በጥቅምት 23/2011 ዓ.ም  “ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሰዎች ሁሉ የምናስስበት” የሙታን ቀን ተዘክሮ ማለፉ ይታወሳል። በዚህ ዕለት ቤተ ክርስቲያ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን እህት ወንድሞቻችንን በማሰብ፣ ለእነርሱ መጸለያችንን አጠናክረን እንድንቀጥል እና እግዚኣብሄር ምሕረቱን እንዲያወርድላቸው የምሕረት አባት የሆነውን እርሱን እንድንማጸን ቤተ ክርስቲያን ታሳስበናለች። እኛም የበለጠ እምነታችንን አጠናክረን በመቀጠል ክርስቲያኖች ሁሉ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ በማመን በተስፋ የምንጓዝበት ዕለት እንዲሆን በጸሎት የምንተጋበት ቀን ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በሕይወት ሂደት ውስጥ እያንዳንዳችን በሞት የተለዩን ወላጆች፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ እንዲሁም የምናውቃቸውን ሰዎች በሞት መነጠቃችን ይታወቃል። ሞት ለሁላችንም የማይቀር እዳ ነው። ክርስቶስ ሞቶ፣ ሞትን ድል አድርጎ እንደ ተነሣ ሁሉ እኛም ክርስቲያኖች ከሞት በኋላ በክርስቶስ አማካይነት ሕይወት እንደ ምናገኝ፣ በእርሱ ምሕረት ለዘለዓለም እንደ ምንኖር ተስፋችንን በድጋሚ የምናለመልምበት ቀን ነው።

ቀደምስ ሲል ለመገለጽ እንደ ሞክርነው በጥቅምት 23/2011 ዓ.ም “የሙታን ቀን ተዘክሮ ማለፉ ይታወቃል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህን ሙታን የሚዘከሩበትን ቀን ለማክበር በሮም ከተማ ውስጥ ወደ ሚገኘው ላውሬንትኖ በመባል ወደ ሚታወቀው የመካነ መቃብር ስፍራ በመሄድ በዚያ ስፍራ በምገኘው የጸሎት ቤተ መስዋዕተ ቃዳሴ ከማሳረጋቸው በፊት በዚያ ስፍራ የምገኘውን መካነ መቃብር መጎብኘታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

በሮም ከተማ ውስጥ 4 ትላልቅ የሚባሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር ቦታዎች እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ላለፉት ሦስት አመታት ይህ አመታዊ የሙታን በዓለ በተከበረበት ቀን ሦስቱ መካነ መቃብር ስፍራዎች በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መጉብኘታቸው የሚታወስ ሲሆን ይህ  (ጥቅምት 23/2011 ዓ.ም) በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የተጎበኘው የላውሬንቲኖ መካነ መቃበር 4ኛው  መካነ መቃብር እንደ ሆነ ለመረዳት ተችሉዋል።

በጥቅምት 23/2011 ዓ.ም “የሙታን ቀን ተዘክሮ ባልፈበት ወቅት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይህንን በዓል ለምዘከር በማሰብ በሮም ከተማ ውስጥ ወደ ሚገኘው ላውሬንትኖ በመባል በሚታወቀው የመካነ መቃብር ስፍራ ተገኝተው ጸሎት ካደረጉ በኋላ በዚያ ስፍራ በሚገኘው የጸሎት ቤተ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ግለጹት “ማህደረ ትውስታ እና ተስፋ በፍጹም ማጣት የለብንም” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዛሬው ሰርዓት አምልኮ ትክክለኛ እና ተጨባጭ እንደ ሆነ በመግለጽ ስብከታቸውን የጀመሩት ቅዱስነታቸው ሕጻናት እንኳን ሳይቀር ሊገነዘቡት ወይም ሊረዱት የሚችሉት ያለፈውን፣ የአሁኑን፣ የወደፊቱን ሦስት የሕይወት ገፅታዎች ያመለክተናል ብለዋል።

ዛሬ እየዘከርነው የምንገኘው ያለፈውን ማህደረ ትውስታ ነው፣ ከእኛ በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩንን ሰዎች የምናስታውሰበት፣ በመንፈስ ከእኛ ጋር መሆናቸውን የምንገነዘብበት፣ ለእኛ ሕይወት ሰተው ያለፉ ሰዎችን የምንዘክርበተ ዕለት ነው በማለት ሰብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በአጠቃላይ ማሕደረ ትውስታችንን በመፈተሽ መልካም የሆኑ ነገሮችን ፈጽመው ያለፉ ወገኖቻችንን ማስታወስ ያስፈልጋል ብለዋል። በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ በሚገኙ ሕዝቦች ውስጥ የተተከለ ታሪክ፣ አብሮዋቸው በመጓዝ ሕዝቡ ጠንካራ እንዲሆን የሚያደርገው ማሕደረ ትውስታ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እኛ ብቻችንን እንዳልሆንን፣ እኛ አንድ ሕዝብ እንደ ሆንን፣ እኛ ታሪክ ያለን ሕዝቦች እንደ ሆንን፣ እኛ ያለፈ ታሪክ እንዳለን እንድንረዳ የምያደርገን ማሕደረ ትውስታ ነው ማለታቸው ለመረዳት ተችሉዋል።

በሕይወት ዘመናቸው ከእኛ ጋር መልካም የሚባል ሕይወት አሳልፈው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሰዎችን ማስታወስ በራሱ ቀላል የሆነ ነገር እንዳልሆን በመገልጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እኛ ብዙን ጊዜ ወደ ኋላ በመሄድ ያለፈው ሕይወታችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ ሕዝቦቻችንን . . . ወዘተ ማስታወስ እንቸገራለን ያሉት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ዛሬ የሙታን ቀን በምንዘክርበት ወቅት ያለፈው ጊዜያችንን እንድናስታውስ ይረዳናል፣ የእኛ ስር መሰረት ምን እንደ ሆን እንድናስብ እና እንድናስታውስ ያግዘናል ብለዋል።

ዛሬ (ጥቅምት 23/2011 ዓ.ም ) ይህንን የሙታን ቀን በምንዘክርበት በአሁኑ ወቅት ተስፋችን በድጋሚ እንዲለመልም ይረዳናል በማለት ስበከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ዛሬ ከዮሐንስ ራእይ (21፡2) ተወስዶ በተነበበው ሁለተኛው ምንባብ ላይ እንደ ተጠቀሰው “አዲስ ሰማይ እና አዲስ መድር በቅዲስቱቷ ኢየስሩሳሌም እንደ ሚጠብቀን” በመገልጽ ተስፋችን እንዲለመልም አድርጎታል ያሉት ቅዱስነታቸው “ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ” (21፡2) በማለት መልካም እና ሁሉም ሰው ሊረዳው በሚችለው መልኩ በመግለጽ ተስፋችንን እንዲለመልም አድርጎታል ያሉት ቅዱስነታቸው ይህም ያለፈውን ጊዜ በማስታወስ የወደ ፊቱን ነገር በተስፋ በመጠባበቅ የአባታችን ሰማያዊ ፍቅር እንደ ሚጠብቀን ተስፋ እንድናደርግ ይረዳናል ብለዋል።

በማሕደረ ትውስታ እና በተስፋ መካከል የሚገኝ ሦስተኛው የሕይወት ገጽታ መኖሩን በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ይህም እኛ በሕይወት ሂደት ውስጥ ልንከተለው የሚገባው መንገድ ነው ብለዋል። ታዲያ ይህንን መንገድ ያለምንንም ስህተት እንዴት ነው መጓዝ የምንችለው? ይህንን መንገድ ሳልሳሳት እንድጓዝ የሚረዳኝ ብርሃን የተኛው ነው? ምን ዓይነት ትክክለኛውን “አቅጣጫ መጠቆሚያ” መሳርያ መጠቀም አለብኝ? በሕይወት መንገዴ ላይ ሳልሳሳት እንድጓዝ የሚረዳኝ እግዚኣብሔር ራሱ የሰጠኝ ስጦታ የቱ ነው? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ያሉት ቅዱስነታቸው የሕይወት መንገዳችንን ሳንሳሳት ለመጓዝ የሚረዳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል 5 ላይ በተጠቀሰው የተራራ ላይ ስብከት ውስጥ የተጠቀሱት የዋሕነት፣ በመንፈስ ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ፍትህ፣ ምሕረት፣ የልብ ንጽህና እነዚህ በሕይወት መንገዳችን ላይ ሳንሳሳት መጓዝ እንችል ዘንድ የሚመሩን አብረውን የሚጓዙ መንገዳችንን የሚያበሩ የሕይወት ብርሃን ናቸው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ ደግሞ አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታችንን ያመልክታል ብለዋል።

በዚህ አሁን ባለንበት የመካነ መቃብር ስፍራ ሦስት የሕይወት ገጽታዎችን እናገኛለን፣ ማሕደረ ትውስታ (በሞት ከእኛ የተለዩ ወዳጆቻችን እናስታውሳለን)፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ (አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድር እንደ ሚጠብቀን በማሰብ) በቅዤት ሳይሆን በእመንት ተስፋችንን እናለመልማለን፣ የሕይወት መንገዳችንን ሳንሳሳት እንድንጓዝ የሚረዱንን አሁን ሲነበብ በነበረው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱትን ሕይወታችን በብርሃን ተሞልቶ ያለ ስህተት እንድንጓዝ የሚረዱንን ኢየሱስ በተራራ ላይ የሰበከውን እና ወደ ብጽሕና ሕይወት የሚመሩንን መሳርያዎች እንመለከታለን ብለዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 November 2018, 14:53