ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ሐሜት ገዳይ ነው፣ እግዚኣብሔር ግን እውነት ነው!”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎቢኚዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መረሀ ግብር መሰረት በዛሬው ዕለት ማለትም በሕዳር 05/2011 ዓ.ም ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከሳምንታት በፊት በዐስርቱ ትእዛዛት ዙርያ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት (በሕዳር 05/2011 ዓ.ም) ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር” በሚለው በስምንተኛው ትዕዛዝ ዙሪያ ላይ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “ሐሜት ገዳይ ነው፣ እግዚኣብሔር ግን እውነት ነው!”  ክርስቲያኖች እግዚኣብሔርን  በእውነት እና በፍቅር ሊመሰክሩት ይገባል” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ- ቫቲካን

እኛ በአሁኑ ወቅት በእውነት እና በውሸት መካከል በመዋለል እንደ ምንኖር በአስተምህሮዋቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ነገር ግን ትክክለኛው የክርስቲያን ተልዕኮ እና ተግባር እግዚኣብሔር አብ እውነተኛ አምላክ መሆኑን መመስከር እንደ ሆነ ገልጸው እኛም የተጠራነው በእውነት እና ለእውነት ብቻ እንድንኖር መሆኑን ተገንዝበን ሕይወታችንን በዚህ መልኩ ማስኬድ ይኖርብናል ብለዋል።

በዕለቱ የተነበበው የእግዚኣብሔር ቃል

“እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።  መልካሙን ራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ 5፡14-16)።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዕለት ማለትም በሕዳር 05/2011 ዓ.ም ከዐስርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱ በሆነው “በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር” በሚለው በሰምንተኛው ትእዛዝ ላይ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል፣ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት የጠቅላላ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዐስርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ በሆነው በባልንጀርህ ላይ በሐሰት አትመስክር” በሚለው በስምንተኛው ትዕዛዝ ላይ እናደርጋልን። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምሕርተ ክርስቶስ ስምንተኛው ትዕዛዝ ከሌሎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት እውነትን እንዳናዛባ ይመክረናል” (2464) ይለናል ። እውነተኛ ባልሆነ ግንኙነት ውስጥ መኖር በጣም አላስፈላጊ የሆነ ነገር ነው፣ ምክንያቱም ግንኙነቱ እውነተኛ እንዲሆን ስለማያደርግ ፍቅር እንዳይኖር ያደርጋል። ውሸት ባለበት ቦታ ላይ ፍቅር የለም፣ በፍጹም ሊኖር አይችልም። በሰዎች መካከል ስላለው ግንኙነት በምናወራበት ወቅት በቃላት የሚደርጉ ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን የምንመለከተው ነገር ግን አካላዊ መገለጫዎችን፣ አመላካከቶችን፣ ስሜትን  እና በመጨረሻም ዝም ብሎ ቁጭ ማለትን ያካተተ እንደ ሆነ እንገነዘባለን። አንድ ሰው በሁሉም ነገር እና በሚሠራው ነገር ሁሉ ይናገራል። እኛ ሁላችን ሁል ጊዜ በግንኙነት ላይ ነን። እኛ ሁላችን የምንኖረው ግንኙነት በመመስረት እና ቀጣይነት ባለው መልኩ በእውነት እና በሐሰት መካከል በመዋለል እንኖራለን።

ነገር ግን እውነትን መናገር ማለት ምን ማለት ነው? ሐቀኛ መሆን ማለት ነው ወይ? ወይም ትክክለኛ መሆን ማለት ነው? በተጨባጭ ግን ይህ በቂ አይደለም፣ ምክንያቱም አንድ ሰው ያለ ምንም ስህተት ሊኖር አይችልም፣ ወይንም ደግሞ አንድ ሰው ሁሉንም ነገር በዝርዝር ማስቀመጥ ይችል ይሆናል ነገር ግን ስለነገሩ ግንዛቤ ላይኖረው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ "እኔ የተሰማኝን ነገር ነው የነገርኩዋችሁ!” በማለት ራሳችንን እውነተኛ አድርገን እናቀርባለን። አዎ! ግን የአንተን አመለካከት አጽኖት በመስጠት ገልጸሃል። ወይም ደግሞ እኔ እውነት የሆነውን ነገር ብቻ ነው የተናገርኩት” ልትል ትችል ይሆናል። ምናልባት አንዳንድ የግል ወይም ምስጢራዊ እውነቶችን አሳይተህ ይሆናል። አግባብ የሌለው ወይም ጣፋጭነት የጎደለው ግንኙነት ውስጣዊ ስሜትን ምን ያህል ይጎዳል! በእርግጥ ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ እንደ ሚለን ሐሜት ገዳይ የሆነ ነገር ነው። ሐሜት እና ሐሜተኛ ገዳይ የሆኑ ነገሮች ናቸው፣ ሌሎችን ይገድላል፣ ምክንያቱም ምላስ እንደ ስይፍ ገዳይ ናትና” ይለናል። ጥንቃቄ አድርጉ! አንድ ሐሜተኛ የሆነ ሰው ወይም ሐሜተኛ የሆነች ሴት እንደ አንድ አሸባሪ አድርገን መቁጠር እንችላለን፣ ምክንያቱም በምላሳቸው ቦንብ ጥለው እነርሱ ተረጋግተው ይሄዳሉ፣ ነገር ግን በምላሳቸው አማካይነት የጣሉት ቦንብ የሌላ ሰውን ስም እና ዝና ያበላሻል። ሐሜት ገዳይ መሆኑን በፍጹም መርሳት የለባችሁም።

ታዲያ እውነት ምንድነው? ጲላጦስ በኢየሱስ ፊት ቆሞ ለኢየሱስ ያቀረበው ጥያቄ በተመሳሳይ መልኩ ይህንን ስምንተኛውን ትዕዛዝ እንደ ተገነዘበው ያመለክታል። በእርግጥ "በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር" የሚለው ትዕዛዝ የፍርድ ቋንቋን የሚያመልክት ነው። አራቱም ወንጌሎች በኢየሱስ ስቃይ፣ ሞትና ትንሳኤ ዘገባ ላይ ያጠነጥናሉ፣ እናም ይህ የፍርድ ታሪክ የዓረፍተ ነገሩ ፍፃሜ እና ያልተለመዱ ውጤቶችን ያመላክታሉ።

“ጲላጦስም። እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ። እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው።እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” (ማቴ 18፡37) በማለት ይመልስለታል። ይህም ኢየሱስ በሞቱ እና በትንሳኤው የገለጠው “ምስክርነት” ነው። ወንጌላዊው ማርቆስ  “በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ” (ማር. 15፡39) በማለት እንደ ተናገረ ይተርክልናል። አዎን!  ምክንያቱም ይህ መልስ ተመጣጣኝ እና ተገቢ የነበረ መልስ ነው፣ በዚሁ አሟሟት ኢየሱስ አብን   ይገልጽልናል ፣ ርህሩህና ታማኝ ፍቅሩን ገልጾልናል።

እውነት የኢየሱስ አኗኗር እና አሟሟት ከአብ ጋር ያለው ግንኙነት ፍሬ ማለት ነው። ይህ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን መጠን እሱም ከሞት የተነሳው የእውነት መንፈስ የሆነው መንፈስ ቅዱስን በመላክ ጸጋውን ይሰጠናል፣ ይህም በልባችን ውስጥ የሚገኝ እግዚአብሔር አባታችን ነው።

ከቀላል የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች አንስቶ እስከ በጣም አስፈሪ ምርጫዎች ድረስ ሰዎች በእያንዳንዱ ተግባራቸው ይሄንን እውነት ያረጋግጣሉ ወይንም ይክዳሉ። ይህ ደግሞ ሁልጊዜ አንድ ዓይነት የሆነ አመክንዮ ነው፣ ሁሌም ቢሆን ወላጆቻችን እና አያቶቻችን ልጃች ውሸት እንዳይናገሩ ያስተምራሉ።

የእኛ ስራዎች የሚረጋገጡት በየተኛው እውነት ነው? ክርስቲያናዊ በሆኑ ተግባሮች ነው፣ በቃላቶቻችን ነው፣ ወይስ በምርጫዎቻችን ነው? ብለን እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ። ሁላችንም ራሳችንን -እኔ የእውነት መስካሪ ነኝ ወይም ደግሞ እኔ የተበላሸ ውሸታም የሆንኩኝ ሰው ነኝ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። እኛ ክርስቲያኖች ከሌሎች የተለየን ሰዎች አይደለንም። እኛ ግን መልካም እና የማያሳፍረን፣ ወንድሞቻችንን ማገልገል እንችል ዘንድ በልባችን ውስጥ ፍቅሩን የሚያኖርልን የሰማያዊ አባታችን ልጆች ነን። ይህ እውነት በንግግሮች ሊገለጽ የማይችል መሆኑ የተረጋገጠ ነው፣ ነገር ግን በአኗኗር እና በሕይወት መንገድ እንዲሁም በሁሉም ድርጊቶች ሊገለጽ የሚገባው እውነት ነው። ይህ ሰው በጣም እውነተኛ የሆነ ሰው መሆኑ፣ ያቺ ሴት በጣም እውነተኛ መሆን አለመሆናቸው በደንብ ቁልጭ ብሎ ይታያል። አፋቸውንም ከፍተው ባይናገሩ እንኳን ይታወቃል። ምክንያቱ እውነተኛ መሆናቸውን በባሕሪያቸው ያሳያሉና ነው። እውነትን ይናገራሉ፣ በእውነት ሥራቸውን ይሰራሉ። ይህም ለእኛ መልካም ምሳሌ የሚሆን ነው።

እውነት የእግዚኣብሔር አስደናቂ የሆነ ግልጸት ነው፡ ይህም ማለት ከአባታዊ ምልክታው ጥልቅ የሆነ ፍቅር ይገለጻል ማለት ነው። ይህ እውነት ከሰብዓዊ ፍጡር አስተሳሰብ ጋር ይዛመዳል ነገር ግን ሰብዓዊ አስተሳሰብን ያሸንፋል፣ ምክንያቱም ይህ ስጦታ በምድር ላይ የወረደው በምድር ክርስቶስ የእኛን ስጋ በመልበሱ እና ክርስቶስ ለእኛ ብሎ በመሰቀሉ የተነሳ በመሰቀሉ የተሰጠን ጸጋ በመሆኑ ምክንያት ነው። እሱም የእርሱ የሆኑትን በማየት እና በመለየት የእርሱን አመለካከት እንድንላበስ ይረዳናል።

በሐሰት አለመመስከር ማለት ደግሞ እንደ እግዚኣብሔር ልጅ ሆኖ መኖር፣ በፍጹም ክህደትን ማስወገድ እና በፍጹም ሐሰት አለመናገር ማለት ነው፣ እንደ እግዚኣብሔር ልጅ ሆኖ በመኖር በውስጣችን እውነት እንዲገለጽ በማድረግ፣ እግዚኣብሔር አባት በመሆኑ የተነሳ በእርሱ መተማመን ማለት ነው። እኔ በእግዚኣብሔር እተማመናለሁ ማለት በራሱ በጣም ትልቅ የሆነ እውነታ ነው። እግዚኣብሔር አባታችን መሆኑን በምናምንበት ወቅት፣ በእግዚኣብሔር መታመናችን በራሱ እርሱ እንደ ሚወደን በማሰብ እውነተኞች እንጂ ሐሰተኞች እንዳንሆን የሚያደርግ ጸጋ እንድናገኝ ያደርገናል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ በቅ. ጴጥሮስ አደባባይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት
14 November 2018, 17:10