ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “የሕግ ዋነኛው ተግባር ሰው ልቡን ለእግዚአብሔር እንዲከፍት ማድረግ ነው”

ሁሉም ትእዛዛት የሕይወትን ገደብ የሚያመለክቱ፣ የሰው ልጅ ራሱን እና ባልንጀራውን እንዳይጎዳ ለማድረግ እና በዚህም የተነሳ ከእግዚኣብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳያበላሽ ለመርዳት ታስቦ የተሰጡ ትእዛዛት መሆናቸውን ማስታወስ ይገባል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ ዕለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎቢኚዎች ሳምንታዊ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መረሀ ግብር መሰረት በዛሬው ዕለት ማለትም በሕዳር 12/2011 ዓ.ም ያደረጉት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከሳምንታት በፊት በዐስርቱ ትእዛዛት ዙርያ ጀምረውት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት (በሕዳር 12/2011 ዓ.ም) ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት፣ ሎሌውንም አገልጋዩንም፣ በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” (ኦ.ዘጸዐት 20፡17) በሚለው በዐስረኛው ትእዛዝ ዙሪያ ላይ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “የሕግ ዋነኛው ተግባር ሰው ልቡን ለእግዚአብሔር እንዲከፍት ማድረግ ነው” ማለታቸውን ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዛሬው ዕለት ማለትም በሕዳር 12/2011 ዓ.ም ከዐስርቱ ትእዛዛት መካከል አንዱ በሆነው የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም አገልጋዩን፣ በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” (ኦ.ዘጸሐት 20፡17) በሚለው ዐስረኛው ትእዛዝ ላይ ተመርኩዘው ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል፣ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

ከዚህ ቀደም በዐስሩ ትእዛዛት ዙሪያ ላይ ስናደርገው የነበረው አስተምህሮ ዛሬ የመጨረሻውን ትእዛዝ በመመልከት እናጠናቅቃለን። እነዚህ የዐስርቱ ትእዛዛት የመጨረሻ ቃላት ብቻ አይደሉም፣ ነገር ግን ከዚህ እጅግ የላቁ ናቸው፣ እነሱ በእስርቱ ትዕዛዛት ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛት ሁሉ በመነካካት በእነዚህ በዐስርቱ ትእዛዛት አማካይነት ወደ ፊት በመጓዝ ልብን በመንካት ወደ ፍጻሜ የሚያደርስ የመጨረሻው ትእዛዝ ጭምር ነው። እንዲያውም ቀረብ ብለን በደንብ ስንመረምረው ለየት ያለ አዲስ ይዘት አናገኝበትም፣ ለምሳሌ የባልንጀራህን ሚስት አትመኝ [. . .]፣ የባልንጀርህ የሆኑ ነገሮችን አትመኝ” የሚሉትን ስንመለከት አታመንዝር እና አትስረቅ”  ከሚሉ ትእዛዛት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ትእዛዝ ሲሆን ታዲያ የእዚህ የዐስረኛው ትእዛዝ ጥቅም ምንድነው? የሁሉም ትእዛዛት መደምደሚያ ነው? ወይስ ከዚህ ለየት ያለ ትርጉም ይኖረዋል? ብለን ልንጠይቅ እንችል ይሆናል።

ሁሉም ትእዛዛት የሕይወትን ገደብ የሚያመለክቱ፣ የሰው ልጅ ራሱን እና ባልንጀራውን እንዳይጎዳ ለማድረግ እና በዚህም የተነሳ ከእግዚኣብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳያበላሽ ለመርዳት ታስቦ የተሰጡ ትእዛዛት መሆናቸውን ማስታወስ ይገባል። ከዚህ ባሻገር የምንሄድ ከሆነ በቅድሚያ ራሳችንን እንጎዳለን፣ ከዚያም በመቀጠል ከእግዚኣብሔር እና ከባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እናበላሻለን። ትእዛዛቶቹ ይህንን እንዳናደርግ ጥቆማ ያደርጉልናል። በዚህ የመጨረሻ ትእዛዝ አማካይነት እውነታው ሁሉ ጎላ ብሎ በመውጣት ሁሉም መጥፎ ነገሮች የሚመነጩት እና የሁሉም መጥፎ ነገሮች ሥር መሰረታቸው ከውስጣችን የሚወጣ ክፉ የሆነ ምኞት እንደ ሆነ ጎላ አድርጎ ያሳየናል። ሁሉም ኃጢያቶች የሚፈጸሙት ከውስጣችን በሚመነጩ ከክፉ ምኞቶች የተነሳ ነው። ሁሉም ኃጢያት የሚፈጸመው በዚሁ ምክንያት ነው። ክፉ ምኞት ልብ እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል፣ ከዚያም የክፉ ምኞት ሞገድ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ከዚያም በመቀጠል በደል በመፈጸም ይጠናቀቃል ማለት ነው። ነገር ግን ይህ በደል መደበኛ የሆነ  ህጋዊ መተላለፍ አይደለም: ነገር ግን ራስን እና ባልንጀሮቻችንን የሚያቆስል በደል ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ ይህንን በተመለከተ እንዲህ ይለናል ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥  ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤  ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል” (ማር. 7፡21-23) ።

ስለዚህ በእነዚህ በዐስርቱ ትእዛዛት ውስጥ የተደረገው ጉዞ በሙሉ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ የሰዎችን ልብ የማይነካ ከሆነ ምንም ዓይነት ጥቅም እንደ ሌለው እንረዳለን። እነዚህ ሁሉ መጥፎ ነገሮች የሚመጡት ከየት ነው? ዐሰርቱ ትእዛዛት ይህንን በተመለከተ ግልጽ እና ጥልቅ በሆነ መንገድ በዚሁ መልኩ ይገልጻል፣  የመጨረሻው ዐስረኛው ትእዛዝ ልባችን በዚህ መንገድ በመጓዝ ነጻ እንዲሆን ይጠይቀናል፣ ዐስረኛውን ትእዛዝ ተከትለን ልባችንን ከክፉ ምኞቶች ነጻ የማናደርግ ከሆንን ግን ሌሎቹ ማለትም የቀሩት ዘጠኙ ትእዛዛት በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ጥቅም የላቸውም ማለት ነው። ልባችንን ከነዚህ ሁሉ ክፉ እና አስቀያሚ ከሆኑ ነገሮች ነጻ ማድረግ ደግሞ በጣም ፈተኝ የሆነ ተግዳሮት ነው። በዚህ ረገድ ልባችንን ነጻ የማናደርግ ከሆንን ግን፣ የእግዚአብሔር ህግጋት ሕይወት ሰጭ እና የሕልውናችን መገለጫ ውበት ከመሆን ይልቅ በባርነት ሕይወት ውስጥ ገብተን፣ የልጅነት መብታችንን ተነጥቀን እንድንኖር ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ ከመጠን በላይ የቆሸሸ (የረከሰ) ጭንብል ውስጥ አስቀያሚ እና ያልተለመዱ ነገሮች ተደብቀው ይገኛሉ።

በተቃራኒው በእዚህ “አተመኝ” በሚለው ዐስረኛው ትእዛዝ ታግዘን ከዚህ ምኞት ነጻ መውጣት ይኖርብናል፣ ምክንያቱም ይህ ትእዛዝ ደካማ መሆናችንን ያሳየናል፣ ቅዱስ ወደ ሆአን መገለጥ ይመራናል። ነገር ግን እኔን ብዙን ጊዜ የሚፈታተኑኝ   መጥፎ ምኞቶች የተኞቹ ናቸው? ብለን   እያንዳንዳችን እራሳችንን   መጠየቅ እንችላለን። ቅናት፣ ስግብግብነት፣ ሐሜት እነዚህ ነገሮች ሁሉ በውስጤ አሉ ወይ? እያንዳንዳችን ይህንን ጥያቄ አንስተን ለራሳችን መልስ ብንሰጥ መልካም ነው። የሰው ልጆች ሁሉ ይህ ብሩክ የሆነ ትህትና ያስፈልጋቸዋል፣ በዚህም አግባብ ከእነዚህ ምኞቶች እርሱ በራሱ ኃይል ብቻ ነጻ መውጣት እንደ ማይችል በመገንዘብ እግዚኣብሔር ነጻ ያወጣው ዘንድ ወደ እርሱ እንዲጮኽ ይረዳዋል። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን “አተመኝ”  የሚለውን ትእዛዝ በተመለከተ በሚገባ ግልጽ አድርጎ አስቀምጦታል። (ሮሜ 7፡7-24)

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ሳይታከልበት   ራሳችንን በራሳችን ጥረት ለማስተካከል መሞከር ምንም ፋይዳ የለውም። ትይንት በሚመስሉ ስራዎቻችን አማካይነት ልባችንን ለማንጻት ማሰቡ ከንቱ ነው -ይህ የማይቻል ነገር ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመመስረት በእውነት እና በነፃነት መራመድ ይኖርብናል፣ በዚህ መንገድ ብቻ ነው ጥረታችን ፍሬያማ ሊሆን የሚችለው፣ ምክንያቱም እኛን ወደ ፊት ሊመራን የሚችል መንፈስ ቅዱስ ስላለ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሕግጋት ተግባር የሰው ልጅን ማታለል አይደለም፣ ይህም ሲባል እንዲሁ በግርድፉ ቃል በቃል በመታዘዝ ሰው ሰራሽ እና ሊደረሰበት ወደ ማይችል ደህንነት የሚመራ ተደርጎ መቆጠር የለበትም። የህግ ዋነኛው ተግባር ሰውን ወደ እውነት ማለትም ወደ ደህንነቱ ማምጣት ማለት ነው፣ ይህም በትህትና፣ በግልጽነት እና የግለሰብ ልብን በመክፍት የሰው ልጅ ወደ እግዚአብሔር ምሕረት እንዲቀርብ በማድረግ እንዲለወጥ እና እንዲታደስ ማድረግ ነው። እኛ ልባችንን ግልጥልጥ አድርገን ብንሰጠው ልባችንን የማደስ ብቃት ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡ ይህ ብቸኛው አማራጭ ነው፣ እርሱ ሁሉንም ነገር ያደርጋል፣ ነገር ግን እኛ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል።

የዐስረኛው እና የመጨረሻው ትእዛዝ መልእክቶች ሁላችንም ራሳችንን መመልከት እንዳለብን ያስተምረናል፣ በልባችን ውስጥ ያለውን ችግር እንድንጋፈጥ፣ ራስ ወዳድነትን እንድናስወግድ እና   በመንፈስ ድሆች እንድንሆን፣ በአብ ፊት እንድንኖር፣ በልጁ እንድንዋጅ እና መንፈስ ቅዱስ እንድያስተምረን እንድንፈቅድለት ይረዳናል። መንፈስ ቅዱስ መሪያችን እና አስተማሪያችን ነው፣ እንዲረዳን እንጠይቀው። እኛ ለማኞች ነን፣ ስለሆነም   ይህን ጸጋ እንዲሰጠን እንጠይቀው።

“በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሁሉ ብጹዕን ናቸው መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና” (ማቴ 5፡3)። አዎን! ራሳቸውን በራሳቸው ኃይል ብቻ ከድክመታቸው ለመላቀቅ እንደ ሚችሉ አድርገው በመቁጠር ራሳቸውን በማታለል ላይ የነበሩ ሰዎች ይህንን አስተሳሰባቸውን ትተው ሊፈውሰው የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን አውቀው ወደ እግዚኣብሔር የሚጠጉ ሰዎች ሁሉ የተባረኩ ናቸው። ልባችንን ሊፈውስ የሚችለው የእግዚኣብሔር ምሕረት ብቻ ነው። የራሳቸውን ክፉ ምኞት ጠንቅቀው የተረዱ ሰዎች፣ በተጸጸተ እና በትሕትና በተሞላ ልብ እንደ አንድ ቅዱስ ሰው ሳይሆን እንደ አንድ ኃጢያተኛ ሰው በእግዚኣብሔር ፊት ለመቆም የሚከብዳቸው፣ ራሳቸውን እንደ ጻድቅ ሳይሆን እንደ ኃጢያተኛ የሚቆጥሩ ሰዎች ሁሉ የተባረኩ ናቸው። እኔ ኃጢያተኛ የሆንኩ ሰው ነኝና እባክህን ጌታ ሆይ ከእኔ ራቅ” በማለት  ቅዱስ ጴጥሮስ ለኢየሱስ የተናገረው ቃል በጣም ውብ የሆነ ቃል ነው።  “ጌታ ሆይ ኃጢያተኛ ነኝና እባክህን ከእኔ ራቅ” የሚለው ጸሎት በጣም ውብ የሆነ ጸሎት ነው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሕዳር 12/2011 ዓ.ም
21 November 2018, 17:18