ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የወጣቶች ሕብረት የሃያላንን ጉልበት ሳይቀር ያሸንፋል አሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን 34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የቪዲዮ ምስል መልዕክታቸው ወጣቶች ሃይላቸውን አጠናክረው በሕብረት ሲቆሙ ማንኛውንም ጠንካራ የተባለ ሃይል ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ገለጹ። ነገር ግን ይህን ለማድረግ ከግለኝነት መንፈስ ወጥተው ወደ ሌሎች ዘንድ በመሄድ የሚጠበቅባቸውን የአገልግሎት ተልዕኮን በተግባር መግለጽ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በመካከላኛ የላቲን አሜሪካ አገር በሆነችው ፓናማ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶችን በዓል ለማክበር ከተለያዩ ሐይማኖቶች የተወጣጡ፣ እምነት የሌላቸውም ቢሆን በዓሉ ወደ ሚከበርበት አገር ወደ ፓናማ ለመጓዝ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው  ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ወደ ፓናማ የሚደርሱት ጥር 15 ቀን 2011 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል።

የቪዲዮ ምስል መልዕክት ወጣቶች በሚረዱት ቋንቋ ተዘጋጅቷል፣

የአውሮጳውያኑን የዘመን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮ መሠረት ብጽዕት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የተወሰደችበት ዕለት በታሰበበት በህዳር 12 ቀን 2011 ዓ. ም. ቅዱስነታቸው ያስተላለፉት መልዕክት ከዚህ በፊት በፓላንድ ክራኮቪያ ከተማ ተከብሮ በነበረው የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል ቀርቦ ለነበረው ማርያማዊ መልዕክት ማጠቃለያ መሆኑ ታውቋል። በቅድስት መንበር የቤተሰብና የሕይወት ተንከባካቢ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት፣ ለዓለም አቀፍ ወጣቶች በዓል ዝግጅት እንዲሆን በማለት፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን በቁጥር በርካታ የሆኑ ወጣቶች ፍላጎት ላማሟላት፣ ጥያቄያቸውንም ለመመለስ ተብሎ በቅርቡ በተካሄደው በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እንደተደረገ ሁሉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣቶች ያስተላለፉት የዘንድሮ መልዕክት ወጣቶች በሚመርጡት መንገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በቪዲዮ ምስል እንዲሰራጭ መደረጉ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉት የቪዲዮ ምስል መልዕክት ዘንድሮ በፓናማ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ በዓል እንደ መሪ ርዕሥ የተመረጠው፣ ማርያም ለእግዚአብሔር ጥሪ “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ፣ አንተ እንዳልህ ይሁንልኝ” ያለችውንና በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 1.38 ላይ የተጻፈውን ጥቅስ የሚያብራራ እንደሆነ ታውቋል።

ለእግዚአብሔርና ለባለንጀራ የሚቀርብ አገልግሎት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማርያም ለእግዚአብሔር የሰጠችው አዎንታዊ መልስ ቸርነትና ድፍረት የተሞላበት እንደሆነ አስረድተው የጥሪ ታላቅ ምስጢር የሚገለጠው ለራስ ብቻ የሚለውን አስተሳሰብ አሸንፎ ሌሎችን ማሰብ ስንጀምር ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ሕይወታችን ትርጉም የሚያገኘው እግዚአብሔርንና ሌሎችን ስናገለግል እንደሆነ አስረድተዋል። በርካታ ወጣቶች ትምህርታቸውን ሲጨርሱ የተቸግሩትን ለመርዳት ትልቅ ፍላጎት እንደሚያድርባቸው ገልጸው በእርግጥም ወጣቶች በሕብረት ሆነው የሚያቀርቡት መልካም አገልግሎት በምድራችን የሃያላንን ጉልበት አሸንፎ ዓለምን ሊቀይር እንደሚችል አስረድተዋል።

አዎንታዊ መልስ ለመስጠት ድፍረት ይስፈልጋል፣

ሌሎችን ማገልገል ማለት ለአገልግሎት መዘጋጀት ብቻ  ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር፣ ቅድስት ድንግል ማርያምም በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኩል የደረሳትን የእግዚአብሔር ጥሪ በማዳመጥ መልስ እንደሰጠች ሁሉ ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ልባዊ ወዳጅነት በመመራት ማንነታችንንና ጥሪያችንን በመገንዘብ፣ ይህን ጥሪያችንን በተለያዩ መንገዶች፣ ለምሳሌ በትዳር ሕይወት፣ በምንኩስናና በክህነት ሕይወት መግለጽ እንደሚቻል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። ከእነዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ሌሎች በርካታ መንገዶች እንዳሉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን ከተረዳን አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ድፍረት እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

ማርያም በደስታ የተሞላች ሴት፣

እግዚአብሔር አንድ እቅድ ያዘጋጀላት ቅድስት ድንግል ማርያም በእርሱ ፊት ቸር ሆና እንደተገኘች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ለእኛም ያዘጋጀውን እቅድ ለመቀበል ያለንን ምኞት ሳንሰውር፣ ይህን እቅድ ለመቀበል ያለን ፍላጎታችን ይበልጥ እንዲጎላ ማድረግ፣ ፍሬን እንዲያፈራ፣ ልባችንም በደስታ የሚሞላ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ ለእግዚአብሔር እርግጠኛ የሆነ መልስ መስጠት ማለት  ራሳችንን በደስታ ሞልተን ሌሎችም በደስታ እንዲሞሉ የምናድርግበት የመጀመሪያ ደርጃ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዝግጅት ወቅት፣

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ወጣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ዘወትር እንዲገናኙ ብርታትን ሰጥተው፣ ለእግዚአብሔር ድምጽ ወይም ጥሪ እድልን እንዲሰጡና ከእግዚአብሔር በሚቀበሉት ጥሪ ሕይወታቸው ተለውጦ በደስታ እንዲሞሉ ያስፈልጋል ብለዋል። ዘንድሮ ለ34ኛ ጊዜ የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ክብረ በዓል ለማክበር ወደ ፓናማ ጉዞ በሚጀመርበት ባሁኑ ወቅት ወጣቶች በቅድስት ድንግል ማርያም እርዳታ በመታገዝ፣ ለበዓሉ በሚደረጉ አንዳንድ ቅድመ ዝግጅቶች በንቃት በመሳተፍና እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር በሚሰጡት መልስ ደፋሮችና ደስተኞች እንዲሆኑ አሳስበዋል።                

22 November 2018, 16:33