ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሊባኖስን ብጹዓን ጳጳሳት አመሰገኑ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙትን በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሊባኖስ አንጾኪያ ሜሮናዊያን ጳጳሳትን ተቀብለው ማነጋገራቸው ታውቋል። ከሊባኖስ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር የሊባኖስ ዳያስፖራ ማሕበረሰብም መገኘውታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው ብጹዓን ጳጳሳትን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት ጳጳሳቱ በሊባኖስ ለሚያበረክቷቸው ፍሬያማ ሐዋርያዊና ማሕበራዊ አገልግሎቶች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ወንድማማቾች በሆኑ ክርስቲያኖችና ሱኒት ሺኣ ሙስሊሞች መካከል ስላለው መልካም ግንኙነቶችም አመስግነዋቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ባሁኑ ጊዜ ሊባኖስ ከመካከለኛው የምሥራቅ አገሮች የተሰደዱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች ሰብዓዊ እርዳታን በማቅረብ ላይ መገኘቷን በማስታወስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቀለሜንጦስ ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተቀብለው ካነጋገሯቸው በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአንጾኪያ ማሮናዊያን ስርዓተ አምልኮን የሚከተሉ 35 የሊባኖስ ብጹዓን ጳጳሳት በተጨማሪ በሊባኖስ የማሮናዊያን ፋውንዴሽን አባላት፣ የሊባኖስ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናትና በሊባኖስ እርዳታን በማከፋፈል አገልግሎት ላይ የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላትም መገኘታቸው ታውቋል።

ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር የነበሩ ምዕመናን “የሊባኖስን ሕዝብ በሚገባ እናውቀዋለን”።

በሊባኖስ የአንጾኪያ ማሮናዊያን ስርዓተ አምልኮን የምትከተል የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ቤካራ ቡትሮስ ራይ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ቅዱስነታቸው በቀለሜንጦስ ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለተገኙት ከ50 በላይ ለሚሆኑ የማሮናዊያን ፋውንዴሽን ምዕመን አባላት ባሰሙት ንግግር በሊባኖስ ስለምታበረክቱት የእርዳታ አገልግሎት በይበልጥ ማወቅ እንድንችል ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር መገኘታችሁ መልካም ሃሳብ እንደሆነ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ሊጎበኟቸው የሚመጡ የእንግዶች ቁጥር ወደ አርባ የሚጠጉ እንደሚሆን ቢነገራቸውም ነገር ግን በቀሌመንጦስ ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተገኙት ሊባኖሳዊያን ቁጥር ከእጥፍ በላይ እንደነበር ገልጸው ይህም እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው በድጋሚ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በክርስቲያኖችና በሙስሊም ወንድሞች መካከል ወገናዊነትን ላልተከተለ ግንኙነት ምስጋና አቅርበዋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሊባኖስ እየተከናወነ ስላለው በጎ ተግባር መላው የሊባኖስን ሕዝብ አመስግነው በተለይም በክርስቲያኖችና በሙስሊም ሺኣና ሱኒ ወንድሞች  መካከል ወገናዊነትን ላልተከተለ ጠናካራ ግንኙነት ምስጋንቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በሊባኖስ እርዳታን እያገኙ የሚገኙትን ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ስደተኞችን አስታውሰው፣ የሊባኖስ ሕዝብ ለእነዚህ ስደተኞች ስላሳየው ቸርነት፣ የእንግዳ ተቀባይነት ልብ ምስጋናቸውን አቅርበው በመጨረሻም እግዚአብሔር ሊባኖስን፣ የሊባኖስን ሕዝብ፣ በሊባኖስ የሚገኙ ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን እንዲባርክ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።                     

21 November 2018, 15:41