ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ክርስቲያኖች የእምነትን ነጻነት እንደሚነፈጉ ሞትም እንደሚደርስባቸው ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእግዚአብሔርን ፍቅር መመስከር፣ የደም ዋጋን ከሚያስከፍል ሰማዕትነት በተጨማሪ የሐይማኖት ነጻነት ተነፍገው በየዕለቱ ስቃይ ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች የምትሰጡትን እርዳታ አታቋርጡ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የዴሞክራሲን ስርዓት በሚከተሉ አገሮችም የሃይማኖት ነጻነት ገደኣብ መጣሉንና በክርስቲያኖች ላይም ስቃይ እየበረታ መምጣቱን በመልዕክታቸው ገልጸዋል። በቫቲካን በሚገኘው በቀለሜንጦስ ሐዋርያዊ ሕንጻ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ፣ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ድንጋጌን የሚመለከት የመማክርት ጉባኤ ማሕበር አባላትን ተቀብለው ባነጋገሩበት ጊዜ እንደገለጹት ስቃይ ለሚደርስባቸው በሙሉ እርዳታን ማቅረብ አታቋርጡ በማለት አሳስበዋል።

ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ለሚደረግ እርዳታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ ስብሰባ የሚቀመጡትን የዘንድሮን በሮም ላካሄዱት 130 ታላላቅ የሕግ አዋቂዎች ባሰሙት ንግግር፣ የሕግ ባለሞያዎቹ በቅድስት አገር በኢየሩሳሌም ለነዋሪው ሕዝብ ለሚያበረክቱት በርካታ መንፈሳዊ የቸርነት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለሕግ አዋቂዎች ባሰሙት ንግግር፣ ለስብሰባ የመጡባት ቅድስት መንበር ቤታቸው እንደሆነች ገልጸው ከጥንት ጀምሮ ለተቋቋመው ጳጳሳዊ ማሕበራቸው ቅድስት መንበር ከለላንና ጥበቃን እንደምታደርግ አረጋግጠውላቸዋል። ይህ ማበራቸው የመጨረሻ ስብሰባ ካደረገበት ከ 2005 ዓ. ም. ጀምሮ የማሕበርተኞቹ ቁጥር በዓለም ዙሪያ እያደገ መምጣቱንና በኢየሩሳሌም ለምትገኝ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የሚቀርብ የቁሳቁስ ድጋፍም መጨመሩን ገልጸዋል።            

በማህበሩ የሚመሩ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ለሁሉም ክፍት ናቸው፣

ማሕበሩ ከአገሩ የላቲን ስርዓተ አምልኮ ፓትሪያርክ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ኤድዊን ኦ ብራያንና ከብጹዕ አቡነ ፔር ባቲስታ ፒሳቤላ ጋር በመተባበር በኢየሩሳሌም በሚገኙት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ ተቋማት በርካታ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ ኢየሩሳሌምና አካባቢው አገሮች ለሚመጡ በርካታ ስደተኞች ቤተክርስቲያኒቱ ለምታቀርበው የእርዳታ አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በኢየሩሳሌም የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ባለማቋረጥ፣ እርዳታን በሚፈልጉ ተረጂዎች መካከልም ልዩነትን ሳያደርግ አገልግሎት እየሰጡ መቆየታቸው መልካም ምስክርነት መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

“አገልግሎታችሁን በተግባር እያሳያችሁ የክርስትናን እሴቶች ገሃድ ታደርጋላችሁ፣ በሐይማኖቶች መካከልም ፍሬያማ ውይይቶች እንዲካሄዱ በማድረግ መተጋገዝ እንዲኖር ታደርጋላችሁ፣ ይህን በማድረጋችሁ በአካባቢ አገሮች ሰላም እንዲወርድ በማለት ለምናደርገው ያማያቋርጥ ጸሎትና ጥረት ተስፋ እንዲኖር ታደርጋላችሁ” በማለት ማሕበርተኞቹ ለሚያበረክቱት አስተዋጽዖ በሙሉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

በቅድሚያ ማሕበሩ በመንፈሳዊነት ይደግ፣

የማህበሩ መንፈሳዊ እድገት በማሕበሩ ቀዳሚ ዓላማ በሆነው መንፈሳዊነት እንደሚወሰን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም ውስጥ በ30 አገሮች ውስጥ የሚገኙ የማሕበር አባላት በሙሉ ተግባራዊ የሚያደርጉትን እቅዶች በማውጣት መንፈሳዊ ስልጠናዎችን በመስጠትና ከስልጠናውም በኋላ በሚሰጡት ምስክርነት እንደሚታይ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

“በዓለም ዙሪያ በምትፈጽሙት ተልዕኮአችሁ ቁሳዊና ማህበራዊ አገልግሎትን ለማሻሻል ቃል እንደሚገቡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ራሳችሁን መመልከት የለባችሁም። የተጠራችሁበት ቀዳሚ ተልዕኮአችሁ በአካባቢያችሁ ለምታገኟቸው በሙሉ የወንጌልን ፍቅር እያሳያችሁ፣ እግዚአብሔር በፍቅር ያሳየውን መልካምነትና ጥበቃ መመስከር ነው” በማለት አስረድተዋል።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሚከተሉ አገሮች ውስጥ የሚታይ ሰማዕትነት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለማሕበርተኞቹ ባሰሙት ንግግር የጳጳሳት፣ የካሕናትና የዲያቆናት የአገልግሎት ድርሻ ማሕበርተኞች በሕብረት ጸሎት ስነ ስርዓት ተገኝተው ማገዝ፣ የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓትን ማሳረግና ትምህርተ ክርስቶስን ማዳረስ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አሳስበው ስቃይና መከራ የሚደርስባቸውን ክርስቲያኖች አስታውሰዋል።

“ብዙን ጊዜ ወደ ሌላው ዓለም በምንመለከትበት ጊዜ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመውን ስቃይና ስደት እናስታውሳለን፣ ስቃይና በደል የሚፈጸምባቸው፣ ሞትም የሚያጋጥማቸው ክርስቲያኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል። የደም መስዋዕትነት ከፍለው ሰማዕት የሚሆኑ ክርስቲያኖች ቁጥር እንዳለ ሆኖ የሃይማኖት ነጻነትን ተነፍገው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ቁጥር በዴሞክራቲክ አገሮችም እየጨመረ መምጣቱን ቤተክርስቲያንን በዕለታዊ ሕይወቷ እያጋጠማት ያለ ግልጽ ሰማዕትነት ነው”።

የስቃይተኞች ሁሉ እናት የሆነች ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቀለሜንጦስ ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ለተገኙትና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መካነ መቃብር ለሚመለከት የሕግ ባለሞያ ማሕበር አባላትን እንደገለጹት ማሕበሩ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው አሳስበው፣ የፍልስጤም እመቤታችን ማርያም በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ማሕበራቸው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ በቀለሜንጦስ ሐዋርያዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የቀረበውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መንፈሳዊ ምስል ባርከው ለማሕበርተኞቹ ካስረከቡ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም በክርስቲያናዊ ጉዞአቸው እንድታግዛቸው በማለት ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ቅድስት አገር ኢየሩሳሌምንና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን በሙሉ እንድትጠብቅ ጸሎታቸውን አቅርበው፣ የሐይማኖት ነጻነትን ለተነፈጉትና የሞት አደጋ ለተጋረጠባችው በሙሉ  ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅ ትሁናቸው በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
17 November 2018, 16:01