ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልባችን ከአመጽ ፈንታ ስለ ፍቅር ማሰብ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥቅምት ወር እንድናቀርብ ባሳሰቡን የጸሎት አስተንትኖአችን ልባችን ከጥላቻና ከአመጽ ይልቅ ስለ ፍቅር ማሰብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመላው ዓለም ምዕመናን በቪዲዮ ምስል በላኩት መልዕክታቸው ፍቅርን በተግባር በመኖር አመጽን፣ ጥላቻንና ጦርነትንም በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ሁላችንም ሰላምን እንሻለን፣ ነገር ግን ከማንም በላይ ሰላምን የሚፈልጉት ሰላምን በማጣት ስቃይና መከራ የሚደርስባቸው ናቸው ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የሰላምን ትርጉም ወይም ስለ ሰላም ቃላትን አሳምሮ መናገር ወይም መግለጽ ይቻላል፣ ነገር ግን በሰዎች ልብ ውስጥ ሰላም ከታጣ በዓለም ውስጥም ሊገኝ አይችልም ብለዋል። ስለዚህ አመጽ፣ ጥላቻ፣ ግጭትና ጦርነት ባለበት ሰላም እንዲወርድ ጸሎት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በሰዎች መካከል አመጽ ተወግዶ የርህራሔና የፍቅር ልብ ሲኖር ሰላም ለሁሉም ሰው ሊዳረስ ስለሚችል ልባችን ከአመጽ ፈንታ ስለ ፍቅር እንዲያስብ በሕብረት መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅርን ማሳየት የሚቻለው፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል፣ እርሱ ያደርግ እንደ ነበረው በዕለታዊ ኑሮአችን መካከል በምናከናውኗቸው ተግባራት አማካይነት፣ ከሰዎችም ጋር በምናደርጋቸው ዕለታዊ ግንኙነቶች እንደሆነ አስረድተዋል። በዓለማችን ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱት አመጾችና ጦርነቶች በሰላም ማጣት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በዓለማችን በሚከሰቱት ጦርነቶችና አመጾች ምክንያት ጥቃት ከሚድርስባቸው ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑ ሴቶችና ሕጻናት መሆናቸው ታውቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ2011 ዓ. ም. በሰኔ ወር ላይ ባወጣው ጠቅላላ ሪፖርት መሠረት፣ በ2010 ዓ. ም. ብቻ በዓለማችን ዙሪያ 21 ሺህ የሚሆኑ፣ መጠነ ሰፊ የሆኑ አመጾችና ጦርነቶች መቀስቀሳቸውን ገልጾ፣ በእነዚህ አመጾችና ጦርነቶች ጉዳት የደረሰባቸው፣ አመጹን ለማምለጥ ወይም ለመከላከል አቅም የሌላቸው ደሃ ማሕበረሰብ መሆናቸውን ገልጿል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞችን ጉዳይ አስተባባሪ ክፍል መረጃ መሠረት ከ1940 ዓ. ም. ጀምሮ በተካሄዱት ጦርነቶችና አመጾች ወይም ግጭቶች ምክንያት ለመሰደድ የተገደዱትና ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ የተደደረጉት ሰዎች ቁጥር 52 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ ለመስጠት በመንቀሳቀስ የሚገኙት የላቲን አሜሪካ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች በአገሮቻቸው የሚገኙትን ሃገረ ስብከቶችን በማስተባበር፣ በየአገሮቻቸው የሚነሱ ግጭቶችን ለማስቆም በጸሎት መተባበር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበው በሕዝባቸው መካከል ሊኖር የሚገባው የርህራሄ ልብ እንጂ አመጽ ወይም ጦርነት እንደማያስፈልግ አሳስበዋል። በላቲን  አሜሪካና በካሬቢያን አገሮች፣ ከሜክስኮ እስከ ሰሜን አሜሪካ ድንበሮች እንዲሁም በፓታጎኒያ የሚከሰቱትን ግጭቶችንና አመጾችን ያስታወሱት ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሌሎችንም አብያተ ክርስቲያናት በማስተባበር በአካባቢው በተለይም በሕጻናት ላይ የሚደርሱ የሞትና የመቁሰል አደጋዎች ተወግደው ከአመጽ ፈንታ ስለ ፍቅር የሚያስብ ልብ እንዲኖር፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ክብርን በመስጠት፣ ሰብዓዊ ክብራቸውም መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በአካባቢ አገሮች ሰላምን ለማስፈን የተደራጁ  የወጣቶች ቅዱስ ቁርባን ማሕበር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱሳውያን ማሕበር አባልና የዓለም የጸሎት ሕብረት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍሬደሪክ በበኩላቸው እንዳስረዱት በሕዝቦች መካከል ሊመጣ የሚችለው ሰላም የሚጀምረው እያንዳንዳችን በመካከላችን ከምናደርጋቸው ዕለታዊ ግንኙነቶች ነው ብለዋል። አባ ፍረደሪክ በማከልም የማናውቀውን፣ በባሕል የማንገናኘውን በቋንቋ የማንግባባውን ሰው መንገድ ላይ ስናገኝ ይህ ሰው እንግዳ ነው በማለት መቅረብ ይከብደን ይሆናል። ነገር ግን በሕዝቦች መካከል ፍቅር የሚጀምረው በማናውቀው ስፍራ፣ ከማናውቀው ወይም ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሌለን ሰው ጋር በምንጀምረው ትውውቅ፣ በቤተሰቦቻችን መካከል፣ በምንሰራበት አካባቢ ሁሉ ሊሆን እንደሚችል ገልጸው፣ በሰዎች መካከል ምንም ዓይነት ልዩነትን ሳያደርጉ፣ የሰው ልጅ ሊኖረው የሚገባውን ክብር በመስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።                                                           

07 November 2018, 15:22