ፈልግ

2018.11.07 Copertina Laudato si 2018.11.07 Copertina Laudato si 

የምድሪቱ እና የድሆች ጩሄት መልስን እንደሚሻ ተገለጸ።

የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ጩሄት መስማት ብቻ ሳይሆን መፍትሄን የያዘ ምላሽ መስጠት፣ ድህነትን መዋጋት፣ በዚህች ምድር ላይ ከእኛ በኋላ የሚመጡትንም በማሰብ ከጉዳት የተረፈች ዓለምን፣ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ያወረሰንን በእርካታ መኖር የሚቻልባትን ምድር ማውረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ትናንት ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ. ም. “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት በሮም በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት በተደረገው ሲምፖዚየም ላይ መቅረቡ ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ስምፖዚየሙን መካፈላቸው ታውቋል።

የሲምፖዚየሙ ርዕስም “የጋራ ቤታችን የሆነውን ምድራችንን እየተንከባከብን ስነ ምሕዳርን መለወጥ ያስፈልጋል” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ሲምፖዚየሙ ከዚህ በፊት ከህዳር 20 እስከ 22፣ 2010 ዓ. ም. ድረስ በኮስታ ሪካ፣ ሳን ሆሴ ላይ፣ በቫቲካን የዮሴፍ በነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽንና በሃገሪቱ የሚገኘው ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ሆነው ባዘጋጁት ስብሰባ ላይ የቀረቡት የውይይት ርዕሶችን መመልከቱ ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘውን መጽሐፍ ለስምፖዚየሙ ያቀረቡት ክቡር አባ ፈደሪኮ ሎምባዲ፣ በቫቲካን የዮሴፍ በነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንትና ሞንሲኞር ማሪዮ ኪሮስ በኮስታ ሪካ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት መሆናቸው ታውቋል።    

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ መልዕክት በቁጥር ወደ 700 የሚጠጉ ምሁራን፣ የትምህርት ቤት መምህራን፣ የፖለቲካ መሪዎችና አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ገዳማዊያንና ገዳማዊያት፣ ሳይንሳዊ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች፣ በሐዋሪያዊና ማሕበራዊ አገልግሎት ሥራ ላይ የተሰማሩት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች በጋራ ሆነው የተወያዩበትና ሃሳባቸውን ያቀረቡበት የሰፊ ጥናት ውጤት እንደሆነ ታውቋል።  

በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ካቀረቡት መካከል ረሃብንና ድህነትን ከዓለም ለማስወገድ በመስራት ላይ የሚገኘው የዓለም የግብርና ልማት ዓለም አቀፍ ፈንድ (IFAD) መገኘቱ ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ አረላኖ ንግግር ማድረጋቸው ሲታወቅ ብጹዕነታቸው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ውዳሴ ላንተ ይሁን የተሰኘው ሐዋርያዊ መልዕክት ለዓለም አቀፉ ፎረም ግልጽና እጅግ ጠቃሚ ሃሳቦችን ሊያበረክት ይችላል ብለው

ብጹዕነታቸው በማያያዝም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕት በብዙዎች ዘንድ ተደማጭነት ያለው፣ በዓለማችን ለሚታዩት መጠነ ሰፊ ችግሮች መፍትሄን በማፈላለግ መልሶችንም የሚያቀርብ እንደሆነ አስረድተዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት ይፋ ከሆነ ሦስት ዓመት እንደሆነውና በመካከለኛው የላቲን አሜርካ አገር በኮስታ ሪካ በሐዋሪያዊ መልዕክቱ ሰፊ ውይይት ከተካሄደ አንድ ዓመት ያለፈው እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ አረላኖ፣ ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን ግልጽና ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ስለገልጹት በርካታ ሕዝቦች እንዲሁም ምዕመናን በቀላሉ ሊገነዘቡት ችለዋል ብለው፣ ውዳሴ ላንተ ይሁን የሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያንና ለሰው ልጅ በሙሉ ያበረከቱት ትልቅ አገልግሎት እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ አረላኖ፣ ቅዱስነታቸው ለሰው ልጆች በሙሉ፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው መልዕክታቸው ያበረከቱትን አገልግሎት ሲዘረዝሩ፣ በቅድሚያ በዓለማችን የሚታዩትንና እየታዩ ያሉትን ችግሮች ለይተው በማውጣታቸው፣ ቀጥለውም በችግሩ ይበልጥ የሚጠቃውን ደሃውን ሕብረተሰብንና የምንኖርባትን ምድር በማስታወሳቸው፣ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ማራኪ ቃላትን በመደርደር ወይም ትላልቅ ስብሰባዎችን በማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን የባሕል፣ የሐይማኖት፣ የጾታና የእድሜ ልዩነት ሳይደረግ፣ የችግሩ ተጠቂ የሚሆን እያንዳንዱን የሕብረተሰብ ክፍል ዓለማችን ከተጋረጠችበት አደጋ የምትተርፍበትን መንገድ በመፈለግ የሚፈለግበትን አስተዋጽዖን እንዲያበረክት በማድረጉ ነው ብለዋል። ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፣ ጉዳት እያደረሱብን ያሉ ችግሮችን በግልጽ እያየ አይናችን የምንጨፍንበት፣ እየሰማን ጆሮ ዳባ ልበስ የምንልበት፣ እጆቻችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ሳይሆን መልስ እንድንሰጥበት ለእያንዳንዳቸን የቀረበ ጥሪ ነው ብለዋል። 

ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ አረላኖ የምድራችንና በምድራችን የሚኖሩ የድሆች ጩሄት በምንልበት ጊዜ በቅድሚያ መታሰብ ያለበት እነዚህን ጩሄቶች የሚያዳምጥ አካል ሊኖር ይገባል ብለው ምድራችንና የምድራችን ሕዝቦች ጩሄታቸውን አላቋረጡምና ልናዳምጣቸው ያስፈልጋል ብለዋል። እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩሄት ይሰማል፣ ነገር ግን እኛ ሰዎች ሌሎችን መስማት አቅቶናል፣ ምክንያቱም ለራስ ብቻ በማሰባችን፣ በስግብግብነታችን፣ የተነሳ በባሰ ችግር ውስጥ ሆነው እርዳታን የሚጠይቁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን ማድመጥ ተስኖናል ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ቺካ በማከልም የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ጩሄት መስማት ብቻ ሳይሆን መፍትሄን የያዘ ምላሽ መስጠት፣ ድህነትን መዋጋት፣ በዚህች ምድር ላይ ከእኛ በኋላ የሚመጡትንም በማሰብ ከጉዳት የተረፈች ዓለምን፣ እግዚአብሔር ሲፈጥረን ያወረሰንን በእርካታ መኖር የሚቻልባትን ምድር ማውረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።   

09 November 2018, 15:18