ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “አለማፍቀር የመግደል መጀመሪያ ደረጃ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ማለትም ረቡዕ የጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን፣ ነጋዲያንና ሀገር ጎብኝዎች ያቀረቡትን ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የዕለቱን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ወድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ እንደ ምን አረፈዳችሁ!

በዛሬ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አትግደል በሚለው በአምስተኛው ትዕዛዝ ላይ የጀመርኩትን አስተምህሮ መመልከት እፈልጋለሁ። በዚህ ትዕዛዝ በኩል የሰው ሕይወት በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ክቡር፣ ቅዱስና የማይጣስ መሆኑን ተመልክተናል። ማንም ሰው ቢሆን የራሱንም ሆነ የሌላውን ሰው ሕይወት ማሳነስ ወይም ዋጋ ቢስ አድርጎ መመልከት የለበትም። የሰው ልጅ በተጠራበት የሕይወት መንገድ፣ በሚገኝበት የኑሮ ሁኔታ በሙሉ የእግዚአብሔርን አምሳያነትና የማያልቅ ፍቅሩን ተሸክሞ ይገኛል።

ዛሬ በተነበበው የወንጌል ክፍል፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አትግደል” የሚለው አምስተኛው ትዕዛዝ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ያስገነዝበናል። በዚህ ማስገንዘቢያው በወንድም ላይ መቆጣት እንኳ ቢሆን እንደ ነፍስ መግደል ይቆጠራል ይላል።  “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፣ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ” (1ኛ ዮሐ.3.15)። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በማለት ብቻ አላበቃም፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በወንድሙ ላይ የስድብ ቃልን የሚያወጣና የሚንቅ ነፍሰ ገዳይ ነው ይላል። ነገር ግን እኛ ሰውን መስደብ እንደ ቀላል አድርገን ስለምንወስድ ልምድ አድርገነዋል። ኢየሱስ ግን መሳደብ ክፉና የሚገድል በመሆኑ ሰውን መስደብ ይቅርባችሁ ይለናል። ንቀትም ቢሆን እንደዚሁ ሰብዓዊ ክብርን እንደ መግደል ይቆጠራል ይለናል። የኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት ወደ እያንዳንዳችን ልብና አእምሮ ውስጥ በማስገባት፣ ሁለተኛ ማንንም አልሰድብም ማለትን በቻልን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን አትናቁ፣ ሰዎችን አትስደቡ፣ ሰዎችን አትጥሉ፣ ምክንያቱም ይህን ያድረጋችሁ ከሆነ ነፍሰ ገዳዮች ናችሁ ያለውን አስተውለን ተግባራዊ ብናደርገው ለሕይወታችን ጥሩ መመሪያ ይሆነናል።

ማንኛውም የፍርድ መንገድ ይህን በመሰለ መልኩ ፍርድ እንዲሰጥ ተደርጎ አያውቅም። ኢየሱስ ክርስቶስ ምስዋዕትህን ወደ ቤተመቅደስ ከማቅረብህ በፊት የበደልከው ወይም ያሳዘንከው ወንድም ካለ ፈልገውና ከእርሱ ጋር በቅድሚያ ታረቅ፣ በኋላም መስዋዕትህን አቅርብ በማለት ይመክረናል። ስለዚህ እኛም ብንሆን ወደ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመሄዳችን በፊት የተጣላነው ሰው ካለ፣ ከዚህ ሰው ጋር አስቀድመን መታረቅ ይኖርብናል። መጣላት ብቻ ሳይሆን ስለዚያ ሰው ክፉ ያሰብን እንደሆነ፣ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ከማቅረባችን በፊት ይቅርታን መጠየቅ ያስፈልጋል። መስዋዕተ ቅዳሴ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞም ቢሆን የሌሎችን ሰዎች ስም ያጎደፍን ከሆነ ይህ ጥሩ አይደለም። ስድብ፣ ንቀትና ጥላቻ አስከፊና ወደ ነፍሰ ገዳይነት ወንጀል እንደሚወስዱን ማሰብ ይኖርብናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ጉዳዩን ወደዚህ ደረጃ ያደረሰው ስለምንድነው? የሰው ልጅ የተከበረ ሕይወት አለው። አንድን ሕጻን ለማሳዘን ትንሽ ነገር ማለት በቂ ነው፣ ወዲያው ይቆጣል ወይም ያለቅሳል። አንድን ሴት ለማሳዘን ከተፈለገ ዝምታም በቂ ነው። አንድን ወጣት ለመናቅ ከተፈለገ እምነተ ቢስ ማድረግ በቂ ነው። ከአንድ ሰው መለያየት ከተፈለገ ስለዚያ ሰው እርግፍ አድርጎ አለማሰብ በቂ ነው። ለአንድ ሰው ሕይወት ግድ የለሽነትን የምናሳይ ከሆነ፣ ለዚያ ሰው በልባችን ውስጥ ቦታን ባለመስጠታችን እንገድለዋለን። ሰውን አለማፍቀር የመግደል መጀመሪያ ደረጃ ነው። አለመግደልም የማፍቀር መጀመሪያ ደረጃ ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሞት መጀመሪያ የተገለጸው እግዚአብሔር ቃኤልን ወንድምህ አቤል የት አለ ብሎ በጠየቀው ጊዜ የሰጠው መልስ ነው። ቃኤልም መለሰ፣ እንዲህ አለ፣ “አላውቅም፣ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን”? ሲል መለሰ ይላል። እኛስ ብንሆን ተመሳሳይ ጥያቄ ቢቀርብልን፣ “የወንድሜ ጠባቂ ንኝን”? ብለን መመለስ እንችላለን ወይ? በእርግጥ እኛ የወንድሞቻችን ጠባቂዎች ነን፣ አንዳችን የሌላችን ጠባቂዎች ነን። የሕይወታችን አካሄድም ይህን መምሰል ይኖርበታል።

የሰው ሕይወት ፍቅር ያስፈልገዋል። ስለዚህ እውነተኛ ፍቅር የቱ ነው? ብለን ብንጠይቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየን የምህረት መንገድ ነው። ለበደሉን በሙሉ ምሕረትን የሚያድረግ ፍቅር። ከመካከላችን ማንም ቢሆን ያለ ምሕረት ሊኖር አይችልም። ሁላችንም ምሕረት ያስፈልገናል። ስለዚህ መግደል ማለት የአንድን ሰው ሕይወት ማጥፋት ከሆነ፣ አለ መግደል ደግሞ ለሰው ልጅ አስፈላጊውን ክብርና እንክብካቤ በመስጠት የበደለንም ከሆነ ይቅርታን ማድረግን ያጠቃልላል።

ማንም ሰው በሌላ ላይ ክፉን አላደርግም በማለት ራሱን ማታለል የለበትም። ሕይወት የሌለው ግዙፍ ነገር ብቻ በሌላ ላይ ክፉ አላደርግም ሊል ይችላል፣ ነገር ግን የሰው ልጅ ይህን ማለት አይችልም። አንድ ሰው ክፉን በማድረግ ፈንታ የበኩሉን መልካም ተግባር እንዲያደርግ የቀረበለት ጥያቄ አለ። “አትግደል” የሚለው የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ሌሎችን እንድናፈቅር፣ ምሕረትንም እንድናደርግላቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ የቀረበልን ጥያቄ ነው።  ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረትን ሊያስገኝልን ለበደላችን ሞተ፣ ከሞትም ለእኛ ሲል ተነሳ። በዚህ አደባባይ ላይ ሆነን፣ አንድ ቅዱስ የተናገረውን ዐረፍተ ነገር መድገማችን ይታወሳል፣ ይህም “ክፉን አለማድረግ መልካም ነው፣ መልካምን አለማድረግ ክፉ ነው” የሚል ነበር።

እግዚአብሔር ስጋን በመልበሱ እኛን ቀድሶናል፣ በደሙ ትልቅና ክቡር አድርጎናል፣ ሕይወትንም ሰጥቶናል። ለዚህ ታላቅ ቅስጦታው እግዚአብሔር አባታችንን እናመሰግነዋለን። በፍቅሩ ብዛት በሞትን አሸንፈነዋል። እግዚአብሔር አባታችን በሚሰጠን የመንፈስ ቅዱስ ሃይል በመታገዝ አትግደል የሚለው ትዕዛዝ ሌሎችን እንድናፈቅር የቀረበልን ጥሪ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን”።                         

17 October 2018, 18:02