ፈልግ

ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር ሕይወትን ይወዳል፤ ፅንስ ማስወረድ የሰው ልጅ ተግባር አይደለም”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት ማለትም ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን፣ ነጋዲያንና ሀገር ጎብኝዎች የተለመደውን ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት የጠቅላላ ትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ማቅረባቸው ተመልክቷል። የቅዱስነታቸው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘት የሚከተለው ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ ግርማቸው ተስፋዬ - ቫቲካን

“በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወድ ወንድሞቼና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬው ትምህርታችን ከ10ቱ ትዕዛዞች በ5ኛው ላይ የሚያተኩር ሲሆን ይህም ትዕዛዝ ኣትግደል የሚለው ነው። ኣሁን የዐሥርቱን ትዕዛዝ ሁለተኛ ክፍል ጀምረናል ይህም ትዕዛዝ ከወንድማችን ጋር ያልንን ግንኙነት በተመለከተ ሲሆን በተጨማሪ ኣትግደል የሚለው ትዕዛዝ የሰዎች መሠረታዊ ግንኙነት እንከን እንዳያጋጥመው ልክ እንደ መከላከያ ግንብ ሆኖ የሚያገለግል ነው። በዓለም ላይ ያሉ ክፋቶችና ኃጢኣቶች ሁሉ በዚሁ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው ለማለት ይቻላል ለሕይወት ተገቢውን ቦታና ክብር አለመስጠት።

ሕይወት በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጥቃት ይደርስባታል ኣንዳንድ ድርጅቶችም ሰዎችን በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢውን ነገር ሳያደርጉላቸው ለራሳቸው ጥቅም ብቻ ይጠቀሙባቸዋል የራሳቸውንም ትርፍ ብቻ ለማብዛት የሌሎችን ችግር እነሱ የበለጠ ሊያድጉበት ወዲህና ወዲያ ሲሉ ይስተዋላሉ ነገር ግን ይህ በሚሆንበት ሰዓት ኣንዳንድ ሰዎች ለሰው ባልተገባ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ይኖራሉ።

ኣንዳንድ ጊዜ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሓሳብም ሲሰነዘር ይሰማል ይህም የሌሎችን ሰዎች መብት ለመጠበቅ በሚል ሰበብ በማህፀን ውስጥ ያለውን የሰውን ህይወት ያጠፋል። ነገር ግን እንዴት የሰዉን ያዉም ምንም የማያውቅን በማህፀን ውስጥ ያለን ነብስ አጥፍቶ ሰብአዊነት ነው ለማለት ይቻላል?

ይህ ሁሉ ከየት የመነጨ ይመስላችኋል? ይህ ሁሉ የሚመጣው በፍርሃት ውስጥ ከተደበቀ ሥርዐት አልበኝነትና እንቢተኝነት የሚመጣ ነው። ኣንዱ ሌላውን የመቀበል ሁኔታ በእርግጥም ትልቅ ፈተና የሆነበት ጊዜ ነው። እስቲ ትንሽ ቆም ብለን እናስብ ኣንዳንድ ጊዜ በእርግዝና ወቅት በሚያጋጥሙ የተለያዩ ዓይነት እክሎች ወላጆች በኋላ የሚመጣዉን ነገር በመፍራት ያ እርግዝና እንዲቋረጥ የተለያዩ ምክሮችን ከተለያዩ ቦታዎች ይቀበላሉ ነገር ግን የሰው ልጅ ካለው ክብር ኣንፃር ሲታይ በዚህና ተመሳሳይ በሆኑ ችግሮች ኣማካኝነት የሚገኙ ወላጆች ያለዉን እውነታ እንዲጋፈጡ የበለጠ ሊታገዙና ሊበረታቱ ይገባል።

ኣንድ ታማሚ ሕፃን ልክ አንድ በምድር ላይ ያለ ሰው ኣንድ የሚያስፈልገው ነገር እንዳለው ሰው ዓይነት ነው ኣንድ ታማሚ ሕፃን ልክ እንደ አንድ አረጋዊ ወይንም በእርጅና ውስጥ እንዳለ የሌላውን የቅርብ እርዳታ እንደሚፈልግ ዓይነት ሰው ነው ኣንድ ታማሚ ሕፃን ልክ ራሳቸዉን ለማቆም እየታገሉ ያሉ ብዙ ድሃ ሰዎች ዓይነት ነው። እራሱን እንደ ችግር የሚያቀርብ ሰው በእርግጥ ከራስ ወዳድነት ለራሴ ብቻ ከማሰብ ሊያወጣኝ የሚችል ከእግዚአብሔር የተላከልኝ ስጦታ ነው።

የተጎዳ ሕይወት ወይም ደግሞ የሌሎች ስቃይ ለሌሎች የሚኖረኝን ፍቅርን ያሳድጋል የህይወት መውጫ መንገዱን ያሳየናል። እኛ እራሳችንን ከሕልውናችን ውስጥ እራሳችንን ለማዳን እና የፍቅርን ደስታ ለማግኘት ራሳችንን እንድንጠይቅ ይረዳናል። ሰውን ለሕይወት ፊቱን እንዲያዞር የሚያደርጉት ነገሮች ምን ይመስላችኋል? የዚህ ዓለም ገዢ የሆኑት ገንዘብ ሥልጣን ክብር ዝናና የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ ህይወት ለመገምገም ትክክል ያልሆኑ መመዘኛዎች ናቸው ብቸኛው የህይወት መለኪያ ፍቅር ነው ልክ እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ በሚወድበትና በሚያፈቅርበት ዓይነት።

አትግደል የሚለው ቃል አዎንታዊ ትርጉሙ ምንድን ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ እንደሰማነው አምላክ "ሕይወትን የሚወድ" አምላክ መሆኑን ተመልክተናል።

የህይወት ምሥጢር በእግዚአብሔር ልጅ ኣማካኝነት እንዴት ተደርጎ መያዝና መጠበቅ እንዳለበት ተገልጾልናል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው ከመሆን ጀምሮ መስቀልን ወቀሳን ድክመትን ድህነትንና ሥቃይን እንደተቀበለ በዮሐ. 13፡1 ላይ በሚገባ ተገልጾ እናገኘዋለን። በእያንዳንዱ ደካማ ልጅ በእያንዳንዱ ደካማ ሽማግሌ ተስፋ በቆረጡ ስደተኞች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወታቸው የተጎዳ ሁሉ ክርስቶስ እንደሚፈልጋቸው (ማቴ 25፣ 34-46) ተጠቅሶ እናገኛለን።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የፍቅርን ደስታ ማግኘት እንድንችል ልባችንን ሊከፍትልን ዘወትር ይፈልገናል። እያንዳንዱን ሰው መቀበል ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው የክርስቶስ ደም ዋጋ ያለው በመሆኑ ነው (1 ጴጥ 1 18-19). አምላክ የሚወደውን ነገር አምላክ ያከበረዉን ነገር ማቃለል አይቻልም።

በዓለም ላይ ላሉ ወንዶችን እና ሴቶች ሁሉ የራሳቸውን እንዲሁም የሌሎችን ሕይወት በሚገባ ጠብቁ ብለን መንገር ይስፈልጋል ምክንያቱም ይህ "አትግደል" የሚለው ትዕዛዝ የሚያመለክተው ይህንን ነው። ለበርካታ ወጣቶች ህይወታቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ሥራ በእነርሱ ውስጥ እንዲከናወን ልባቸውን መክፈት ያስፈልጋል ምክንያቱም ሁላችን የእግዚአብሔር ሥራ ውጤቶች ነንና ነው።

ማንም ሰው በዚህ ዓለም አታላይነት ላይ ተመርኩዞ ሕይወትን አይለካም ነገር ግን እያንዳንዳችን ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እያንዳዳችንን በፈጠረን በእግዚኣብሔር ስም እንቀበላለን እርሱ "ሕይወትን የሚወድ" ኣምላክ ነው እኛም ለእርሱ እጅግ ኣድርጎ የሚወደን ልጆቹ ነን ኣንድያ ልጁን ወደ እኛ የላከበትም ምክንያት ይኸው ፍቅሩ ነው። በእውነት እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጥቷል በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና" (ዮሐንስ 3:16)

10 October 2018, 17:55