ፈልግ

2018.09.28 Rosario 2018.09.28 Rosario 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቤተክርስቲያን መጸለይ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

የቤተክርስቲያን ቁስሎችን በጸሎት መፈወስ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሃይልንና ፍቅርን በመጨመር፣ እንዲሁም ለቤተክርስቲያን ታማኞች እንድንሆን በማድረግ ታግዘናለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአውሮጳውያኑ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ዛሬ በተጀመረው የጥቅምት ወር ለቤተክርስቲያን መጸለይ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። የክርስቲያን ማሕበረሰብን ከሚከፋፍል ክፉ መንፈስ እግዚአብሔር እንዲሰውረን በማለት በመላው ዓለም የሚገኙ ምዕመናን በሙሉ በየዕለቱ ጸሎታቸውን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ወደ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ዘንድ ጸሎት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ሲያሳስቡ ቤተክርስቲያን በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው መላው የዓለም ምዕመናን በየቀኑ የመቁጠሪያን ጸሎት በማድረስ፣ የክርስቲያኖን አንድነት ለማናጋት የተነሳውን ክፉ መንፈስ ለመዋጋት የሚያስችለንን ሃይል እንድናገኝ ጸሎታችንን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ወደ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል እንድናደርስ አደራ ማለታቸውን ከቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል የወጣው መግለጫ አስገንዝቧል። ቅዱስነታቸው ይህን ጥሪያቸውን ያቀረቡት በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባልና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሚደረግ ዓለም አቀፍ የጸሎት ሕብረት አስተባባሪ ለሆኑት ለክቡር አባ ፍረደሪች መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ  ሊቃነ ፍራንችስኮስ ጳጉሜ 5 ቀን 2010 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ እንዳስገነዘቡት በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የቤተክርስቲያንን አንድነት ለማደፍረስና በምዕመናን መካከል ክፍፍልን ለመፍጠር የተነሳ ታላቅ ክፉ ሃይል እንዳለና ይህንን ሃይል በሌላ ሳይሆን በጸሎት ሃይል ማሸነፍ እንደሚቻል ማሳሳባቸው ይታወሳል።

የዓለም አቀፍ ጸሎት ሕብረት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አባ ፍረደሪች፣ በእነዚህ መጨረሻዎቹ ዓመታትና ወራት ውስጥ ቤተክርስቲያን አስቸጋሪ የፈተና ወቅቶችን መካከል እንደምትገኝ ገልጸው ከፈተናዎችም መካከል ወሲባዊ ጥቃቶች፣ በስልጣን መባለግ፣ በቤተ ክህነት፣ በገዳማዊያንና በምዕመናን በኩል የታዩት ምግባረ ብልሹነት እንደሚገኙበት አስረድተዋል። አባ ፍረደሪች በማከልም በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታየውን መከፋፈል መርሳት የለብንም ብለው ይህ ሊመጣ የሚችለው ውድቀትንና ሞትን ማየት ከሚሻ ከሰይጣን በኩል መሆኑን የማሕበራቸው መሥራች ቅዱስ ኢግናሲዮስ ያለውን በመጥቀስ አስታውሰዋል።

ቤተክርስቲያን የሰጠችንን አደራና ሃላፊነት ወደ ጎን በማድረግ በእውነተኛ ሕይወት እንዳንመራ የሚያደርጉን የተሳሳቱ መንገዶች አሉ ያሉት አባ ፍረደሪች፣ እነርሱም በሃብት መመካት፣ እብሪተኝነትና ኩራት መሆናቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ መናገራቸውን አስታው እነዚህ መጀመሪያ ላይ ጥሩ መስለው በመታየት ነገር ግን ቀስ በቀስ ወደ ጥፋትና ወደ ውድቀት በመምራት ዓላማቸውን ወደ ማሳካት ይደርሳሉ ብለዋል። ለመላው እግዚአብሔር ሕዝብ ብለው በጻፉት መልዕክታቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የዘንድሮን የአብይ ጾም በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ እንደ እባብ አሳሳች የሆኑ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ተሳሳተ መንገድ ይወስዱናል። የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማታለል፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚገኘውን እውነተኛ ደስታን በጊዜያዊ ደስታ በመለወጥ፣ በመጨረሻም ብዙዎችን ለብቸኝነት ሕይወት በመዳረግ ወደ ባርነት ቀንበር ይጎትታሉ ማለታቸውን ክቡር አባ ፍረድሪች አስታውሰዋል። በማከልም እነዚህን የቤተክርስቲያን ቁስሎችን በጸሎት መፈወስ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሃይልንና ፍቅርን በመጨመር፣ እንዲሁም ለቤተክርስቲያን ታማኞች እንድንሆን በማድረግ ታግዘናለች ብለዋል።  በመሆኑም በችግር እንዳንሸነፍ፣ ለክፉ መንፈስም እድል እንዳንሰጥ፣ የክርስቲያኖች እናት፣ የቤተክርስቲያን እናት ወደ ሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እንዲሁም ቤተክርስቲያንን ከፈተናና ከውድቀት፣ ከማንኛውም ዕይነት ጥቃት እንዲጠብቃት ወደ ሊቀ መላዕክቱ ወደ ቅዱስ ሚካኤል ጸሎታችንን በያዝነው ወር እንድናቀርብ ማሳሰባቸውን ክቡር አባ ፍረደሪች ገልጸዋል።      

01 October 2018, 18:15