ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመሬት መንቀጥቀጥና በባሕር መናወጥ የተጎዱትን በጸሎታቸው አስታወሱ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተናንትናው ዕለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ ነጋዲያንና ሀገር ጎብኚዎች በሙሉ በዕለቱ በተነበበው ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ የብሥራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። በመቀጠልም በስፍራው ለነበሩት በሙሉ ሰላምታቸውንም አቅርበው በከባድ የባሕር መናወጥ የተጎዳውን፣ በኢንዶኔዢያ የሱላዌሲ ሕዝብን በማስታወስ በዚህ አሰቃቂ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡትን፣ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸውን፣ ከቤት ንብረት፣ ከሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉትን በሙሉ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜም በመንፈስም አብሮአቸው እንደሚሆኑ ገልጸዋል። በተጨማሪም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከተገኙት ምዕመናን ጋር በሕብረት ሆነው ለሱላዌሲ ሕዝብ በሙሉ የሰላም ለኪ ማርያም ሆይ ጸሎትን ደግመዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም በዕለቱ በፈረንሳይ ማርሲሊያ፣ የዣን ባቲስት ፎክ ብጽዕና አዋጅን ይፋ አድርገዋል። ዣን ባቲስት ፎክ በማርሲሊያ በሚትገኝ ቁምስና ሕይወቱን በሙሉ ምክትል ቆሞስ ሆኖ ያገለገለ የሰበካ ክህን እንደነበረ አስታውሰዋል። ካህኑ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መካከል፣ ወጣቶችን፣ አዛውንትን፣ ድሆችንና የታመሙትን በመንከባከብ በርካታ ማሕበራዊ አገልግሎቶችን እንዳበረከተ አስታውሰው፣ የዚህን ሐዋርያ የፍቅር ምሳሌን በመከተል የተቸገሩትን፣ መጠጊያ የሌላቸውን፣ አቅመ ደካሞችን ተቀብለን እንድንረዳቸው እግዚ አብሔር ሀይሉን ያብዛልን ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ከሮምና አካባቢዋ ለመጡትን ምዕመናንን፣ ከተለያዩ አገሮች ለመጡት ነጋዲያንም ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በተለይም ከስፔን ለመጡት ምዕመናን፣ ከሳልስቡርጎ ለመጡት የከንቲባ አባላትና የተለያዩ አውራጃዎች አስተዳዳሪዎች፣ ዕለቱ ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቀን እንደመሆኑ የዚህ ዓለም አቀፍ ማሕበር ተወካዮች በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በማከልም በደቡብ ኢጣሊያ የካምፓኒያ ክፍለ ሀገር የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር አባላትንና በፉቼኪዮ የሻሎም እንቅስቃሴ ወጣቶችን፣ በኢጣሊያ ውስጥ የፎጃ እና የራፓሎ ምዕመናን ሰላምታቸውን ካቀረቡ በኋላ በአደባባዩ ላይ ለተሰበሰቡት በሙሉ መልካም ዕለተ እሑድን ተመኝተው ምዕመናኑም በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለው መልካም ምሳን በመመኘት ተሰናብተዋል።   

01 October 2018, 17:55