ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ቅዱሳን በኢየሱስ ክርስቶስ በሙላት እንድንኖር ያስተምሩናል”።

እሑድ ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ. ም. መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ ሰባት አዳዲስ ቅዱሳኖችን ለመላው ምዕመናኖቿ ይፋ አድርጋለች። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ ነጋዲያንና የሃገር ጎብኝዎች እንዲሁም በመላው ዓለም የዕለቱን ልዩ የመስዋዕተ ቅዳሴውን ስነ ስርዓት ለተከታተሉት በሙሉ፣ ስባት የቤተክርስቲያን ልጆች ወደ ቅድስና መብቃታቸው ይፋ አድርገዋል። ቅድስናቸው የታወጀላቸውም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ፣ አቡነ ኦስካር አርኑልፎ ሮመሮ ጋልዳሜዝ፣ ፍራንቸስኮ ስፒነልሊ፣ ቪንቼንሶ ሮማኖ፣ ማርያ ካታሪና ካስፐር፣ የቅድስት ተሬዛ ናዛሪያ ኢኛሲያና ኑንሲዮ ሱልፕሪዚዮ መሆናቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሮም 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤን በመካፈል ላይ ከሚገኙት ብጹአን ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳትና ክቡርን ካሕናት ጋር ሆነው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት የስብከተ ወንጌል አስተንትኖ እንደገለጹት ቅዱሳን በኢየሱስ ክርስቶስ በሙላት እንድንኖር ያስተምሩናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከማር. ወንጌል ምዕ. 10፤ 17-30 ተውስዶ የተነበበውን ቅዱስ ወንጌል መሠረት በማድረግ ያሰሙት አስተንትኖ ትርጉም ይዘት የሚከተለው ነው። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ።

በሁለተኛ የተነበበው ወደ ዕብራውያን የተላከ መልዕክት በምዕ. 4 ቁጥር 12 ላይ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው፣ ሁለት አፍ ካለው ሰይፍ ይልቅ ስለታም ነው” በማለት ይናገራል። የእግዚአብሔር ቃል በእርግጥም መንፈሳዊ፣ እውነቶች የተገለጡበት ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወታችንን በሚነካና የሚለውጠን ዘለዓለማዊ ቃል ነው። በዚህ ቃል በኩል ሰው ሆኖ የተገለጠው፣ ዘለዓለማዊ ቃል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዳችን ልብ ይናገረናል።

ከማርቆስ ወንጌል ከምዕ. 10 ተውስዶ የተነበበውና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሮጦ የሄደው ሰው ታሪክ፣ እኛም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንድናገናኝ ይጋብዘናል። ይህ ስሙ ያልተጠቀሰውና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሮጦ የሄደው ሰው እኛን እንደሚወክለን አድርገን መቁጠር ይኖርብናል። ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ያቀረበው ጥያቄ “ደግ መምሕር ሆይ! የዘለዓለምን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይገባኛል?! የሚል ነበር። የጠየቀውም ወይም የፈለገው ሙሉና ዘለዓለማዊ ሕይወትን ነበር። ዘለዓለማዊና ሙሉ ሕይወት ለማግኘት የሚያስችለውን ትዕዛዛት፣ ከወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ የጠበቃቸው ወይም ያከበራቸው መሆኑን ለኢየሱስ በተናገረ ጊዜ ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው ይላል በማርቆስ ወንጌል በምዕ. 10 ቁ. 21. ላይ። ኢየሱስ ክርስቶስም ሃሳቡን፣ ይህ ሰው፣ ትዕዛዛትን ጠብቆ እንደሆነ ለማወቅ ከነበርው ወደ ነጻና ሙሉ ፍቅር አሸጋገርው። ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሙሉ ፍቅር ሲናገር ነገር ግን ሰውየው የሚናገረው ወይም የሚያስበው ለዕለታዊ ሕይወት ስለሚያስፈልጉ ነገሮች ነበር። ኢየሱስም፣ ይህ ሰው፣ ትዕዛዛትን በመጠበቁ ምክንያት ለራሱ ከሚያተርፈው ጥቅም ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንደሚሻል ሃሳብ ያቀርብ ነበር። ስለዚህም ቁርጥ ውሳኔን እንዲያደርግ በማለት “አንድ ነገር ብቻ ቀርቶሃል፣ ሂድ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ገንዘብህን ለድሆች ስጥ፣ ከዚያ በኋላም ተከተልኝ አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ኑና ተከተሉኝ ሲል በአንድ ስፍራ መቆም አያስፈልግም። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመሆን ክፉን አለማድረግ በቂ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ተከተሉኝ ሲላችሁ፣ በምትፈልጉበት ጊዜ ብቻ ከኋላው ሆናችሁ መከተል የለባችሁም። ትዕዛዛትን አክብራችሁ ስለተገኛችሁ ወይም ካላችሁ ለደሃ በማካፈላችሁ፣ ወይም በየዕለቱ ጸሎት ማቅረብ ስለቻላችሁ ደስታ ሊሰማችህ አይገባም። በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘለዓለም አፍቃሪያችሁ፣ የሕይወታችሁ ትርጉም፣ የዘወትር ሃይላችሁ የሆነው እግዚአብሔርን አግኙት።

ኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን በሙሉ ሽጡና ለፍድሆች ስጡ ይላል። ይህን በሚልበት ጊዜ ስለ ድህነት ወይም ስለ ሃብት የተለያዩ ገለጻዎችን ማቅረብ አልፈለገም። ቀጥታ ወደ ሕይወት ውስጥ ነው የገባው። ልባችሁ ውስጥ የሞላውን ከባድ ሸክም አውጥታችሁ በመጣል ለእግዚአብሔር ቦታን ስጡት። በብዙ ዓለማዊ ነገሮች ተሸብበን ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት መከተል አንችልም። ልባችን በቁሳዊ ሃሳቦች የተሞላ ከሆነ ለኤይሱስ ክርስቶስ አንዳችም ቦታ አይኖረውም። ስለዚህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደሚለው፣ ምድራዊ ሃብት፣ የመዳን ተስፋችንን ያጨልምብናል። ይህም እግዚአብሔር ሩቅ በመሆኑ አይደለም። ነገር ግን በስግብግብነት ብዛት፣ ይህን ተከትሎ የልብችን ምኞት እጅግ ብዙ በመሆኑና ከራሳችን አልፈን ሌሎችን እንዳናፈቅር አንቆን ስለሚያስቀረን ነው። ይህን አስመልክቶ ሐዋ. ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ “የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ምንጭ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ከእምነት ርቀዋል፣ ልባቸውንም በሐዘን ጦር ወግተዋል” ይላል። ይህን ማየት የምንችለው ሰዎች ለእግዚአብሔር ወይም ለሰዎች ቦታን ከመስጠት ይልቅ ለገንዘብ ቦታን በሚሰጡበት ጊዜ ነው። 

ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅሩን ሙሉ አድርጎ ሰጥቶናል። እኛም በምላሹ ሙሉ ልባችንን እንድንሰጠው ይፈልጋል። ዛሬም ቢሆን ራሱን በሕያው እንጀራ አማካይነት ይሰጠናል። እርሱ የእኛ አገልጋይ ሆኖ፣ ለእኛ ሐጢአት ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሞትን ከመረጠ፣ እኛ በምላሹ ምን ልንሰጠው እንችላለን? ከትዕዛዛት መካከል ጥቂቶቹን መፈጸም ወይም ማክበር በቂ ሊሆን አይችልም። ዘለዓለማዊ ሕይወት ለሚሰጠን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን መካከል የተወሰኑ ጊዜያትን ብቻ መስጠት በቂ አይሆንም። ፍቅራችንን በመጠን ስንገድብ ኢየሱስ ክርስቶስ አይደሰትም። ሃያ፣ ሃምሳ ወይም ስልሳ ከመቶ ብቻ ኤይሱስን ማፍቀር አንችልም። ማፍቀር ካለብን በሙሉ ልባችን መሆን ያስፈልጋል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ልባችን እንደ ማግኔት በፍቅር ይሳባል። የሚሳበውም ጌታችን ሊሆንነ ወደሚችለው ወደ እግዚአብሄር ፍቅር ወይም ወደዚህ ዓለም ሃብት ነው። “አንድ ሰው የሁለት ጌታ አገልጋይ ሊሆን አይችልም፣ አንዱን ይጠላል ሌላውን ይወዳል፣ አንዱን ያከብራል ሌላውን ይንቃል። እንዲሁም የገንዘብ ተገዥ የሆነ ሰው የእግዚ አብሔር አገልጋይ መሆን ከቶ አይችልም”  (ማቴ. 6.24)። “ሕይወቱን ለማዳን የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፣ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያድናታል” (ማር. 8.35)። ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ፍቅር፣ ምን ደረጃ ላይ ነን ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። አንዳንድ ትዕዛዛትን ብቻ በመጠበቃችን ደስተኞች ነን? ወይም ያለንን ሁሉ ትተን እርሱን ልናፈቅር ዝግጁዎች ነን? ኢየስሱ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን ሆነ እንደ ቤተክርስቲያን አንድ ጥያቄ ይጠየናል። መልካም ትዕዛዛትን የምትሰብክ ቤተክርስቲያን ብቻ ወይስ የመሠረታትን ኢየሱስ ክርስቶስ የምታፈቅር ቤተክርስቲያን ነን? ኢየሱስ ክርስቶስን በእውነት የምንከተል ወይስ ወደ ዓለማዊው አቅጣጫ የዞርን። ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ይበቃናል ወይስ ሌሌች በርካታ ዓለማዊ ዋስትናዎችን መፈለግ ይኖርብናል? ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳንከተል የሚያደርጉንን ነገሮች አውልቀን ለመጣል የሚያስችለንን ጸጋ እንለምን። ዓለማዊ ሃብት፣ ዝናና ሥልጣን፣ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ከተልዕኮአችን ወደ ኋላ የሚያስቀሩን እንጂ ለወንጌል አገልግሎት የሚጠቅሙን አይደሉም። ቤተክርስቲያናችን ያለ ፍቅር ጉዞ ጤናማ ልትሆን አትችልም። በጊዜያዊ ደስታ እንታለላለን፣ በሃሜት እንዋጣለን፣ ትርጉም የሌለውን ኣሳዛኛን ጎዶሎ ክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር እንፈልጋለን።  

ይህን የምናደርግ ከሆነ፣ ቅዱስ ወንጌል እንደሚለን፣ በሐዘን ውስጥ ወድቆ ሃብቱን ላለመተው ፈልጎ ወደ ኋላ የተመለሰውን ሰው እንሆናለን። ልቡ የተመኘው ወይም የሚያስበው ሕግጋትን ለማክበር ወይም ለመፈጸም፣ ሃብት ለማከማቸት እንጂ ሌላ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኘው ቢሁንም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ዓይኑ የተመለከተው ቢሆን በሐዘን ተውጦ ሄዶአል . . . . .”።     

15 October 2018, 17:54