ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “በሮም በግፍ የተገደሉት ክርስቲያኖች መቃብር በይፋ መታሰብ ይጀምራል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተናንትናው ዕለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ ነጋዲያንና ሀገር ጎብኚዎች በሙሉ በዕለቱ በተነበበው ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ የብሥራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። በመቀጠልም በስፍራው ለነበሩት በሙሉ ሰላምታቸውንም ካቀረቡ በኋላ ዕለቱ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል የሚከበርበት ዕለት መሆኑን አስታውሰዋል። በዚህም መሠረት የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ በሚገኝበት በመካከለኛው የደቡብ ኢጣሊያ ግዛት በሆነው በፖምፔይ፣ በሶርያ የቅድስት መንበር ልዑክ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ጋር በመሆን ጸሎታቸውንና መስዋዕተ ቅዳሴን ላቀረቡት ምዕመናን የከበረ ሰላምታቸውን ልከውላቸዋል። ቅዱስነታቸው የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል የተከበረበትን ዕለት አጋጣሚ በማድረግ ምዕመናን በተጀመረው የአውሮጳዊያኑ ጥቅምት ወር በቀኑ የመቁጠርያ ጸሎትን እንዲደግሙ አደራ ብለው፣ ቤተክርስቲያንን ከጥቃትና ከክፍፍል እንዲጠብቃት ወደ ሊቀ መልዓኩ ወደ ቅዱስ ሚካኤልም ጸሎታቸውን እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።   

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም መጭው ቅዳሜ በሮም በግፍ የተገደሉት ምዕመናን የተቀበሩበት ዋሻ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚታወስበት እለት እንደሚሆን አስታውሰው፣ እነዚህ የመቃብር ስፍራዎች ለጎብኝዎች ክፍት ሆነው እንደሚቆዩ ገልጸዋል። ይህን አጋጣሚ ላመቻቹት፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የቅዱስ ስፍራዎች ተንከባካቢ ጽሕፈት ቤት አመስግነዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከሮምና አካባቢዋ፣ በ ኢጣሊያ ከተለያዩ ክፍላተ ሃገር ቁስናዎች እንዲሁም ከመላው ዓለም ለመጡት ነጋዲያንና ቤተሰቦች በሙሉ ልብዊ ሰላምታቸውን አቅርበዋል። በማከልም የግሪክ ካቶሊክ ስርዓት የሚከተሉ የስሎቫኪያ ካቶሊካዊ ምዕመናንን፣ ከፖላንድ የመጡ የፖዝናን ምዕመናንን፣ ከብራዚል የመጡ የፎርታለዛ ምዕመናንን፣ ከማልታ የመጡ አረጋዊያንን፣ ከፈረንሳይ የመጡ ተማሪዎችንና ከአውስትራሊያ ለመጡት የቅዱስ ጳውሎስ ደናግል ማሕበር አባላት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ለቅዱስ ልበ ኢየሱስ እና ለቅዱስ ልበ ማርያም ማሕበር ነጋዲያን፣ በኢጣሊያ የብረሻ መዘምራን ማሕበር፣ የላዚዮ ክፍለ ሃገር ሴት ተማሪዎችንና ለአቢያተግራሶ ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበው፣ ለምዕመናን በሙሉ መልካም ሰንበትንና መልካም ምሳን በመመኘት ከባረኳቸው በኋላ ምዕመናኑ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።   

08 October 2018, 17:44