ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የአባቶች ራዕይ፣ እሴቶችና ምስክርነቶች ያስፈልጉናል”

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአባቶች ራዕይ፣ የቤተክርስቲያን እሴቶችና ምስክርነቶች በግልጽ መታየት እንዳለባቸው አሳሰቡ። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ትናንት ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ. ም. በአጎስቲኒያን ኢንስቲትዩት፣ ወጣቶችንና አዛውትን ባገኙበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ ራዕይን የሚያዩ አባቶች፣ ወጣቶችን የሚያንጹ ምስክርነቶችና፣ የቤተክርስቲያን እሴቶች በግልጽ መታየት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ይህን ያሳሰቡት “የጊዜውን ጥበብ” በሚል ርዕሥ የተጻፈው መጽሐፍ ለአንባቢያን ይፋ በተደረገበት አጋጣሚ ላይ በመገኘት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

በሰዎች መካከል ልዩነቶችንና እንደዚሁም በትውልዶች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲቋርጥ የሚያደርገውን ባሕል መቃወም የሚቻለ በወጣቶችና በአዛውንት መካከል ውይይቶችን በማካሄድ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል። የእርሳቸውን ሃሳብ መሰረት ያደረገና “የዘመኑን ጥበብ እንጋራ” በሚል አርዕስት የታተመ መጽሐፍ ለአንባቢያን ይፋ መሆኑ ታውቋል። የሚቀጥለው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የሚከናወንበት አገር ፓናማ የመጡት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ሜንዲየታ፣ ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላምታ ባቀረቡበት ጊዜ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በትውልዶች መካከል ያለ የጠበቀ ግንኙነት፣ ሕዝቦችን የሚያስተሳስር ጥበብ እንዲጋሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። እያንዳንዱ ትውልድ በመልካም ሁኔታ የሚኖርበትን ጥበብ የሚያገኘው ካለፉት አባቶች ነው ብለው ያለፉት አባቶች ጥበብና ማስተዋል በዘመናችን ትውልድ መካከል መታየት ወይም መንጸባረቅ ይኖርበታል ብለው አሁን በዘመናችን የሚታየው የቤተሰብ መቀራረብ፣ የትውልዶች መመሳሰል ሕብረተሰባችን ወደ ፊት እንዲጓዝ የሚያደርጉ ከቀድሞ አባቶች የወረስናቸው እሴቶች ናቸው ብለዋል። ቤተክርስቲያንም ይህን በመገገንዘብ በወጣቶችና በአዛውንት መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ የበኩሏን ተልዕኮን እንድተወጣ ያስፈልጋል ብለዋል።

መጽሐፉ ለንባብ ይፋ በተደረገበት ዝግጅት የተገኙት የካቶሊካዊ ስልጣኔ መጽሔት ዳይረክተር ክቡር አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ በበኩላቸው መጽሐፉ እንዲታተም የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ፍላጎት እንደሆነ አስረድተው በመጽሐፉ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረጉት፣ ከ30 አገሮች በላይ ለተሰበብሰቡት 250 ጥያቄዎች መልሶችና ትናታኔዎች እንዲሰጡበት ተደርጓል ብለዋል። መጽሐፉን ለማሳተም እገዛ ያደረጉትን በኢየሱሳዊያን ማሕበር የስደተኞች አገልግሎት ክፍልን አመስገነዋል። አባ አንቶኒዮ ስፓዳሮ በማከልም ወጣቶች የሥራን ክብርና አስፈላጊነት፣ ለችግሮች እጃቸውን እንዳይሰጡ ጥረት ማድረግ፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ተስፋና ሞትን አስመልክተው  አባቶች መዕክታቸውን በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

እምነት ከሕይወት ምስክርነት ጋር ይሁን፣

እምነት በሕይወት ምስክርነት የታገዘ መሆን አለበት ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጋብቻቸውን ከፈጸሙ 43 ዓመታትን ያስቆጥሩ የማልታ ተወላጆች ቶኒ እና ግሬስ ናውዲ ለልጅ ልጆቻቸው እምነትን በተረትና ምሳሌ እየነገሯቸው እንዲያስተምሯቸው፣ በእለታዊ ኑሮአቸው በተግባር እያሳዩ መመስከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቱ ትውልድ ከአዛውንት ጋር ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ሲገልጹ፣ ወጣቶች የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑ ሰዎች ምክርና ተግሳጽ ችላ ማለት እንደሌለባቸው አስገንዝበው አዛውንት ከወጣቶች ጋር በሚፈጥሩት የጠበቀ ግንኙነት በኩል የወደፊት ሕይወታቸው መልካም እንዲሆን ለማድረግ መሪና አጋዥ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

“የጊዜውን ጥበብ መጋራት”  በሚል አርዕስት የተጻፈው መጽሐፍ፣ በሌሎች ርዕሦችም ለምሳሌ ስለ ፍልሰትና በፍልሰት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ አሰቃቂ አደጋዎች የሚዘረዝር ሲሆን የሰዎችን መሰደድና የሚደርስባቸውን አደጋ ለማስቆም የአገራቱ መንግሥታት፣ ሕግ አውጭ አካላትና የዓለም መሪዎች በጋራ ሆነው የስዎችን ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ የጋራ ሃላፊነቶችን መውሰድ እንዳለባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳስበዋል።

24 October 2018, 16:40