ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ቤተክርስቲያንን እናት ሆና እንድትቆይ ማድረግ ተገቢ ነው”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በቫቲካን በተጀመረው 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ሲኖዶስ ላይ በመገኘት፣ ጉባኤውን ለሚካፈሉት ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግልና ወጣት የምዕመናን ተወካዮች የመክፈቻ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። የቅዱስነታቸው ንግግር ሙሉ ይዘት ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ የተቀመጠው ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም ውድ ወጣቶች በሙሉ። ወደዚህ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ስንገባ በእርግጥም የወጣቶች ሃይል፣ ችሎታና ደስታን የተላበሰ ብሩሕ አመለካከት በዚህ ስፍራ ብቻ ሳይሆን በመላዋ ቤተክርስቲያንና በዓለም ዙሪያ በሙሉ እንደሆነ እንገነዘባለን።

ይህንን በቅድሚያ በመግለጽ ምስጋናዬን ሳላቀርብ ንግግሬን መጀመር አልችልም። እዚህ ለተገኛችሁ በሙሉ፣ ከሁለት ዓመታት ወዲህ በሮምም ሆነ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ቤተክርስቲያኖች ዝግጅቶችን በማድረግ ወደዚህ ደረጃ እንድንደርስ በማድረግ ብዙ ለደከማችሁና ለለፋችሁት በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ሎረንዞ ባልዳሰሪ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ዘርፍ ለተሰማራችሁ ተወካይ ሊቃነ መናብርት፣ ጠቅላላ አስተባባሪ ለሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሰርጆ ዳ ሮካ፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ምክትል ዋና ጸሐፊ ለሆኑት ለብጹዕ አቡነ ፋቢዮ ፋበን፣ የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አባላትና ለረዳቶቻቸው በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እንደዚሁም ለሲኖዶሱ አባቶች፣ ምሁራንና የተለያዩ ማሕበራት ተወካዮች፣ በትርጉም ሥራ ላይ ለተሳተፋችሁ፣ በመዝሙር አገልግሎት ለተሰማራችሁ፣ ለጋዜጠኞች፣ አነሰም በዛ ይህን ጉባኤ ለማዘጋጀት ተስትፎን ላበረከታችሁ በሙሉ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

ልባዊ ምስጋናዬን ለሁለቱ ልዩ ዋና ጸሐፊዎች፣ የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል ለሆኑት ለክቡር አባ ጃኮሞ ኮስታ እና ላሳሌዚያን ዶን ቦስኮ ማሕበር አባል ለሆኑት ለክቡር አባ ሮዛኖ ሳላ፣ በቸርነታቸው ላበረከቱት እገዛ ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

በተለያዩ የማሕበራዊ ሚዲያ በኩል በዓለም ዙሪያ ሆነው ይህን 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤን በቀጥታ በመከታተል ላይ የሚገኙትን ወጣቶችና ለዚህ የጳጳሳት ሲኖዶስ ድምጻቸው እንዲሰማ ያደረጉትን ወጣቶች በሙሉ አመሰግናለሁ። እነዚህና ሌሎች ወጣቶችም ቤተክርስቲያን የራሳቸው መሆኗን በመገንዘብ፣ ከእርሷ ጋር ለመነጋገር ወደ ውይይት ገበታ የመጡትን፣ እናታቸው መሆኗን አውቀው አስተማሪያቸው መሆኗን አውቀው፣ መኖሪያ ቤታቸው መሆኗን ተገንዝበው፣ ምንም እንኳን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ብትገኝም ከኢየሱስ ክርስቶስ በተቀበለችው አደራ መሠረት የወንጌልን መልካም ዜናን በዓለም ለማዳረስ ጥረት ላይ ከምትገኝ ቤተክርስቲያን ሥር ለመሆን ለፈለጉት፣ በዚህች ቤተክርስቲያን ሥር ሆነው እርስ በርስ ለመወያየትና ለመደማመጠ ፍላጎታቸውን ለገለጹት፣ እንቅፋቶችን ተቋቁመው ቤተክርስቲያን የምትሰጣቸውን ከፍተኛ እሴቶች እነርሱም የቤተሰብ ሕይወት፣ ታማኝነትን፣ ፍቅርን፣ እምነትን፣ መስዋዕትነትን፣ አገልግሎትንና ዘለዓለማዊ ሕይወትን ለመቀበል ምኞት ያደረባቸውን በሙሉ አመሰግናቸዋልው። በዚህ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ ሃላፊነታችን የሚሆነው ከወጣቶቻችን የሚቀርቡ አስተያየቶችን፣ ትችቶችን፣ ስሞታዎችንና አቤቱትታዎችን በሙሉ ማዳመጥ ስለሆነ ይህ ጊዜ በእውነቱ በጣም ውድ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።

እዚህ የተገኛችሁትን ወጣቶች በሙሉ በተለየ መልኩ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። ምክንያቱም በዚህ ጳጳሳዊ ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት ወቅት ያሳያችሁት ንቁ ተሳትፎ፣ ያለ እናንተ ተሳትፎ ምንም ማድረግ እንደማንችል በገሃድ አሳይቶናል። ይህ ንቁ ተሳትፎአችሁ በደስታና በተስፋ እንድንሞላ ስላደረገን አመሰግናለሁ።

ይህ ዛሬ የጀመርነው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሃሳቦቻችንን የምንጋራበት ምቹ መድረክ በመሆኑ ሁላችሁም በድፍረት፣ በንጻነት፣ በእውነትና በቸርነት መንፈስ ሆናችሁ እንድትናገሩ አደራ እላለሁ። ሊይሳድገን የሚችለው ውይይት ብቻ ነው። ግልጽነት ያለበት ትችት እንድናድግ ያግዘናል። ነገር ግን ፍሬ የሌለው ከንቱ ንግግር፣ ሐሜትና አሉባልታ ዋጋ የላቸውም።

በድፍረት መናገር በጽሞና ከማዳመጥ ጋር መሆን አለበት። በዚህ ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት ወቅት እንደተናገርኩት፣ የማይጥመኝ ሰው ሲናገር እንኳ ከልብ ማዳመጥ አለብኝ። ምክንያቱም ማንም ሰው የመናገር መብት እንዳለው ሁሉ እያንዳንዱ ሰው የመደመጥ መብት አለውና። ይህ በነጻነት የማዳመጥ ጥበብ፣ በመካከላችን የሌሉ ነገር ግን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶች ድምጽ በዚህ ሥፍራ እንዲሰማ ስለሚያደርግ ነው። እንግዲህ ይህ የማዳመጥ ጥበብ ካለ ፍሬያማ ውይይቶችን ማካሄድ እንችላለን። ይህ በመካሄድ ላይ ያለው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወይም ጉባኤ በተለይም በጉባኤው ለተገኙት በሙሉ መልካም የውይይት መድረክን የሚከፍት መሆን አለበት። የውይይቱ የመጀመሪያ ፍሬ የሚሆነው እያንዳንዱ የጉባኤው ተሳታፊ ሌሎችን በሚገባ በማዳመጥ፣ በልቡ የነበርውን ሃሳብ በማሻሻል አዲስ ሃሳብን ለመቅሰምም ሆነ ለማካፈል ሲችል ነው። ይህ ደግሞ ለዚህ ሲኖዶስ እጅግ አስፈላጊ ነው። አብዛኛዎቻችሁ በዚህ ጉባኤ በምታቀርቡት ሃሳብ ላይ ተዘጋጅታችሁበታል። ለዚህም አመሰግናችኋለሁ። ስለዚህ ይህን ሃሳባችሁን ከሲኖዶስ መካከል ከምታገኟቸው ሃሳቦች ጋር በማዛመድ፣ የሚጨመር፣ የሚቀነስ ወይም የሚሻሻል ሃሳብ ካለ እንድትመለከቱት አደራ እላችኋለሁ። ሰብዓዊ ጨዋነትና መንፈሳዊናትም በመሆኑ ሌሎችን ካዳመጡ በኋላ አቋምን ለመቀየርም ሆነ ለማዳመጥ ነጻነት ሊሰማን ይገባል።

ይህ ዛሬ የጀመርነው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሃሳቦቻችንን በጽሞና የምናስተነትንበት መንፈሳዊ መድረክም ነው። ይህ ሲኖዶስ ሃሳቦቻችንን ማስተውል በታከለበት መንገድ የምናስተነትንበት መንፈሳዊ መድረክ በመሆኑ በግልጽ መናገርና ማዳመጥ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ማስተውል በታከለበት መንገድ ማስተንተን በምንልበት ጊዜ ከሌሎች አስተንትኖች ሁሉ ልዩ የሚሆነው እምነት የታከለበትን ልባዊ ስሜትን ስለሚላበስ ነው። ጥበብ በታከለበት መንገድ ማስተዋል በራሱ አንድ ዓይነት ዘዴ ከመሆኑም በተጨማሪ  በዓለም ታሪክ ውስጥ፣ በሰዎች ሕይወት ውስጥ፣ በሚናገሩን ንግግሮች በኩል የእግዚአብሔር እቅድ እንዳለበት የምንገነዘብበት መንገድ ነው። ስለዚህ በምናዳምጥበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ምን እንደሚናገረን፣ የትኛውን አቅጣጫ እንደሚያመለክተን መመልከት ይኖርብናል። ጥበብ በታከለበት መንገድ ማስተዋል ቦታና ጊዜ ሊኖረው ይገባል። በመሆኑም የቡድን ውይይቶችን በምታደርጉበት ጊዜ የምታዳምጡትን ለማገናዘብ፣ ልባችሁን የማረከ ሃሳብ ከተገኘ ለማሰባሰብ እንዲያመቻችሁ ለሦስት ደቂቃ ያህል የጸጥታ ጊዜ እንዲኖራችሁ ያስፈልጋል። ይህ ውስጣዊ ትኩረት አንድን ሃሳብ ለማወቅ፣ ለመተርጎምና ለመምረጥ በጣም ጠቃሚ መንገድ ነው።

እኛ በጉዞ ላይ ያለችና የምታዳምጥ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ነን። የማዳመጥ ዝንባሌያችን በዚህ ጉባኤ መካከል የሚነሱ ሃሳቦችን በሙሉ ከማዳመጥ የሚገድበን መሆን የለበትም። ከብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት እንደተገነዘብነው ቤተክርስቲያን ወጣቶችን የማዳመጥ ዕዳ አለባት። ይህ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የምታዳምጥ ቤተክርስቲያን ምሳሌ የመሆን ሃላፊነትና ግዴታ አለበት። ቤተክርስቲያን ምዕመናኖችዋን የማታዳምጥ ከሆነ አዳዲስ ክስተቶችን መመልከት አትችልም። የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች መመልከት አትችልም። በምዕመናኖችዋ በተለይም በወጣት ልጆችዋ ዘንድ እምነት የላትም።

ከጭፍንና የተዛባ አመለካከቶች መላቀቅ አለብን። በማዳመጥ ሂደት የመጀመሪያው አቅጣጫ አእምሮአችንን ከተዛቡ አመለካከቶች ነጻ ማድረግ ነው። ስለ ሌላ ሰው ማንነት፣ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ስንፈልግ፣ ይህን ሰው በሙሉ ልብ ለማዳመጥ እንቸገራለን። በትውልዶች መካከል ያሉት ግንኙነቶች፣ ምንም እንኳን ባንገነዘባቸውም በጭፍንና የተዛቡ አመለካከቶች የተሞላ ነው። ወጣቶች አዛውንቶችን የበለጧቸው እንደሆነ ያስባሉ። አዛውንቶች ደግሞ ወጣቶችን እንደ አላዋቂ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይህ አመለካከት በትውልዶች መካከል የጋራ ውይይቶች እንዳይካሄዱ እንቅፋትን ሊፈጥር ይችላል። ወጣቶች አብላጫ ቁጥር ስላላቸውና የደረሱበትም የአስተሳሰብና የዕውቀት ደረጃ እያደገ በመምጣቱ ስለ ወጣቶች ስንናገር ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። ይህንን ከተረዳን በትውልዶች መካከል ያለውን ሕብረት ማጎልበት እንችላለን። አዛውንቶች በወጣቶች ላይ ያላቸውን የተዛባ አመለካከት ቢቀይሩ መልካም ይሆናል። ከክርስቶስ ልደት 3000 ዓመት በፊት የተጻፈውን ታሪክ እንዳነበብኩት፣ ወጣቱ ትውልድ ሥነ ምግባር የጎደለውና የሕዝቡንም ባሕል ከጥፋት መከላከል የማይችል ነው የሚል ነበር። ይህ ጊዜ ያለፈበት የአባቶች ንግግር ነው። ወጣቶችም በበኩላቸው አዛውንቶችን ከመናቅ ወይም ከማሳነስ ተቆጥበው፣ ያለ እነርሱ ጥረት አሁን የተደረሰበትን የኑሮ ደረጃ መድረስ እንደማይቻል መገንዘብ ያስፈልጋል። አዛውንቶች ከአካላዊ ድክመት ባሻገር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሥፍራ የሚሰጣቸው የሕብረተሰባችን የስልጣኔ መሠረት እንደሆኑ መዘንጋት የለበትም። ለአዛውንቶች የሚገባቸውን አክብሮት ካልሰጠናቸው፣ የማንንከባከባቸውና ብቻቸውን የምንተዋቸው ከሆነ በሕይወታቸው ላካበቱት ልምድ አድናቆትን ከመንፈግ አልፎ፣ መጭው ትውልድ ከልምድ ማጣት የተነሳ ራሱን በራሱ የሚያጠፋበትን መንገድ ይፈጥራል ማለት ነው. . . . . . . . ።

 

04 October 2018, 17:23