ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “መንፈስ ቅዱስ ራእይንና ተስፋን የምናደርግበትን ችሎታ ይሰጠናል”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ምእመናን፣ ዛሬ በቫቲካን የሚጀመረውን 15ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት መደበኛ ሲኖዶስ መክፈቻ ይሆን ዘንድ፣ ከበርካታ ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳትና ካህናት ጋር ሆነው መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል። ቅዱስነታቸው መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ መንፈስ ቅዱስ ራእይንና ተስፋን የምናደርግበትን ችሎታ ይሰጠናል ማለታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፣ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ. 14. 26)።

ይህን በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን ለአገልግሎት በላካቸው ጊዜ የተሰጣቸውን አገልግሎት በብቃት እንዲያከናውኑ የሚያግዛቸውን አስተማማኝ ሃይል እንድሚያገኙ ተስፋ ሰጥቶአቸዋል። አጥብቀው መያዝ፣ ማዳመጥና መከተል ያለባቸው፣ ሳይዘነጉ በልባቸው መያዝ  ያለባቸው የመጀመሪያው አጽናኙን መንፈስ ቅዱስ ነው። ምክንያቱም የማያልቅ ደስታ ምንጭ፣ ለአገልግሎት የሚያነሳሳ ሃይል የሚገኘው ከወንጌል መሆኑን የሚያረጋግጥላቸው መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ስለሆነ ነው። የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጸጋ በረከት የሆነውን 15ኛውን አጠቃላይ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ስንጀምር፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማዳመጥና በማስተዋል በድጋሚ በልባችን ውስጥ እንዲቀጣጠል የመንፈስ ቅዱስን እገዛ እንጠይቃለን። ለቅዱስ ወንጌል ቃል ያለን ጉጉትና ምኞት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ይመራናል። ተስፋን እንድናደርግና የገልግሎት ምኞታችን በውስጣችን እንዲጨምር የሚያደርገውን ሃይል የምናገኘው ከወንጌል ቃል ነው። ወጣቶቻችን የትንቢትና የራዕይ ችሎታ ሊኖራቸው የሚችለው እኛ ሽማግሌዎች ሕልም ስናልም፣ ጎልማሶችም ራዕይ ስናይ ነው።

እነዚህ የሲኖዶስ አባቶች በሙሉ መንፈስ ቅዱስ የተስፋንና የራዕይ በረከትን እንዲሰጣቸው እንለምናለን። በዚህም የተስፋና የራዕይ በረከት ወጣቶቻችንን በትንቢትንና በራዕይ ስጦታ መባረክ እንችላለን። በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያበቃ፣ በራሳችን ስንፍና፣ ስሕተትና ሐጢአት ምክንያት የሚቋረጥ ሳይሆን ዘላቂና ፍሬያማ የማስተዋል ጸጋን መንፈስ ቅዱስ አብዝቶ ይስጠን። ይህ የማስተዋል ስጦታ በልባችን ውስጥ በመቀጣጠል መንፈስ ቅዱስ የሚያሳየንን ትክክለኛውን አቅጣጫ ጥበብ በተመላበት አኳኋን እንድንገነዘብ ያድርገን። ከዓለም ዙሪያ በሙሉ ወደዚህ ሥፍራ የተሰበሰብነውም መንፈስ ቅዱስ የሚነግረንን ሁሉ በታዛዥነት ስሜት ለማዳመጥ ነው። ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሕዝባዊት ሪፓብሊክ ቻይና የመጡ ሁለት ብጹዓን ጳጳሳት በመካከላችን ይገኛሉ። እነዚህን ብጹዓን ጳጳሳት እንኳን ደህና መጣችሁ እንላለን። መላው የቻይና ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ከሆኑት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያላቸው ውህደትና አንድነት የበለጠ ግልጽ እየሆነ መጥቶአልና ይህን ለማረጋገጥ በዚህ ሥፍራ ከእኛ ጋር ስለተገኙ እናመሰግናቸዋለን።

በተስፋ በመሞላት ይህን አዲስ የቤተክርስቲያን ጉባኤ በሕብረት እንጀምር። ስለ ወጣቶች እንዳናስብ፣ እንዳንጨነቅ ከሚያደርገን፣ ለሃይለኛ የዘመናችን ማዕበል እንዲጋለጡ ከሚያደርግ አካሄድ፣ ሊንከባከቧቸው ከሚችሉ ክርስቲያናዊ ማሕበረሰብ ተነጥለው እንደ ወላጅ አልባ ልጆች እንዲኖሩ ሚያደር አካሄድ፣ የሕይወት ትክክለኛ ትርጉምና አቅጣጫን ከሚያስት አካሄድ ወጥተን የማሰብ አድማሳችንን እንድናሰፋ፣ የተዘጋ ልባችንን እንድንከፍት የሚያግዘንን ይህን የቤተክርስቲያን ጉባኤ እንጀምር (ከወንጌል የሚገኝ ደስታ ከሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቁጥር 49)።

ተስፋ፣ ቸልተኝነትንና ግድ የለሽነትን አስወግደን፣ ውጣቶች እስካሁን ያጋጠማቸውን፣ እያጋጠማቸው ያለውንና ወደፊትም ሊያጋጣሟቸው የሚችሉ ችግሮችን በጥንቃቄ እንድንመለከት ያደርገናል። ይህ ተስፋ፣ በወጣቶቻችን መካከል የሚታየውን ተስፋ የመቁረጥን፣ የልዩነትና የክፍፍልን፣ እንዲሁም የአመጽን ስሜት ለማስወገድ ያግዛል።

በርካታ ዕድሎችና ምርጫዎች መኖራቸውን የተገነዘቡት የዛሬው ወጣት ትውልድ፣ ለእድገታቸው እንቅፋት ሆነው የቆዩትን መሰናክሎች ተጋግዘን ማስወገድ እንዲቻል በማለት የእኛን እገዛ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ። ከእኛ የሚጠይቁትና የሚፈልጉት፣ በጭቆና ብዛት ሕይወታቸውን ወደ ሞት፣ ወደ ተስፋ ቢስነት እንዲሁም ወደ ጨለማ ወደ ሚዳርጉት እጅ እንድንተዋቸው ሳይሆን፣  በቆራጥነት፣ በፍላጎትና በጥበብ ተነሳስተን በሙሉ ተስፋ እንድናግዛቸው ነው።

በሕብረት የመሥራትን ምኞት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተክርስቲያን የሰጣት ስጦታ በመሆኑ፣ ሐዋሪያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ሰዎችን በመጀመሪያ መልዕክቱ እንደመከራቸው “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” (በምዕ. 2.4)። እኛ ደግሞ ከዚህም በበለጠ፣ በቁ. 3 ላይ እንደተገለጸው፣ ሌሎች ከእኛ እንደሚሻሉ በትሕትና በማሰብ እንጂ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴን ለማግኘት ብለን ማድረግ የለብንም። በዚህ መንፈስ የተነሳሳን ከሆነ እርስ በርስ በመደማመጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተክርስቲያኑ ምን እንደሚፈልግ ማገናዘብ እንችላለን። ይህ ደግሞ በቅድሚያ ለሌሎችም ማድረግ ያለብንን ተግባር ወደ ጎን በማድረግ ራሳችንን ብቻ ለማዳን ከምናደርገው ጥረት እንድንጠነቀቅ ይሳስበናል። የወንጌል ፍቅርና እንድናገለግላቸው የተጠራንበት የሕዝበ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ተልዕኮአችንን እንዳንዘነጋና አመለካከታችንን የበለጠ እንዳናሰፋ አደራ ይለናል። ይህን ካስደረግን ሁሉንም የሚጠቅም የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን። ይህ ካልሆነ ግን ጥረታችን በሙሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል።

በቅንነትና በጸሎት መንፈስ፣ ከተሳሳተ አስተሳሰብ ነጻ በሆነ መንገድ ሌሎችን እንድናዳምጥ የተሰጠን ስጦታ እውነተኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚኖሩትን ኑሮ እንድንጋራ ያደርገናል። እግዚአብሔርን የምናዳምጥ ከሆነ ከእርሱ ጋር ሆነን የሕዝባችንን ብሶትና ዋይታ መስማት እንችላለን። የሕዝባችንን ብሶትና ዋይታ የምንሰማ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር እንድናከናውን የሚጠይቀንን ሁሉ ከሕዝቡ ጋር በሕብረት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን።

በዚህ ሁኔታ፣ በተግባር የማይገለጡ ሃሳባዊ አመለካከቶችን ወደ ጎን በማድረግ፣ ለሕዝባችን ማድረግ የሚገባንን ተግባር እንዳናከናውን ከሚያደርገን የመውደቅ አደጋ ራሳችንን መከላከል እንችላለን። 

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ይህን የጉባኤ ጊዜን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእናታዊ ጥበቃዋ ፍሬያማ እንዲሆን ታደርግልን ዘንድ በጸሎት እንጠይቃታለን። የሚለምኑትን የምታዳምጥ፣ መንፈስ ቅዱስ የሚነግረንን መንገድ እንድንከተል፣ እርሱ የሚነግረንን እንድንሰማ በማገዝ በእነዚህ የጉባኤ ቀናት በሙሉ ከእኛ ጋር እንድትሆን በጸሎት እንጠይቃታለን። በተስፋችንና በመልካም ምኞታችን፣ ወጣቶቻችን የሚያስቡትንና የሚመኙትን ተጨባጭ እንዲያደርጉ እንርዳቸው፣ እናበረታታቸው።

ውድ የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች ሆይ፣

ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሲካሄድ ብዙዎቻችን ገና በወጣቶች የቤተክርስቲያን ሕይወት እንገኝ ይሆናል። የጉባኤው አባቶች የመጨረሻ መልዕክት የሚናገረው ስለ ወጣቶች ነበር። ደራሲው ፍሬድሪክ ሆልደርሊን በአንድ ወቅት “ሕጻን የተናገረው ነገር መረሳት የለበት” እንዳለው ሁሉ በወጣትነት ዕድሜአችን የሰማነውን ያንን የሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ መልዕክት በድጋሚ ብናስታውሰው የሚጠቅመን ይሆናል።

የጉባኤው አባቶችም ያስተላለፉልን መልዕክት ይህ ነበር፣ ላለፉት አራት ዓመታት ያህል ቤተክርስቲያን የእሷን ገጽታ በማነቃቃት፣ መስራቿና ሁል ጊዜ ወጣት ሆኖ ለዘለዓለም የሚኖረውን የኢየሱስ ክርስቶስ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። የቤተክርስቲያንን ሕይወት እንደገና ለማጤን ስትነሱ ቤተክርስቲያንም እናንተን ትመለከታችኋለች። ቤተክርስቲያን በዚህ ጉባኤ አማካይነት፣ እናንተ ወጣቶች ለወደፊት ሕይወታችሁ ተስፋ የሚሆናችሁን ብርሃን እንድታበሩ ትጠይቃችኋለች። እናንተ ወጣቶች፣ ልትገነቡትና ልታሳድጉት የምትሄዱበት ማሕበረሰብ ለሰው ልጅ ክብርና ነጻነት፣ ለእያንዳንዱ ሰው መብት ምን ያህል ታላቅ ዋጋን እንደሚሰጥ ቤተክርስቲያን መመልከት ትፈልጋለች። እያንዳንዳችሁ የምትባሉ እናንተ ናችሁ። እምነታችሁን ለሕይወት ትርጉም በሚሰጥ መንገድ በተግባር እንድትገልጹ ቤተክርስቲያን አደራ ትላችኋለች። በእግዚአብሔር መልካምነትና ፍትሃዊነት እርግጠኞች እንድትሆኑ ትፈልጋለች። በእግዚአብሔርና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ልባችሁን ለዓለም ክፍት በማድረግ በዚህ በወጣትነት ዕድሜአችሁ አገልግሎታችሁን እንድታቀርቡ እንጠይቃችኋለን። ስግብግብነትን አስወግዱ፣ ወደ ጦርነት የሚያደርሰውን የአመጽና የጥላቻ ስሜቶችን ከመካከላችሁ አስወግዱ። በቸርነት፣ በንጽሕና፣ በሰው አክባሪነትና በታማኝነት፣ ከዚህ በፊት ታላላቆቻችሁ ያልደረሱበትን የተሻለ ዓለም ለመገንባት ጥረት አድርጉ።         

ውድ የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች በሙሉ፣ መላዋ ቤተክርስቲያን በእምነትና በፍቅር ልብ እናንተን ትመለከታችኋለች”። 

03 October 2018, 17:25