ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ከባርነት ሁሉ የከፋ ባርነት፣ ራስ ወዳድነት ነው”።

“ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ፣

በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ ከአስርቱ ትዕዛዛት መካከል ወደ ሦስተኛው ትዕዛዝ በመመለስ ስለ ዕረፍት የሚናገረንን እንመለከታለን። በኦሪት ዘጸአት የተገለጸው በተመሳሳይ መልኩ በኦሪት ዘዳግም ላይም ተጠቅሶ እናገኘዋለን። ነገር ግን፣ ሊሰመርበት የሚያስፈልገው አንድ ልዩነት ቢኖር፣ በኦሪት ዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ የዕረፍት ቀንን አስመልክቶ የተገልጸው ሦስተኛው ቃል፣ የዕረፍት ቀን ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ለፍጥረት መባረክ የሚል ሲሆን ነገር ግን በኦሪት ዘዳግም ላይ፣ ዕረፍት ያስፈለገበትን ዋና ምክንያት ሲገልጽ፣ ዕረፍት ያስፈለገበት ምክንያት የባርነት ጊዜ በመገባደዱ ስለ ሆነ ነው በማለት ያስረዳል። በኦሪት ዘዳግም እንደተገለጸው በተወሰነው የዕረፍት ቀን፣ ጌታው እንዳደረገ ሁሉ ባሪያውም፣ የነጻነቱን ቀን ለማክበር ሲል ማረፍ አለበት።

በመሠረቱ በዚያን ጊዜ አገልጋዮች ወይም ባሪያዎች ማረፍ የለባቸውም ነበር። ነገር ግን ብዙ ዓይነት የባርነት ቀንበር በመኖሩ፣ እነርሱም የውስጥና የውጭ ባርነት ተብለው በሁለት የተከፈሉ ነበሩ። የውጭ ባርነት የምንላቸው እንደ ጭቆና፣ የፍትህ መጓደል፣ ጥቃትና ምርኮኝነትና ሌሎችም በደሎች ሲሆኑ፣ የውስጥ ባርነት የሚባሉት ደግሞ የስነልቦና መዘጋት፣ ውስብስብ የሆኑ የባሕርይ መገደብ እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል። ይህን በመሰለ ሁኔታ ላይ ላለ ሰው እረፍት አለ ወይ?  የታሰሩ ወይም የተጨቆኑ ሰዎች ነፃነት ተሰምቷቸው ሊኖሩ ይችላሉን?

በእርግጥም አንዳንድ ሰዎች በእስር ቤት ውስጥም እንኳ ሆነው የአእምሮ ነጻነት አግኝተው የሚኖሩ አሉ። ለምሳሌ ቅዱስ ማክሲሚሊያን ኮልቤ ወይም ካርዲናል ቫን ቷንን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ስቃይና ጭቆና የበዙባቸውን ሥፍራዎች ወደ ብርሃን የለወጡ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በውስጣቸው ትልቅ ውስጣዊ ችግር ያለባቸው፣ ነገር ግን የምህረት እረፍት እንዴት ማድረግ እንደሚቻልና ለሌሎችም ማስተላለፍ እንደሚቻል በትክክል የሚያውቁ ሰዎች አሉ።

ስለዚህ ትክክለኛውና እውነተኛው ነጻነት የቱ ነው? ምናልባትም ምርጫ ማድረግ ያስፈልግ ይሆን? በእርግጥ ምርጫን ማድረግ መቻል፣ የነጻነት አንዱ አካል ነው። ይህን የመሰለ ነጻነት ለእያንዳንዱ ሰው እንዲኖር ጥረት እናደርጋለን። የምንፈልገውን ሁሉ የማድረግ እና የማግኘት ነጻነት እውነተኛ ነጻነትንና ደስታን እንደማያስገኝ ጠንቅቀን እናውቃለን። እውነተኛ ነጻነት ከዚህ ሁሉ በላይ ነውና።

በእስር ቤት ውስጥ ከሚታይ ባርነት የበለጠ ባርነት አለ፣ ፍርሃትና ጭንቀት ከሚያስከትለው ባርነት የበለጠ ባርነት አለ፣ ማድረግ የማንፈልገውን ተገድደን እንድናደርግ የሚያደርግ ባርነትም አለ። ከእነዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ትክክለኛ የሆነውን መንገድ እንዳንጓዝ የሚያደርገን የክፋት ባርነት ነው። የክፋት ባርነት የሰውን ልጅ በደረሰበት ሁሉ የሚያሰቃይና የሚጎዳ ባርነት፣ ይህም ሐጢአት የሚባለው ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ ይህን አስመልክቶ እንደጻፈው፣  “ኢየሱስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባርያ ነው” (የዮሐንስ ወንጌል በምዕ. 8፤34)

ስግብግብነት፣ ሴሰኛነት፣ ምቀኝነት፣ ጨካኝነት፣ ቅናት፣ ተንኮል፣ ትዕብተኝነት፣ ስንፍና እነዚህ በሙሉ ወደ ሐጢአት ባርነት የሚወስዱ ናቸው። ስግብግብና ሴሰኛ በደስታ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው ምንም የለም፣ ምክንያቱም በጭንቀት የተያዙናቸውና። የቁጣ እሳትና ቅናት የሰዎችን መልካም ግንኙነት ያበላሻሉ። እነዚህ በሙሉ በደስታ ለመኖር የምናደርጋቸውን ጥረቶች ያዳክማሉ። ራስ ወዳድነትም ራስንና ሌሎችም የሚወድቁበትን ጥልቅ ጉድጓድ ያዘጋጃል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ስለዚህ እውነተኛ ባሪያ ማን ነው ትላላችሁ? የእረፍትን ትክክለኛ ትርጉም የማያውቅ ማን ነው ትላላችሁ? ሌላውን ማፍቀር የማይችል ሁሉ እርሱ እውነተኛ ባሪያ ነው። በነጻነት እንድናርፍ የሚጋብዘን ሦስተኛው ትዕዛዝ፣ እኛ ክርስቲያኖች የሰው ልጅን እንዳንወድ የሚያደርገንን ውስጣዊ ባርነት አውልቀን በመጣል የፍቅር አምላክ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ በትንቢት ይናገረናል። እውነተኛ ፍቅር፣ ከስግብግብነት ነጻ የሚያደርግ፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነትን የሚያጠናክር፣ ባልንጀራችንን እንድናውቅ የሚያደርግ፣ በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋትን  እያንዳንዷን ጥረት ወደ ደስታ በመለወጥ የጋራ ኑሮን እንድንኖር የሚያደርገን እውነተኛ ነጻነት ነው። ፍቅር በእስር ቤት ውስጥ ብንገኝ፣ ደካሞች ብንሆን፣ የተጨቅንን ብንሆንም ነጻ ያደርገናል

እውነተኛ ነጻነትን የምናገኘው፣ የባርነት ልባችንን በፍቅር ከሚለውጥ፣ በማዳን ሥራው ከሚያሸንፍ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እጆቹንና እግሮቹን በሚስማር ወግተው ባሰቃዩት ጊዜም ወዶናል፣ በፍርሃት ተውጠን ሳለ በድፍረት እንድንወጣ አድርጎናል። እውነተኛ ነጻነትን ሰጥቶናል። እያንዳንዳችን ከኢየሱስ ክርስቶስዘንድ ነጻ የሚያደርገንን እረፍት፣ ምሕረትንና እውነትን ማግኘት እንችላለን”።  

12 September 2018, 17:32