ፈልግ

Papa e lavoratori Papa e lavoratori 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንጹሕ ገንዘብ የሚገኘው በሥራ እንደሆነ አስገነዘቡ።

በእያንዳንዱ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በስተጀርባ የሰው ልጅ እንዳለ መዘንጋት የለበትም ያሉት ርዕሠ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ኤኮኖሚ ስናስብ ለሰው ልጅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ምክንያቱንም ሲገልጹ ሰብዓዊ ክብርን የሚሰጥ ሥራ እንጂ ገንዘብ አይደለም ብለው ሥራን የሚያከናውን ሰው ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ ከሚታተም “ሶለ 24 ኦረ” ከተባለ ዕለታዊ የንግድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ሰፋ ባለ ቃለ ምልልሳቸው ኤኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃን፣ የስደተኞችን ጉዳይ፣ የአውሮፓ አገሮችንና ሰላምን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ በማሕበራዊ ኤኮኖሚ ዙሪያ የጋራ ጥቅሞች ላይ ያተኮረ እንደነበር ታውቋል። በዚህ ቃለ ምልልስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እያንዳንዱ ሰው ለማህበራዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽዖ ሳይዘነጋ ነገር ግን አንድ ማሕበረሰብ የሚያድገው እንደ አንድ ሕዝብ እንጂ በተናጠል እንዳልሆነ ገልጸው ማሕበራዊ ሕይወት የሚለካው በግለሰቦች ስብስብ ሳይሆን በሕዝቦች የጋራ እድገት እንደሆነ አስረድተዋል።

እውነተኛ ማሕበራዊ እድገት፣

በማሕበረሰብ መካከል እውነተኛ እድገት ሊመጣ የሚችለው የእያንዳንዱ ሰው አስተዋጽዖ ሲታከልበት ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ እድገትም በሰዎች መካከል ሊኖር በሚገባው ዘላቂ ርኅራኄ እና ምሕረት እንጂ ልዩነትንና ብክንነትን ሊያስከትል በሚችለው ስኬት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን የለበትም ብለዋል። ብክንነት ምን ማለት እንደሆነ ቅዱስነታቸው ሲያስረዱ ብክንነት ሰዎችን መበዝበዝና መጨቆን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የጊዜአችን አዲስ ክስተት ነው ብለዋል። ልዩነትን ፈጥሮ ማግለል ሰዎችን አቅምንና ሐብትን ማሳጣት ብቻ ሳይሆን ከማሕበራዊ ኑሮ ሙሉ በሙሉ መነጠል እንደሆነ አስረድተዋል።

ለሰዎች ተስማሚ የሆነ ሥነ ምግባር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሰዎች ተስማሚ የሆነ ሥነ ምግባር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ይህ ማለት ደግሞ የሰዎችን የተሳሳተ አስተሳሰብን ለመቀየር የሚያግዝ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። ለሰዎች ተስማሚ የሆነ ሥነ ምግባር፣ ትርፍን ብቻ በሚያስብ ተቋምና ትርፍን በማያስቀድም ተቋም መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚያስችል አስረድተዋል። በእያንዳንዱ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በስተጀርባ የሰው ልጅ እንዳለ መዘንጋት የለበትም ያሉት ርዕሠ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ኤኮኖሚ ስናስብ ለሰው ልጅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ምክንያቱንም ሲገልጹ ሰብዓዊ ክብርን የሚሰጥ ሥራ እንጂ ገንዘብ አይደለም ብለው ሥራን የሚያከናውን ሰው ነው ብለዋል። በማከልም ገንዘብና የንግድ ትርፍ የሚገኘው የሥራ ዕድልን ለመፍጠር በማይችለው የኢኮኖሚ ስርዓት ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል።

ለሰው ልጅ ቅድሚያ ይሰጠው፣

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል የኤኮኖሚ ሥርዓት ለገንዘብ ቅድሚያን ቢሰጥም፣ ሕዝብንና ቤተሰብን ማዕከል ባደረገ ሥርዓት መቃወም ይቻላል ብለዋል። ትላልቅ የማምረቻ ተቋማት የሚያመርቱት ምርቶች ለመላው ማሕበረሰብ አገልግሎት በሚዉሉበት ጊዜ ለማምረቻ ተቋሙ ትርፍን ከማስገባት ይልቅ ረጅም ዕድሜ እንዲኖረው ለማድረግ ጥሩ ይሆናል ብለዋል። ጤናማ ኤኮኖሚ ከምርት ውጤት ጥራትና ከኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሊነጥል አይችልም ያሉት ቅዱስነታቸው ጤናማ ኤኮኖሚ ሁል ጊዜ በመልካም ሥነ ምግባር የታገዘ ነው ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዎ 13ኛን አስተምህሮን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነጻ ገበያ በራሱ ፍትሕን ለማምጣት በቂ አይደለም። ነገር ግን ነጻ ገበያ፣ ነጻ ገበያ ሊባል የሚችለው ከማህበራዊ ፍትህ ጋር በሚጣጣምበት ጊዜ ብቻ ነው ብለዋል።

ሥራ እና ሰብዓዊ ክብር፣

በብዙ ሰዎች ዘንድ፣ እያደገ የመጣው የሥራ ጫና እንደ ከባድ ሸክም ሆኖ ስለመቆጠሩ ሃሳባቸውን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማንም ቢሆን ሥራ ከማጣት ይልቅ ሥራ እንዲኖረው ይፈልጋል ብለው ሥራ ከሰብዓዊ ክብር ጋር የተያያዘ፣ የራስንና የሌሎችንም ሃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል በመሆኑ ሥራ አስፈላጊ ነው ብለዋል። በማከልም የሥራ ትልቁ መንፈሳዊ ትርጉም የሚገኘው በሥራ አማካይነት ለፍጥረት አክብሮትን በመስጠት እንዲቆይ በማድረጋችን ነው ብለዋል።

የአካባቢ ጥበቃ፣

የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ፣ ከዚህ በፊትም እንዳሳሰቡት ሁሉ ኩባንያዎች ለጋራ ጥቅም በሚያደርጉት ጥረት ለአካባቢ ጥበቃ ጥንቃቄን እንክብካቤን እንዲያደርጉ አሳስበው አብዛኞቹ ኩባንያዎች የባለሙያና የቴክኒክ ሥልጠና በመስጠት የሚሰጡትን አስተዋጽዖ አስታውሰው ከዚህም በተጨማሪ እሴቶችንም በመጠበቅ ተመሳሳይ አስተዋጽዖን እንዲያደርጉ አሳስበዋል። የአካባቢን ጥበቃ በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ የሰው ልጅ የደረሰበት የስልጣኔ ደርጃ የጋራ ቤታችን ከሆነው ምድር በተጨማሪ ሌላ አዲስ ፕላኔት ለመቆጣጠር እንደሆነ አስታውሰው የሰው ልጅ ከአሁን ወዲያ ምድርን የሚጠብቅና የሚንከባከብ ሳይሆን የሚያወድም እየሆነ መጥቷል ብለዋል። ስለ አካባቢ ጥበቃ አንስተን በምንናገርበት ጊዜ ሁሉ ስለ ሰው ልጅ የምንናገረውም ለዚህ ነው ብለዋል።  

የአካባቢያዊ መራቆትና የሰው ልጅ ሕይወት አንድ ላይ መታየት አለባቸው ያሉት ቅዱስነታቸው፣ የሥነ ምሕዳራዊ አስተሳሰባችን መልካም የወደፊት መልካም ሕይወትንና የጋራ እድገትን ለማምጣት እንዲሁም በሕዝቦች መካከል እኩልነትን ለማምጣት ያለመ መሆን አለበት ብለው ውዳሴ ላንተ ይሁን በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ የጠቀሱትን ታዳሽ ያልሆኑ ዕቃዎች አጠቃቀም መጠን መወሰን፣ የፍጆታ መጠንን በልኩ ማድረግና መልሶ ጥቅም ላይ መዋልን ባሕል ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ስደት

ስደተኞችንና ስደተኞች በብዛት የሚወጡባቸውን አገሮች አስመልክተው የተናገሩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ አገር ውስጥ ያለውን ብዝሃነት፣ የጋራ አንድነትንና ቤተሰባዊነትን በደስታ ካልተቀበሉ በስተቀር የተረጋጋ ሰላም ሊገኝ አይችልም ብለዋል። በማከልም ተስፋ የተሰደዱትንና ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱትን አንድ፣ ሕይወትንም በጋራ እንዲቋደሱ ስለሚያደርግ ተስፋ ቢሶች መሆን የለብንም ብለው ስለ ስደተኞች ብዛት ከምናወራ ስለ ስብዕናቸው ብናወራ ይሻላል ብለዋል።

አውሮጳ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢጣሊያ ከሚታተም “ሶለ 24 ኦረ” ከተባለ ዕለታዊ የንግድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ሰፋ ባለ ቃለ ምልልሳቸው  አውሮጳ ተስፋ ያስፈልጋታል ገልጸዋል። ስለ ተስፋ የምንሰጠውን ምስክርነት ፈጽሞ ማቋረጥ የለብንም ብለዋ የምስክርነታችንን አድማስ ማስፋት እንጂ በዘመናችን ለሚታዩት አስጨናቂ ችግሮች እጅ መስጠት የልብንም ብለዋል። የስደተኞችን ጉዳይ በድጋሚ በማንሳት የተናገሩት ቅዱስነታቸው ስደተኞች የሚገኙበትን አገር ባሕልና ሕግ ማክበር እንዳለባቸው አሳስበው ይህን አድርገው ከተገኙ ፈጽሞ ስጋትና ፍርሃት ሊይዛቸው አይችልም ብለዋል። በማያያዝም የአውሮጳ መንግሥታት ሃላፊነትን በመውሰድና አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት እርዳታን የሚጠይቁ ስደተኛ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በክብር ተቀብለው እንዲያስተናግዱ አደራ ብለወኣል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በቃለ ምልልሳቸው ማጠቃለያ ላይ ዘንድሮ በተከበረው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን ያስተላለፉትን ምልዕክት በማስታወስ፣ በተግባር ሊተረጎሙ የሚያስፈልጉ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን እነርሱም ለስደተኞች መልካም አቀባበልን፣ ጥበቃን፣ በማሕበረሰቡ መካከል ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግንና ከሕብረተሰቡ ጋር አብረው የመኖር ባሕልን ማሳደግ እንደሆኑ አስረድተዋል። እነዚህ ውጥኖች በፍቅር፣ በጽኑ ዓላማና በድፍረት ማከናወን ያስፈልጋል ብለው ግባችንም ሰላምን መገንባት ይሁን ብለዋል። ይህም ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ዕቅዶች በግድ የለሽነት ያለ ውጤት እንዳይቋረጡ ያግዛል ብለዋል።               

07 September 2018, 17:00