ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ለአፍሪቃ ወጣቶች እንጸልይ”!

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የመስከረም ወር የአፍሪቃ ወጣቶችን በጸሎት የምናስታውስበት ወር እንዲሆን በማለት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት የቪዲዮ ምስል መልዕክታቸው አሳስበዋል። መላው ምዕመናን በጋራ በመሆን የአፍሪቃ ወጣቶች ድንቁርናን፣ ድህነትንና ስደትን ለማስቀረት እንዲችሉ በትውልድ አገራቸው የትምህርት፣ የስልጠናና የሥራ እድል እንዲያገኙ የሚያደርግ መንገድ እንዲመቻችላቸው በጸሎታችን እንድናግዛቸው አደራ ብለዋል። ለአፍሪቃ ወጣቶች የትምህርት ዕድልን ማመቻቸት ለአህጉሪቱ ትልቅ ሐብት ይሆናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም አፍሪቃ በተፈጥሮ ሃብት ይሁን በሰው ሀይል መጠን ሐብታም አህጉር ነው ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የወጣቶች የመማር መብት የተጠበቀ ነው ብለዋል። በማከልም ለወጣቶች ሁለት ምርጫ እንዳላቸው አስገንዝበዋል። እነዚህም በድንቁርናና በድህነት መሸነፍ ወይም ራስን ከእነዚህ ችግሮች ለማውጣት በዕውቀት ማሳደግ ነው ብለዋል። ለአፍሪቃ ወጣቶች የወደ ፊት ሕይወታቸው የተስተካከለ የሚሆነው ራሳቸውን በዕውቀት ያዘጋጁ እንደሆነ ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሥራ ድርጅት እ. አ. አ. አቆጣጠር በ2017 ዓ. ም. ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪቃ አገሮች፣ ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች ሥራ አጥ እንደሆኑና ይህም ከመቶ 12.9 እንደሆነ ይፋ አድርጓል። እንደዚሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት እ. አ. አ. አቆጣጠር በ2017 ዓ. ም. ባወጣው ሪፖርቱ ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪቃ አገሮች፣ ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 17 ዓመት የሆናቸው ወጣቶች ምንም ዓይነት የትምህርት ዕድል እንዳላገኙ ገልጿል።

05 September 2018, 17:31