ፈልግ

2018.08.08 Bartolomeo I Patriarca 2018.08.08 Bartolomeo I Patriarca 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመድረስ፣ የማስተዋል ስጦታ ሊኖር ይገባል”።

በእውነተኛ የማስተዋል ጥበብ፣ የእግዚአብሔር እቅድ እርሱ በፈለገው ጊዜ የሚከናወን እንጂ የራሳችን አለመሆኑን በመረዳት በትዕግስት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከዛሬ ነሐሴ 30 ቀን - ጳጉሜ 3 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ 26ኛውን ዓለም አቀፍ የኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ጉባኤያቸውን በኢጣሊያ ቦሰ ከተማ በማካሄድ ላይ ለሚገኙት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች መልዕክት መላካቸው ታውቋ። ቅዱስነታቸው ለተለያዩ የሐይማኖት አባቶች በላኩት የቴለግራም መልዕክታቸው እንደገለጹት ወደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመድረስ ማስተዋል ሊኖር እንደሚያስፈልግ ገልጸው ለዚህም ራስን ማዘጋጀትና እግዚአብሔር የወሰነውን ጊዜ በትዕግስት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በእውነተኛ የማስተዋል ጥበብ፣ የእግዚአብሔር እቅድ እርሱ በፈለገው ጊዜ የሚከናወን እንጂ የራሳችን አለመሆኑን በመረዳት በትዕግስት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስን የቴለግራም መልዕክት ተቀብለው 26ኛውን ዓለም አቀፍ የኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት የአብያተ ክርስቲያናት አባቶች የላኩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መሆናቸው ታውቋል። ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘ የቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋዜጣ ትናንት በወጣው እትሙ እንደገለጸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለጉባኤው ተካፋዮች ከላኩት መልዕክት ጋር ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውንም እንደላኩ ገልጾ፣ የጉባኤው ተካፋዮች በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሚያደርጉት የወንድማማችነት ውይይት በግልና በጋራ ሆነው በሚያደርጉት ጥበብ በተመላበት የማስተዋል መንገድ በመታገዝ ሙሉ ሕይወት የሚገኝበትን የእግዚአብሔር እቅድ ወደማወቅ እንደሚደርሱ ያላቸውን እምነት ገጿል።  

በጥበብ የተሞላ ማስተዋልና ሕይወት፣

ከዛሬ ነሐሴ 30 ቀን - ጳጉሜ 3 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ ለ26ኛ ጊዜ በመካሄድ ላይ ያለው ዓለም አቀፍ የኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ጉባኤ ዋና ርዕስ “በጥበብ ማስተዋልና የክርስትና ሕይወት” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ይህ ርዕስ በዘመናችን በተለይም ከኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ጋር ለሚካሄዱት የወዳጅነት ውይይት ቀዳሚ ርዕስ እንደሆነ ይነገራል። የጊዜውን ምልክቶችን ተመልክቶ መገንዘብ መቻል ለክርስትና ሕይወት እና ለክርስትያን በሙሉ መሠረታዊ በመሆኑ ይህን በሚገባ በመገንዘብ በማይናወጥ እምነት ላይ ቆሞ በዘመናችን ለሚነሱ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት የሚስችል ጥበብ ከጉባኤው እንደሚቀሰብ ተስፋ ተጥሎበታ ተብሏል። ይህን ተስፋ በማድረግ ዛሬ በተከፈተው ጉባኤ ላይ ከተገኙት የዓለም አቀፍ አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ልኡካን መካከል በኢጣሊያ የቦሴ መነኮሳት ገዳም ምስራች የሆኑት ክቡር አባ ኤንዞ ቢያንኪ፣ የኦርቶዶክስ ቤተክርሲያን ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢሪነ፣ ስለ ቅዱሳት ምስጢራት መጽሐፍ ቅዱስንና የቤተክርስቲያንን ታሪክ መሠረት ያደረጉ ጽሑፎችን እንደሚያቀርቡ ታውቋል።

በአቅምና በሐጢአት ላይ ማስተንተን፣

በጉባኤው ላይ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ጉዳይ ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ የተገኙ ሲሆን እርሳቸው ለጉባኤው ተካፋዮች በሚያቀርቡት በሦስት ርዕሶች ላይ መልዕክት የሚያካፍሉ እንደሆነ ታውቋል። እነዚህ ሦስቱ ርዕሶችም መንፈሳዊ የማስተዋል ጥበብ፣ ስነ መለኮታዊ የማስተዋል ጥበብና ሐዋርያዊ የማስተዋል ጥበብ የሚሉ እንደሆኑ ታውቋል። በእነዚህ መልዕክቶች ላይ በመመርኮዝ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ እንደተናገሩት፣ ቅዱስ ቶማስ የኢየሱስ ክርስቶስ የጎን ቁስል በጣቱ በመንካት እንዳመነ ሁሉ በክርስቲያኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነትና ቁስል የቱጋ እንደሆነ በእምነት በማታገዝ መፈለግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የክርስቲያኖችን አንድነት የሚያራምዱ የቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተለሜዎስ አንደኛ በመልዕክታቸው  ጥበብ በተሞላበት አኳኋን ማስተዋል ለቤተክርስቲያን ሕይወት መሠረታዊ እንደሆነ ተናግረው ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሠረታት ቤተክርስቲያን ውድ ስጦታ እንደሆነ አስረድተዋል። ቤተክርስቲያን ለዓለም የምትሰጠውን ምስክርነት በሁሉም ዘርፍ የሚያሳድግ መልካም ምግባር እንደሆነ በማከል አስረድተዋል። በጥበብ ማስተዋል ብቻ አይደለም ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ በርተለሜዎስ አንደኛ፣ የአቅማችንን መጠንና ሐጢአታችንን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በጥበብ ማስተዋልና የወንጌል ተልዕኮ፣

የቁንስጥንጢንያው ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ በርተለሜዎስ አንደኛ፣ የመልዕክታቸውን ይዘት በአጭሩ ሲገልጹት፣ “ጠቅላላው የቤተክርስቲያን ሕይወት በማስተዋል የታገዘ ነው” ብለዋል። በዚህም በመታገዝ በዘመናችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚጠይቀንንና እርሱን ደስ የሚያሰኝ እውነተኛዉን ምስክርነት መስጠት እንችላለን ብለዋል። በታላቁ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት ጳጳሳዊ ሲኖዶስ እንደተገለጸው ለዓለም የሚሰጥ የወንጌል ምስክርነት ተልዕኮ በሰላማዊ መንገድ፣ በነጻነትና በተለያዩ ባሕሎችና ሕዝቦች መካከል በፍቅር መከናወን ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን ለማድረግ በእርግጥም በአብያተ ክርስቲያናት መካከል፣ ክርስቲያን ካልሆኑ ወገኖችና ተመሳሳ የአንድነት ዓላማ  ካላቸው ተቋማት ጋር የሚደረግ ውይይት ጥበብንና ማስተዋልን በተከተለ መንገድ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የህሊናን እድገት የሚጻረር፣

በኢጣሊያ ውስጥ በቦሰ የተጀመረው የቤተክርስቲያናት አባቶች ጉባኤ፣ ለእያንዳንዱ ክርቲያን ወገንና ለሚኖርበት ሕብረተሰብ አዲስ ጉልበትን በመጨመር፣ መሠረታዊና ትክክለኛ የሆኑ የመንፈሳዊ እድገት መንገዶችን በማሳየት ትልቅ አስተዋጽኦን እንደሚያበርከት ተስፋ እንደተጣለበት የሞስኮ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ክሪል፣ በሊቀ ጳጳስ በብጹዕ አቡነ ሂላሪዮን በላኩት የቴለግራም መልዕክት አስታውቀዋል። ፓትሪያር ኪሪል በመልዕክታቸው እንደገለጹት ከዚህ በፊት የተከናወኑ ታላላቅና መንፈሳዊነትን የተላበሱ በጥበብ የማስተዋል ጉቤዎች እንዳስገኙት ውጤት ሁሉ ሰዎች በራሳቸው ፈቃድ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲኖሩ በማገዝ፣ በክፋት መንገድ ሳይታለሉ፣ ህሊናን የሚጻረሩ የዘመናችንን አደጋዎች ለማለፍ ያግዛል ብለዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ኪሪል በመልዕክታቸው፣ እያንዳንዱ ሰው መጠነ ሰፊ በሆን የመረጃ መረብ ውስጥ በመግባቱ ምክንያት ራሱን ወደ የት መምራት እንዳለበት የሚቸገር መሆኑን ገልጸው ይህም ከክርስትና አስተምህሮ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ወደ ፈተና ውስጥ እንደሚከት አስረድተዋል።

የአብያተ ክርስቲያናት ሕብረት አስፈላጊነት፣

በዘመናችን የቤተክርስቲያን ቀዳሚ ተልዕኮ መሆን ያለበት መልካምን ከክፉ፣ እውነትን ከውሸት፣ ዘለዓለማዊውን ከጊዜያዊ ነገር ለይቶ ማወቅ እንዲችል ወጣቱን ትውልድ ማስተማር እንደሚያስፈልግ ፓትሪያር ኪሪል በመልዕክታቸው አሳስበዋል። ይህን የምናደርግ ከሆነ ለአብያተ ክርስቲያናት አንድነት የሚጠቅም መልካምሥራን በጋራ ለማከናወን፣ ወንጌልንም ለዓለም በጋራ መመስከር እንችላለን ብለዋል። ለዚህ ጉባኤ መልዕክታቸውን ከላኩት መካከል የሮማንያው ብጹዕ ፓትሪያርስ ዳንኤል፣ ከአሌሳንድሪያ የግብጽ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቴዎድሮስ ሁለተኛ፣ የኬቭ ሊቀ ጳጳስ ኦኑፍሪ ሲሆኑ የአንግሊካን ቤተክርስቲያናት ሕብረት መሪ፣ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ወልቢ ይገኙባቸዋል።  የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጃስቲን ወልቢ በመልዕክታቸው እንደገለጹት ክርስቲያኖች በሙሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው የሕይወት መንገድ ለመኖር ስንሞክር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመኖር ቆራጥ ውሳኔን ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በጥበብ የማስተዋል ስጦታ ሊኖረን ይገባል ብለዋል።    

05 September 2018, 18:52