ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የወንድሞቻችንን ስቃይ እያየን እንዳላየ፣ እየሰማን እንዳልሰማ መሆን የለብንም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በትናንትናው ዕለት እሑድ ጳጉሜ 4 ቀን 2010 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናንና የሃገር ጎብኝዎች በዕለቱ ከማርቆስ ወንጌል ምዕ. 7፤ 31-37 ተውስዶ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ ማቅረባቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ ግርማቸው ተስፋዬ - ቫቲካን

“በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ

ዛሬ በማርቆስ ወንጌል በምዕ. 7. 31-37 የሰማነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በኣንድ መስማትና መናገር በተሳነው ሰው ላይ ስላደረገው ተኣምር ይናገራል። ሰዎቹም ወደ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ያመጡት እንዲጸልይለትና እጁንም እንዲጭንበት በዚሀም ሁኔታ እንዲፈውሰው ነው። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን በዚሁ መስማትና መናገር በተሳነው ሰው ላይ የተለያዩ ምልክቶችን ኣደረገ።

ከሁሉ በማስቀደም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰውዬውን ከሰዎቹ ለይቶ ወሰደው ይህም የሚያስገነዝበን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ ሌሎቹ ጊዜያቶች ሁሉ የሚሰራዉን ሥራ በጥበብ ይሠራል ይህንንም በሚያደርግበት ጊዜ ሰዎችን ለማስደመም አይፈልግም ተወዳጅነትን ትልቅ ዝና ወይም ስኬት ለማግኘት ኣይፈልግም የሱ ዓላማ ለሰዎች መልካም ነገር ማድረግ ብቻ ነው። በዚህም ኣኳሃን መልካም ሥራ በብዙ ሆሆታና እልልታ ጡሩምባ እየተነፋ በእዩኝ ባይነት ሳይሆን በተረጋጋና ጸጥታ በሰፈነበት መልኩ እንድሚከናወን ያስተምረናል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰውዬውን ከሰዎቹ ለይቶ ከወሰደው በኃላ እጁን በሰውዬው ጆሮ ኣስገባ እንዲሁም እንትፍ ብሎ የሰውዬውን ምላስ ዳሰሰ ይህም ክስተት የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው የመሆን ምሥጢር ያስታውሰናል የእግዚኣብሔር ልጅ ወደ ሰው የመሆን እዉነታ ውስጥ መግባቱንና ፍጹም ሰው የመሆኑን ምሥጢር ይገልጥልናል። ይህም ስለሆነ የሰዎችን ችግርና ሥቃይ በመመልከትና በመረዳት በተለያየ መልኩ የችግራቸውና የስቃያቸው ተካፋይ ይሆናል።

በተመሳሳይ መልኩ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ተአምር የሚያደርገው ከአብ ጋር ካለው ጥብቅ ትስስር መሆኑን በግልጽ እንድንረዳ ይፈልጋል። ይህንንም ለማስረገጥ ወደ ሰማይ ተመለክቶ ቃተተና ከዚያም "ኤፍታህ" የሚል ቃል ተናገረ ትርጉሙም "ተከፈት" ማለት ነው ከመቅጽፈትም ሰውዬው ተፈወሰ ጆሮውም ተከፈተ ምላሱም ተፈታ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህ በእርሱ የተፈፀመው ተዓምር ለሌሎች ሰዎችና እና በዓለም ላይ ላሉ ችግሮች ሁሉ እንደ ተልቅ ተስፋ ይቆጠራል።

ይህ የወንጌል ዘገባ ሁለት ዓይነት ፈውስ እንደሚያስፈልግ ያመላክታል በመጀመሪያ ደረጃ ምንም እንኳን የሰውን ልጅ ሕመምና ሥቃይ ለማስታገስ ብሎም ካለበት ሥጋዊ ሥቃይ ለመፈወስ በሳይንስና በህክምና ረገድ ብዙ ጥረት ቢደረግም በዉጤቱም ልክ እንደሚፈለገው ሙሉ በሙሉ የተሳካ ነው ሊባል ባይችልም እንኳን ከበሽታ እና ከአካላዊ ሥቃይ ማስታገስና የሰውነትን ጤና ማደስ ሲሆን። ሁለተኛው ፈውስ ደግሞ ምናልባትም የበለጠ ከባድና ኣሳሳቢ የሆነው የፍርሃት ፈውስ ነው።

ሕመምተኞችን አካል ጉዳተኞችን ችግረኞችን የማግለሉ ጉዳይ ከውስጣዊ ፍርሃት የሚመነጩ ባሕሪዎች ሲሆኑ እነዚህም ባሕርያት በተለያዩ የማግለል ዓይነቶች ይገለፃሉ። ለምሳሌ ያህልም ሕመምተኞችን አካል ጉዳተኞችን ችግረኞችን በችግራቸው ተሳታፊ ኣለመሆንና ርኅራሄ ኣለማሳየት ትዕግሥትን ኣለማድረግ በምንችለው ሁሉ ኣለመርዳት ልክ ዱዳና ደንቆሮ እንደመሆን ይቆጠራል። በእርግጥ ህመምተኞችና የእነርሱም ስቃዮች ሊከብዱን ይችሉ ይሆናል ሆኖም ግን እኛ ለእነሱ ያልንን ፍቅርና ወንድማማችንት የምንገልፅበት እንደ ልዩ ኣጋጣሚ ልንወስደዉና ልናገለግላቸው ይገባል።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኤፋታህ ወይም ተከፈት በማለት የሰውዬውን ጆሮና ምላሱን የፈታበትን የዛሬውን ተዓምር ምስጢር የገለፀልን እኛም በተለያዩ ኣጋጣሚዎች የእርሱን ኣብነት በመከተል ለሌሎች ጆሮና ምላስ መከፈትና ለተለያዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች እንዲሁም መፍትሔ ሰጪዎች እንድንሆን ነው። ይህም ማለት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ላሉ ወድሞቻችናና እህቶቻችን የተዘጋውን ልባችንንና ራስወዳድነታችንን በማሸነፍ ከችግራቸው እንድንታደጋቸው ነው። ለዚህም ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከእግዚኣብሔርና ከሌሎች ወድሞቻችናና እህቶቻችን ጋር የጠበቀና መልካም ግንኙነት እንዳይኖረን ጋሬጣ የሆነብንን ልባችን ሊከፍትልን ወደ ምድር የመጣው።

ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው የሆነው ይህ በኃጢኣት ምክንያት ውስጣዊ ልቡ ደንቁሮና ድዳ የሆነው የሰው ልብ የእግዚኣብሔርን የፍቅር ቃል እንዲሰማና በልቡ እንዲያስቀምጥ ከዛም በኃላ በራሱ ጊዜ የሰማዉን ይህን የእግዚኣብሔርን የፍቅር ቃል በታላቅ ርኅራሄና ራሱን ለዚህ ኣገልግሎት ሙሉ በሙሉ በመስጠት በሕይወቱ በተግባራዊ እንዲያደርገው ለማገዝ ነው።

ለእግዚኣብሔር ኣምላክ ራስዋን ሙሉ በሙሉ ክፍት ያደረገች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እናታችን ይህ ሙሉ በሙሉ የመከፈት ምሥጢር በየዕለቱ በዕምነታችን ውስጥ እንድንረዳና በዚሁም ኣማካኝነት ከእግዚኣብሔርና ከወንድሞቻችን ሁሉ ጋር በሰላምና በፍቅር እንድንኖር ታማልደን”።

10 September 2018, 17:19