ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ወጣቶች ልባቸውን በመክፈት ለእግዚአብሔር ጥሪ መልስ መስጠት ያስፈልጋል”።

ሌሎችን በመርዳት ደስታን የምናተርፍ ከሆነ የማይጠፋ ደስታም እግዚአብሔር እርሱ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም ብለዋል። ስለዚህ ወጣቶች ዘወትር እግዚአብሔርን መሻት ማቋረጥ እንደማያስፈልግና ራስን ለአገልግሎት በማዘጋጀት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሚችሉት ሁሉ ከማድረግ እንዳይቆጠቡ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ወደ ደብቡ ኢጣሊያ፣ ፓለርሞ ከተማ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ከሀገረ ስብከቱ ወጣቶች ጋርም መገናኘታቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት መደሰታቸውን ገልጸው ለወጣቶቹ ንግግር ማድረጋቸውና ከወጣቶች ዘንድ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተውባቸዋል። ወጣቶቹ እግዚአብሔርን በሙሉ ልብ እንዴት ማዳመጥ እንችላለን ብለው ለጠየቋቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ እግዚአብሔርን ማዳመጥ የሚቻለ በሕይወት ጉዞ መካከል ነው፣ ከሁሉም በላይ የእርሱን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ እንደሆነ አስረድተው ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ፍርሃት እንዳይዛቸው አሳስበዋል። በተጨማሪም እግዚአብሔር ወጣቶችን ሳያቋርጥ እንደሚጠራቸው ለምሳሌ ወደ ኤማሁስ ሲጓዙ ለነበሩት ደቀ መዛሙርት የደረሳቸውን ጥሪ፣ መንጋውን ይጠብቅ ለነበረው ዳዊትን የተደረገውን ጥሪ እንደዚሁም ሁሉን ነገር ትቶ ለተ ቀን ወደ ቤተ መቅደስ በመመላለስ እግዚአብሔርን ይፈልግ የነበረውን ሳሙኤልን አስታውሰው እነዚህ በሙሉ ቁጭ ብለው ሳይሆን በዕለታዊ ኑሮአቸው እግዚአብሔርን ይፈልጉ እንደነበር ገልጸው እግዚ አብሔር ለሚፈልጉት ሁሉ፣ ለሚጠይቁት ሁሉ መልስ እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ቅዱስ ሉቃስ ኣንደጻፈው በምዕ. 11. ቁ. 9 ላይ ፈልጉ ታገኛላችሁ የሚለውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ጌታን የምትፈልጉት የስልክ ጥሪ በማድረግ፣ በቴሌቪዢን ውስጥ፣  ጆሮን በሚያደነቁር ሙዚቃ ውስጥ፣ ወይም በክፍላችሁ ውስጥ ሊያገኙት እንደማይችሉ አስረድተዋል። እግዚአብሔር የሚገኘው ከእርሱ ጋር በሚደረገው የማያቋርጥ ግንኙነት በመሆኑ፣ በእርሱ በመታመን፣ ልብን ለእርሱ ክፍት በማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣቶችን እንደሚፈልግና እንደሚጠራቸው፣ ራሳቸውን ከሚወዱት በላይ ስለሚወዳቸው ይህን አፍቃሪ ጌታን ለማግኘት ወደ ቤተ ክርስቲያን መጠጋት፣ በመንፈሳዊ ማሕበራት መታቀፍ፣ በጋራ ሆነው መንፈሳዊ ጉዞ ማድረግና የጋራ ጸሎት ዝግጅቶችን መካፈል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የፓለርሞ ተወላጅ የሆኑትን ብጹዕ አባ ፑሊሲን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ አባ ፑሊሲ የቁምስና መሪ ካህን ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ ወንጌልን፣ በምዕመናን መካከል ህብረትን፣ በጋራ መሥራትን፣ ፍትህንና የተቸገሩ ወጣቶችን መርዳትን ያስተምር ነበር። ምክንያቱም ወንጌል የሕይወት ትምህርት ቤት፣ የፍቅር ምንጭ ስለ ሆነ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ነብዩ ሳሙኤልን በድጋሚ በማስታወስ እግዚአብሔር ሳሙኤልን በሌሊት እንደጠራው እንዲሁም ዮሴፍንም በእንቅልፍ ላይ ሳል በሕልም እንዳነጋገረው ሁሉ ወጣቶችም በሕይወት ጉዞ መካከል ማለም እንደሚያስፈልግና እግዚአብሔር ወደ ልብ ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ መፍቀድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ወጣቶች እነዚህን ሦስቱን የሕይወት አካሄዶችን እነርሱም መጓዝን፣ መፈለግንና ማለምን እንዳያቋርጡ አሳስበዋል።  ቅዱስነታቸው ባሁኑ ጊዜ ወጣቶች ብቻቸው መሆንን እንደሚመርጥ፣ ለሌሎች አገልግሎት መስጠትን እንደማይፈልጉ አስታውሰው ለሌሎች አገልግሎት ራስን በማዘጋጀት፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እገዛን ማደረግ ሕይወት ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል ብለው፣ ሌሎችን ለመርዳት የማይኖር የመኖሩ ትርጉም የለውም ብለዋል። የአገልግሎት ባለቤት የሚሆነው አገልግሎትን የሚሻ ነው ያሉትን የብጹዕ አባ ፑሊሲ ንግግር ያስታወሱ ቅዱስነታቸው ለሌሎች አገልግሎት ራሱን የሚያውል ምንም የሚያጣ ነገር እንደሌለ፣ በልቡ ውስጥ ደስታን እንደሚሞላ አስረድተዋል። ሌሎችን በመርዳት ደስታን የምናተርፍ ከሆነ የማይጠፋ ደስታም እግዚአብሔር እርሱ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም ብለዋል። ስለዚህ ወጣቶች የሕይወታቸውን ጉዞ ማቋረጥ እንደማያስፈልግ፣ ዘወትር እግዚአብሔርን መሻት ማቋረጥ እንደማያስፈልግ፣ ሕልም ማድረግና ራስን ለአገልግሎት በማዘጋጀት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የሚችሉት ሁሉ ከማድረግ እንዳይቆጠቡ አሳስበዋል። ፍርሃትን በማስወገድ ከእግዚአብሔር የሚሰጠውን የሕይወት በረከት በመቀበል፣ እርሱ በቅዱስ ቃሉ በኩል የሚናገረውን በጽሞና ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በሁለተኛ ደረጃ የተነሳው የሰው ልጅ ክብርን የተመለከተ ሲሆ ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሲቺሊያ ደሴት ብዙ ሕዝቦች የሚገኙባት ደሴት እንደሆነች አስታውሰው ይህን የስፍራውን መልካም ባሕልና ልማድ ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ከእምነት የተግኘ መልዕክት እንደሆነ አስረድተዋል። እምነት የሚያድገው ወይም የሚሰራጨው ሰዎች ሲገናኙና እግዚአብሔርም ይህ ይከናወን ዘንድ ብቻችን እንዳልተውን አስረድተዋል። በዚህም የእግዚአብሔር ማዳን ለአንድ ሰው ብቻ እንዳልሆን ወይም ለተወሰነ ሕዝብ ብቻ እንዳልሆን ነገር ግን ለዓለም ሕዝብ በሙሉ እንደሆነ እንገነዘባለን ብለዋል። በመሆኑም የሕዝቦች መገናኘት፣ በእንግድነት መቀባበል የሚያመለክተው መረዳዳት የመልካም ስነ ምግባር መግለጫ መንገድ ብቻ ልዩ የሆነ የክርስቲያንነታችን መግለጫ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል እንደተናገረው ተርቤ፣ ታምሜ፣ እንግዳ ሆኜ ካያችሁ እርሱ እኔ ነኝ ያለውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ ዘመን ሰዎች መካከል ከወንጌል የሚገኝ እውነተኛ ፍቅር እንደሚጎድል አስረድተዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ መልዕክቱ በምዕ. 9. ቁ. 7 ላይ “ስለዚህ እግዚአብሔር የሚወድደው በደስት የሚሰጠውን ስው ስለሆነ እያንዳንዱ ለመስጠት የፈለገውን በልቡ ፈቅዶ ይስጥ እንጂ እየተጸጸተ በግዴታ አይስጥ” ያለውን ያስታወሱ ቅዱስነታቸው ከልቡ የሚለግሰውን እግዚአብሔር እንደሚወደው ተናግረው እገዛ ወይም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው አቅም የፈቀደውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

15 September 2018, 19:00