ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ጉዞ ላይ እያሉ ለጋዜጠኞች መልስ ሰጡ።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከኢጣሊያ ክልል ውጭ የሚያደርጉትን ይህን 25ኛ ዙር ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት፣ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ. ም. ከጠዋቱ 2:30 ከፊውሚቺኖ አውሮፕላን ጣቢያ መነሳታቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሦስቱን የባልቲክ አገሮች የሚባሉትን ሊጧኒያ፣ ሌቶኒያንና ኤስቶኒያን እንደሚጎበኙ ታውቋል። የመጀመሪያ መድረሻቸው ወደ ሊጧኒያ እንደሆነ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለከታል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለኢጣሊያው ፕሬዚደንት ለክቡር አቶ ሴርጆ ማታሬላ በላኩት የቴሌግራም መልዕክታቸው፣ ለኢጣሊያ ሕዝብ ሰላምንና ለአገሩም ጸጥታን ተመኝተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዚህ ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት የአየር ክልላቸውን አቋርጠው ለሚሄዱባቸው አገሮች መንግሥታት እንደርሱም ክሮአሺያ፣ ሃንገሪ፣ ስሎቫኪያና ፖላንድ የቴሌግራም መልዕክት ልከዋል። ከፊውሚችኖ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ጣቢያ ከመነሳታቸው አስቀድመው በቦታው ለነበሩት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ብጹዓን ካርዲናሎችና ጳጳሳት ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።  

የኢጣሊያው ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ሴአርጆ ማታሬላም በበኩላቸው በራሴና በመላው የኢጣሊያ ሕዝብ ስም በማለት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላኩት መልዕክታቸው እንደገለጹት በዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው አማካይነት ለሦስቱም አገሮች ሕዝቦች የሚሰጡት ምስክርነት በማሕበራዊ እና ባህላዊ የዕድገት ጉዞ ወደ ከፍተኛ ግቦች ላይ ለመድረስ እንደሚያግዝ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፣ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውም ፍሬያማ እንዲሆን ተመኝተውላቸዋል።

ወደ ሊጧኒያ ባደረጉት በበረራ ሰዓት የቅድስት መንበር የሕትመት ክፍል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ግሬግ ቡርኬ፣ አብረዋቸው የተጓዙትን ነባር ጋዜጠኞችንና ለመጀመሪያ ጊዜ ከባልቲክ አገሮች የተገኙ ዘጠኝ ጋዜጠኞችን በመወከል ለቅዱስነታቸው ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ ይህ ሐዋርያዊ ጉብኝት 25ኛው ዓለም አቀፍ ጉብኝት እንደሆነ አስታውሰው፣ ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ጋዜጠኞች የሚያስተላልፉት መልዕክት እንዳለ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ለጋዜጠኞቹ ሰላምታቸውንና ምስጋናቸውን  ካቀረቡላቸው በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት ይህን ሐዋርያዊ ጉዞአቸውን በጉጉት በመከታተል ላይ ላለው የዓለም ሕዝብ በቂ መረጃን በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቀው፣ በሦስቱ አገሮች መካከል የጋራ ታሪክ፣ የጠበቀ ግንኙነትና በዚያኑ መጠን ልዩነቶችም እንዳሉ በመረዳት ትኩረት እንዲያድረጉ ካሳሰቡ በኋላ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።            

22 September 2018, 19:33