ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቪልኒዩስ ከተማ ለምእመናን ንግግር አደረጉ።

የዚህ ዝግጅት አቅርቅቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በነበራቸው እቅድ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በከተማው በሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም የምሕረት እናት ካቴድራል ሄደው ጸሎት ካቀረቡ በኋላ በቦታው ለነበሩት ምዕመናን ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ በቦታው ለተገኙት በርካታ ምዕመናንና እንግዶች ባደረጉት ንግግር በ1791 ዓ. ም. ከተማው በወራሪ ሃይል ሥር በወደቀ ጊዜ በርካታ የሰው ሕይወት እንደጠፋና  ንብረቶችም መውደማቸውን አስታውሰው፣ ነገር ግን ለወራሪ ሃይል መከላከያ እንዲሆን ተብሎ የተሠራው ወደ ከተማው የሚያስገባው “የአውሮራ በር” በመባል የሚታወቀው በር ምንም ጉዳት ስይደርስበት እስከ ዛሬ መቆየቱንና በዘመኑ በዚያ በር ላይ ተሰቅሎ የነበርው የእመቤታችን ቅድስት ማርያም፣ የምሕረት እናት ምስል እንደነበር አስታውሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት በችግራችን ጊዜ ሁል ልትረዳን ካጠጋባችን መሆኗልን አስረድተዋል።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከአደጋ ልትሰውረን እንደምትችል ለማስተማር እንደምትፈልግ አስረድተው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሁላችን እናት፣ ወደዚህ ስፍራ ለሚመጣ ሁሉ እኛ መረዳት በማንችለው መንገድ የልጇ መልክ በልባችን ውስጥ እንዳለ ትመለከተአዋልች ብለዋል። እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔርን ማየትና ማግኘት የሚችለው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል በልቡ ሲታተም ነው ብለዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በፍርሃትም ይሁን በማንኛውም ምክንያት የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም ዜና ወደ ልባችን ዘልቆ እንዳይገባ ልባችንን የምንዘጋ ከሆነ፣ ግድግዳን የምንገነባ ከሆነ የራሳችንና የሌሎችንም ሕይወት ወደ መልካም አቅጣጫ የሚመራው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ልባችን እንዳይገባ እንከለክላለን ብለዋል። ባለፉት ዘመናት በመካከላችን ጠናካራ የጥል ግድግዳን ገንብተናል፣ ዛሬ ግን ይህ የጥልና የልዩነት ግድግዳ ፈርሶ በመካከላችን የወንድማማችነት ፍቅር፣ የሰላምና የደስታ፣ አብሮ የመጓዝ አስፈላጊነት እንዳለ እንረዳለን ብለውዋል። የምሕረት እናት ቅድስት ድንግል ማርያም በየቀኑ ወደዚህ ቦታ ከሊጧኒያ፣ ከፖላንድ ከቤሎሩሲያ እና ከሩሲያ የሚመጡትን በርካታ ነጋዲያንን ትመለከታቸዋልች። አሁን የደረስንበት ዘመን እርስ በርስ እንድንገናኝ፣ በየአገሮቻችንም መካከል በነጻነት እንድንንቀሳቀስ ምቹ አጋጣሚዎችን አዘጋጅቷል። በተመሳሳይ መልኩ ይህን መልካም አጋጣሚን በመጠቀም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመንቀሳቀስ በአንድ አማካይ ቦታ መገናኘት ብንችል፣ በመካከላችን ያለውን አንድነት ማሳደግ ብንችል፣ በነጻ የተቀበልናቸውን ጸጋዎች መካፈል ብንችል፣ ከግለኝነት ወጥተን ለሌሎች አገልግሎት ራሳችንን ማቅረብ ብንችል፣ በመካከላችን ያሉትን ልዩነቶች እንደ አንድ የሕይወት በረከትና ጸጋ አድርገን መውሰድ ብንችል ምንኛ መልካም ይሆን ነበር ብለዋል።

አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን ወደ ሌላው ዓለም ክፍት ስናደርግ ወይም ከሌላው ዓለም ጋር ውድድር ውስጥ ስንገባ መልካም ግንኙነታችንን ወደሚያደናቅፍ ወደ ጥላቻ ወደ ክፍፍልና ወደ ልይነት እናመራ ይሆናል። ይህ ደግሞ ምንም የሚጠቅመን አይደለም። የምሕረት እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እንደ መልካም እናቶች ሁሉ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ለመሰብሰብ በመፈለግ “ወንድምህን ፈልግ” በማለት ጥሪ ታቀርብልናለች። በዚህ ጥሪዋ ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምንገባበትን በር ትከፍትልናለች ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ንግግራቸው ከሉቃ. ምዕ. 16 19-31 የተጻፈውን የሃብታሙ ሰውና ድሃው አልዓዛር ታሪክ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ታሪክ ጋር በማያያዝ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን በአልዓዛር ላይ የወጣ ቁስል ሳይሆን ዛሬ በዘመናችን በገሃድ እንደምናየው በርካታ ሕጻናትና ቤተሰብ በከባድ ቁስል ሕመም በመሰቃየት የፍቅርና የቸርነት ማስታገሻን እንድናቀርብላቸው በመወትወት ላይ ይገኛሉ። ምክንያቱም ቸርነት ወደ ሰማይ የምንገባበት ቁልፍ ነውና ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ንግግራቸውን በመቀጠል ወደ ፍቅርና ወደ ቸርነት የሚያስገባውን በር ስንሻገር ብቻ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት የተሻለ እንዲሆን የሚያደርግ ሃይል ማግኘት፣ ራሳችንን ከሌሎች የተሻልን አድርገን ሳንመለከት ክፋቶቻችንንና ድክመቶቻችንን ማወቅ እንችላለን ብለዋል። በትሕትና ተሞልታችሁ ሌሎች ሰዎች ከእናንተ እንደሚሻሉ አድርጋችሁ ቁጠሩ እንጂ ወገን በመለየትና በራስ ወዳድነት ወይም ያለ እኔ ማን አለ በሚል ትምክሕት ምንም ነገር አታድርጉ የሐዋ. ጳውሎስ መልዕክት ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች በም. 2 ቁ. 3. የመቁጠሪያን ምስጢር በመገንዘብ ተስፋችን ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት የምንችል እንድንሆን፣ ሁሉንም በየዋህነት የሚቀበልና የሚያስተናግድ ሕብረተሰብን መገንባት እንድንችል፣ የውይይት ልማድንና ትዕግስትን፣ በሌላ ላይ መፍረድን ሳይሆን ይቅር ማለትን፣ የልዩነት ግድግዳን ሳይሆን እርስ በርስ መገናኘት የምንችልበትን ድልድይ የምንገነባበት ልብ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከልጇ ታማልደን። ለዚህ ለተቀደሰ አገር እርሷ የዘወትር በር ትሁነን በማለት እርሷ ትምራን በማለት ምዕመናኑ አጭር ጊዜን በነውሰድ ሦስተኛውን የደስታ ምስጢር በማስታወስ የመቁጠሪያ ጸሎትን እንዲደግሙ ጠይቀዋል።                     

22 September 2018, 19:21