ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ከአምላካችን የተሰጠን የመታረቅ ተልዕኮ አለብን”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ ግርማቸው ተስፋዬ - ቫቲካን

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በዛሬው ዕለት ማለትም መስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም. እ.አ.አ. በሪጋ የሉተራን ወንጌላዊ ካቴድራል ከተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች ጋር መወያየታቸው ታውቋል።

ቅዱስ ኣባታችን ሲናገሩም በዝች ሃገር ማለትም በሌቶኒያ በእያንዳንዱ የክርስትና አብያተ ክርስቲያናት መካከል በአክብሮት በትብብር እና በወዳጅነት የሚከናወኑትን ክንውኖች ሁሉ ለመመልከትና ከእናንተም ጋር ለመገናኘት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ ሲሉ የመግቢያ ንግግራቸው ኣስቀምጠዋል። ይህ ማለት ደግሞ አሉ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ሕይወት ያለው የሃይማኖቶች ሕብረት በዚህ በሌቶኒያ እንዳለ የሚያረጋግጥ ነው ካሉ በኃላ ይህ ደግሞ ያለምንም ጥርጥር የትልቅ ተስፋና የደኅንነት ጸጋ መሆኑን ኣብራርተዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ኣክለዉም በሌቶኒያ የሉተራን ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ የሆኑትን ጃኒስ ቫናግስ ለጸሎትና ለውይይት ቤታቸውን ክፍት በማድረጋቸው ኣመስግነው ይህ ቤተክርስቲያን ከ 800 ዓመት በላይ የክርስትናን ሕይወት በዝች ከተማ ለማጎልበት ለተለያዩ የሃይማኖት ተቋሞች በጸሎትና በአምልኮ እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎች ሥቃይና መከራም በነበረበት ወቅት በብዙ መልኩ የሰዎችን ተስፋ ለማለምለም በሚቻለው ሁሉ ለማገዝ የተቻለዉን ሁሉ እንዳደረገ ኣስታውሰዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ ባዛሬው ዕለትም ሁላችን በዚህ እንድንሰበሰብ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑንና ኣሁንም መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን በሕዝባችንና በምዕመናኖቻችን ሁሉ መልካም ግንኙነት እንዲኖር እንዲጠነክር ያግዘን ብለው በዚህ መልኩ ከተጓዝን ልዩነቶቻችን በመካከላችን መለያየትን አይፈጥሩም እንደውም በተቃራኒው መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን ገብቶ እንድንወያይ እንድንከባበርና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ያስችለናል ብለዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በመቀጠል በዚህ ካቴድራል ውስጥ በተመረቀበት ጊዜ በዓለም ላይ እጅግ ትልቅና ከአውሮፓ ጥንታዊ ከሆኑት ኦርጋኖች አንዱ የሆነው በዚህ ካቴድራል ውስጥ እንደሚገኝ ኣስታውሰው የዚህ ቦታ መኖር ከኦርጋኑም የበለጠ የራሱ ህይወት እና ባህል ማንነቱም ጭምር አካል መሆኑን ኣብራርተው ይህ ለጎብኚዎችም መበራከትም በር ከፋችና የራሱ የሆነ ትልቅ ኣስተዋፅኦ ኣለው ብለዋል።

በመቀጠልም ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ የወንጌሉን ቃለ በልባችን ማዳመጥና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እና ይህ ካልሆነ ግን ከእምነት የሚወለደው ርኅራሄና ጥንካሬ የእርቅን መንገድ ያጠፋል ብለዋል።

በመቀጠልም የወንጌልን ሙዚቃ ቃል መስማቱ ከቀረ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚወስደንን ወይም የሚመራንን ድምፅ የጠፋብናል ወደ ብቸኝነትም ይመራናል ብለዋል።

በዮሓንስ ወንጌል 17,21 ያለው ኣባት ሆይ ዓለም ባንተ ያምን ዘንድ ሁሉም ኣንድ ይሁኑ የሚለው ቃል ዛሬም በመካከላችን እንደሚጮህ ጠቅሰው ለዚህም ቃል እግዚኣብሔርን አመስግነው ዛሬም ቢሆን በፊት የነበሩትን ስህተቶች በማንሳት መወቃቀስ ሳይሆን ለኣንድነትና ለጋራ የክርስትና እድገት ኣብሮ መሥራትና መፀለይ ያስፈልጋል ብለዋል።

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቼስኮስ በመጨረሻም እግዚኣብሔር ለኣንድነት የሚጠራን ሁልጊዜ መልዕክተኞች እንድንሆን እና ሕዝባችን ልቡን ለመንፈስ ቅዱስ ክፍት በማድረግ በውስጣችን ያለዉን ክፋትና ኃጢኣት ሁሉ እንዲደመስስ እና የእርሱ መለኮታዊ ኃይል በውስጣችን እንዲሞላን ለማድረግ ነው ብለው ይህንን የወንጌል ቃል ያለማቋረጥ በሕብረት በመዘመር እግዚኣብሔር ለጠራን ሕይወት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

24 September 2018, 18:13