ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የአንድ ቤተሰብ አባል መሆናቸውን ንገሯቸው”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በታሊን ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስ ካቴድራል ተገኝተው በፍቅር ሥራ ላይ ለተሰማሩት አገልጋዮች ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው እነዚህ አገልጋዮች ላደረጉላቸው አቀባበልና ለሚያበረክቱት አገልግሎት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በመቀጠልም ከሁለት ባልና ሚስት የቀረበላቸውን ስጦታ ተቀብለው እነዚህ ባልና ሚስት በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚሰጡት መልካም ምስክርነት አመስግነዋቸዋል። እነዚህን ባልና ሚስት እግዚአብሔር በዘጠኝ ልጆች እንደባረካቸው አስታውሰው፣ ይህን ያህል ቁጥር ሕጻናት ያለበትን ቤተሰብ መምራት ቀላል እንዳልሆነ አስረድተው ቢሆን ብዙ ልጆች ያሉበት ቤተሰብ የወደ ፊት ተስፋና ደስታ ያለበት መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህም ነው “ፍቅርን ስለ ሰጠሄን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን” የምትሉት ብለዋል። በዚህ አገር የክረምቱ ወራት እጅግ በሚበርድበት ጊዜ በቤተሰባችሁ መካከል ግን ብርድ አይሰማም ብለው ምክንያቱን ሲገልጹ ብዙ ስለሆናችሁ ነው ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም ለአገልግሎት ወደ እናንተ ዘንድ የሚመጡና የእግዚአብሔርን የእርዳታ እጅ የሚዘረጉ የደናግል ማሕበር አባላት የመልካም ሥራ ምስክርነት ስላጋራችሁኝ አመሰግናለሁ ብለዋል።

እምነት በድፍረት በመሞላት ምቾትን በመተው የኢየሱስን ክርስቶስን ቃል በተግባር ለመግለጽ ይችላል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ፣ እኔ እንደወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ የሚለውን ከዮሐንስ ወንጌል ምዕ. 13 ቁጥር 34 በመጥቀስ፣ ፍቅር የሚለያየንንና የሚከፋፍለንን ሰንሰለት በመበጣጠስ በፍቅር በመሙላት የአንድ ቤተሰብ አባል ያደርገናል ብለዋል። ፍቅር ርሕራሄንና ሰብዓዊ ፍቅርን ያውቃልና ብለዋል። በአገልግሎት የታገዘ እምነት፣ እንደነዚህ የደናግል ማሕበር አባላት ወደ ተቸገሩት ዘንድ በመሄድ ተጨባጭ አገልግሎትን በማበርከት፣ እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

በአካባቢው የደናግል ዕርዳታ የማይጎድልበትን ቪላድሚር የተባለ ተረጂን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ተረጂው በአገልጋዮቹ አማካይነት፣ የሚመኘውንና ዘወትር የሚፈልገውን የእግዚአብሔር እርዳታ እንዳገኘም አስረድተው በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 15 ቁጥር 22 ላይ “አባቱ ግን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲህ አለ። ቶሎ ብላችሁ ጥሩ ልብስ አምጡና አልብሱት፣ በጣቱ ቀለበት፣ በእግሩም ጫማ አድርጉለት” የሚለውን የወንጌል ክፍል ጠቅሰዋል። እግዚ አብሔር ዘወትር እኛ ደስተኞች መሆናችንን ማየት ይፈልጋል ያሉት ቅዱስነታቸው የሚያስፈልገንን ከመስጠትና ከማሟላት ወደ ኋላ አይልም ብለዋል። በመሆኑም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን አንድነት ተጠናክሮ የአንድ ቤተሰብ አባሎች እንደመሆናችን፣ ሕይወትም ክቡር መሆኑን በመረዳት አንዱ ለሌላው ለመርዳት ዝግጁዎች መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተጨማሪም በምዕመናን መካከል ያለው መተጋገዝና አንድነት መቀጠል አለበት ብለው ወደ ሌሎች ዘንድ ሄደው የአንድ ቤተሰብ አባል፣ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን እንዲመሰክሩ አደራ ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን እንደጠራቸው ሁሉ የእርሱን መንግሥት እንድታውጁ ዛሬም ቢሆን እያንዳንዳችሁን ይጠራችኋል ብለው በሕይወታችሁ ያያችሁትን የኢየሱስ ክርስቶስ እርዳታ፣ የእርሱን ሃያልነት ለሌሎች መመስከር ይኖርባችኋል ብለዋል።

ጊዜአችሁን ሰውተው በስፍራው ለተገኙት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ሳያቋርጥ በእጆቻችሁ ሥራ አማካይነት እንዲቀጥል በማለት በፍቅር ሥራ ላይ ለተሰማሩት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬአቸውን ከሰጡ በኋላ በጸሎታቸውም እንዲያስታውሷቸው አደራ በማለት ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።                                 

25 September 2018, 18:07