ፈልግ

የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት አልጋ የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት አልጋ 

ር.ሊጳ. ፍራንቸስኮስ “የሞት ቅጣት በፍጹም ተቀባይነት የለውም!”

የካቶሊክ ቤተክርስትያን በቅዱስ ወንጌል ብርሃን በመመራት “ልገረሰስ የማይችለውን የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር የሚጻረረውን የሞት ቅጣት በጽናት ትቃወማለች!”

ር.ሊጳ. ፍራንቸስኮስ “የሞት ቅጣት በፍጹም ተቀባይነት የለውም!”

የካቶሊክ ቤተክርስትያን በቅዱስ ወንጌል ብርሃን በመመራት “ልገረሰስ የማይችለውን የሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር የሚጻረረውን የሞት ቅጣት በጽናት ትቃወማለች!” በዚህም ሳታበቃ ይህ ቅጣት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሀገራት ውስጥ ሁሉ ተፈጻሚ እንዳይን በጽናት ትሠራለች።

የዚህ ዜና አጠናቃሪ መብራቱ ኋይሌጊዮርጊስ-ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 25/2010 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተክርስትያን አንቀጸ እመንት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ በሆኑት በክቡር ካርዲናል ሉዊዝ ፍራንቸስኮስ ላዳሪያ የተፈረመ እና የሞት ቅጣትን በጽኑ የሚያወግዝ አስተምህሮ በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ እንዲካተት ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ያቀረቡት ሰነድ በቅዱስነታቸው ተቀባይነትን አግኝቶ መጽደቁን ለቫቲካን ሬዲዮ ከደረሰው መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

እስከ ሐምሌ 25/2010 ዓ.ም ድረሰ በአገልግሎት ላይ በነበረው የካቶሊክ ቤተክርስትያን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በቁጥር 2267 ብቻ ላይ የሚገኘውን “የሞት ቅጣት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት የፍትሕ ባለስልጣናት ተከሳሹ ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን ካለፈ በኋላ፣ ተከሳሹ የፈጸመው ከባድ ወንጀል መሆኑ እና በፍጹም ተቀባይነት የሌለው፣ በጣም ከባድ እና የከፋ ወንጀል መሆኑ ከተረጋገጠ የማኅበርሰቡን ማኅበራዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ በማሰብ ተፈጻሚ ይሆናል” በሚለው ቀደም ሲል የነበረው የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በሚከተለው አዲሱ አስተምህሮ ተተክቱዋል። በዚህ መሰረት ከሐምሌ 25/2010 ዓ.ም ጀምሮ በካቶሊክ ቤተክርስትያን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ውስጥ በቁጥር 2267 ላይ የነበረው አስተምህሮ በሚከተለው አስተምህሮ ተተክቱዋል።

ይሁን እንጂ ዛሬ አንድ ሰው በጣም ከባድ የሆኑ ወንጀሎች ከፈፀመ በኋላም እንኳን ቢሆን ሰብዓዊ የሆነ ክብሩ እንዳለ እንደ ሚቀጥል ለመገንዘብ ተችሉዋል። በተጨማሪም ሀገራት ባስቀመጡዋቸው ከፍተኛ ቅጣቶች ትርጉም ላይ አዲስ ግንዛቤ ተገኝቷል። በመጨረሻም የዜጎች ደኅንነት መጠበቁን የሚያረጋግጥ የበለጠ ውጤታማ የእስር ማቆያ ስርዓት የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ነገር ግን በተመሳሳይ ሁኔታ ታራሚው ወይም በዳዩ የጎድለውን ሰነ-ምግባር በፍጹም መልሶ መጎንጸፍ አይችልም የሚለውን ሐሳብ ግን የማረጋገጥ እድል የለውም”።  በዚህም ምክንያት ቤተክርስትያን በወንጌል ብርሃን በመመራት "የሞት ቅጣት በፍጹም ተቀባይነት የለውም ምክንያቱም የሞት ቅጣት የሰውን ልጅ ተጋላጭ የሚያደርግ እና በሰው ልጅ ክብር ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው በማለት ታስተምራለች፣ ይህ ቅጣት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፋጻሚ እንዳይሆን በጽናት ትሠራለች”።

በሚለው ከላይ በተጠቀሰው አዲሱ የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከሐምሌ 25/2010 ዓ.ም ጀምሮ እንዲተካ ተደርጉዋል። ይህም ማለት ቤተክርስትያን የሞት ቅጣትን በፍጹም አትቀበልም ማለት ነው።

ከእዚህ ቀደም የነበረው በካቶሊክ ቤተክርስትያን ትምሕርተ ክርስቶስ በቁጥር 2267 ላይ የነበረው አስተምህሮ ላይ እንደ ተጠቀሰው “ነገር ግን ያለደም መፍሰስ የሕዝቡን ደኅንነት ከጥቃት መጠበቅ እና መከላከል ከተቻለ የምንግሥት ባለስልጣናት ይህንን መንገድ ቢከተሉ መልካም ነው” በሚለው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን የተምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ውስጥ “ነገር ግን ያለ ደም መፍሰስ የሕዝቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ከተቻለ” የሚለው ሀረግ ክፍተት ያለው በመሆኑና “ነገር ግን” የሚሉት ቃላት በዚህ አረፍተ ነገር አውድ ውስጥ አሉታዊ የሆነ እንድምታን የሚያሰሙ ቃላት በመሆናቸው የተነሳ አሁን ባለው ነባራዊ ዓለማችን ውስጥ የሞት ቅጣት እንዲፈጸም ክፍተት የሚያሳይ በመሆኑ የተነሳ ይህ አንቀጽ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ከሐምሌ 25/2010 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በአዲሱ እንዲተካ ተደርጉዋል።

የካቶሊክ ቤተክርስትያንን አንቀጸ እመንት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ በሆኑት ክቡር ካርዲናል ሉዊዝ ፍራንቸስኮ ላዳሪያ ይህንን ለውጥ በተመለከተ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ብጹዕን ጳጳሳት በላኩት ይፋዊ መልእክት እንደ ገለጹት ይህ አሁን በካቶሊክ ቤተ ክርስትስያን ትምህርተ ክርስቶስ በቁጥር 2267 ላይ የሞት ቅጣትን በተመለከተ የተደረገው ለውጥ “ቀደም ሲል የነበረውን የቤተ ክርስትያኗን አስተምህሮ የሚቃረን ሳይሆን በቤተ ክርስትያኗ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚደረጉ ማሻሻያዎች አንዱ አካል መሆኑን” ገለጸው “እነዚህ አስተምህሮዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት የፍትህ አካላት ተቀዳሚ ተግባራቸው የማኅበርሰቡን ማኅበራዊ ደኅንነት በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የሚባሉ ቅጣቶች ላይ ያላቸውን አቋም በተለየ መልኩ እንዲገነዘቡ በማድረግ ወንጀለኛው ወይም በዳዩ የፈጸመውን ወንጀል ወይም በደል ደግሞ እንዳይሰራ የሚያስችሉትን ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደ ሚገባቸው ለማስገንዘብ እንደ ሆነ” ጨምረው ገለጸዋል። 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ሁለተኛ የሞት ቅጣት እንዲቀር ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር

የካቶሊክ ቤተክርስትያን አንቀጸ እመንት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር ካርዲናል ሉዊዝ ፍራንቸስኮ ላዳሪያ በመግለጫው ወቅት እንደ ገለጹት “ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በዘመናቸው የሞት ቅጣት እንዲቀር ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደ ነበረ” የገለጹ ሲሆን በተለይም ደግሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን በዚህ ረገድ ያላትን አስተምህሮ እና አንቀጸ እመንት ማሻሻያ እንዲደርግበት  የቤተክርስትያኗን አንቀጸ እመንት ለሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቅርበው እንደ ነበረ ገለጸው “አንድ ሰው የገደለ ወንጀለኛ ሰብዓዊ መብቱን መገፈፍ የለበትም፣ እግዚአብሔር እራሱ ለዚህ ዋስትና ለመስጠት ቃል ገብቱዋል” በማለት የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር መሆኑን ቤተ ክርስትያኗ በአገኘችው አጋጣሚ ሁሉ የግንዛቤ ትምህርት መስጠት እንደ ሚገባት ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በተለያዩ አጋጣሚዎች “የሞት ቅጣት ጭካኔ የተሞላበት እና ጥቅም የሌለው” በመሆኑ የተነሳ የሞት ቅጣት እንዲቀር ከፍተኛ ጥረት አድርገው ማለፋቸውን የካቶሊክ ቤተክርስትያን አንቀጸ እመንት የሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር ካርዲናል ሉዊዝ ፍራንቸስኮ ላዳሪያ ጨምረው ገለጸዋል።

ከዚህ ቀደም የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት በኔዲክቶስ 16ኛ “የኅብረተሰቡ መሪዎች የሞት ፍርድን ለማስቀረት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እና ትኩረት እንዲያደርጉ” በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ካርዲናል ሉዊዝ ፍራንቸስኮ ላዳሪያ “የሞት ቅጣት ተግባራዊ እንዳይሆን በተለያዩ ሀገሮች ውስጥ የተለያዩ ሕግዊ፣ ፖሌቲካዊ እንቅስቃሴዎች እና ተነሳሽነት የሚያሳዩ ሀገራት ቁጠር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨምረ መምጣቱ በጣም አበራታች የሆነ ጅምር እንደ ሆነ፣ ይህም ተጨባጭ የሆነ ለውጥ እያስገኘ በመሆኑ የተነሳ የሞት ቅጣት የወንጀለኛውን ሰብዓዊ ክብር የሚነካ በመሆኑና ማኅበራዊ ደኅንነትን የሚያስጠብቅ ባለመሆኑም ጭምር የሞት ቅጣት ሊወገድ ይገባዋል” በማለት ይሞግቱ እንደ ነበረ ካርዲናል ሉዊዝ ፍራንቸስኮ ላዳሪያ ጨምረ ገለጸዋል።

03 August 2018, 15:59