ፈልግ

ITALY-POPE-YOUTHS-ANGELUS ITALY-POPE-YOUTHS-ANGELUS 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “ክርስቲያን እውነተኛውን እንጂ የግብዝነት ሕይወት መኖር የለበትም”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ከሚገኙት ምዕመናንና ሃገር ጎብኚዎች ጋር ከሚያሳርጉት ከእኩለ ቀን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በፊት በዕለቱ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል እና የሐዋርያት መልዕክቶች ላይ አስተንትኖ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት ትናንት እሁድ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ. ም.፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክት በምዕ. 4 ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት፣ ክርስቲያን እውነተኛ ሕይወትን እንጂ የግብዝነት ሕይወት መኖር የለበትም ማለታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ፣

ውድ የኢጣሊያ ወጣቶች እንደምን አረፈዳችሁ፣

ዛሬው በተነበበው ሁለተኛው ምንባብ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ‘ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ’ (ኤፌ. 4፤30) በማለት ይመክረናል። ለመሆኑ መንፈስ ቅዱስን የምናሳዝነው እንዴት ነው? እኛ ሁላችን በሁለቱ የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት እነርሱም በምስጢረ ጥምቀት እና በምስጢረ ሜሮን አማካይነት መንፈስ ቅዱስn ተቀብለናል። ስለዚህ በሁለቱ ምስጢራት በኩል የተቀበልነውን መንፈስ ቅዱስን ላለማሳዘን ከፈለግን ቃል በገባነው መሠረት እንደ መንፈስ ቅዱስ በሚፈልገው ወይም በሚያዘን አኳኋን፣ በጥምቀት የተቀበልነውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በምስጢረ ሜሮን በማደስ ነው። መንፈስ ቅዱስ በሚፈልገው ወይም በሚያዘን አኳኋን በምንልበት ጊዜ ከግብዝነት ነጻ በሆነ መንገድ መሆኑን መዘንጋት የለባችሁም። ክርስቲያን እውነተኛ ሕይወትን እንጂ የግብዝነት ሕይወት መኖር የለበትም። ምስጢረ ጥምቀትን ስንቀበል የገባናቸው ቃል ኪዳኖች ሁለት ገጽታዎች አሉት። እነዚህ ሁለቱ ገጽታዎች፣ ክፉን በመቃወም መልካምን መከተል ናቸው። ክፉን መቃወም ማለት ለሚያጋጥመን ፈተና፣ ለሃጢአት እና ለሰይጣን፣ እጅ አለመስጠት ማለት ነው። በውሸት ደስታ በመሙላት ወደ ሞት የሚወስደውን መንገድ አለመከተል፣ ፍትሕን ከሚያዛባ ባሕል፣ በሐሰት ከተሞላ ሕይወት እና ሌውላን ከሚንቅ ባሕርይ፣ ከእነዚህ በሙሉ መራቅ ማለት ነው። በምስጢረ ጥምቀት ያገኘነው አዲስ ሕይወት፣ የማያቁርጥ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በመሆኑ ከልዩነት ይልቅ ወደ አንድነት፣ ከሁከት እና ከብጥብጥ ይልቅ ወደ ሰላምን የምንመርጥበት ፍላጎት በልቦናችን እንዲያድር ያደርጋል። ሐዋርያው ጳውሎስም መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ፣ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ በማለት ይመክረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሳቸው ስድስቱ ነገሮች መንፈስ ቅዱስን የሚያስቀይሙ፣ ልብን የሚያቆስሉ፣ ከእግዚአብሔር እና ከባልንጀራዎቻችን ጋር እንዳንሆን ያድረጉናል።

መልካም ክርስቲያን እንሆናለን ብለን ክፋትን አለማድረግ በቂ አይደለም። መልካሙን ገድል በመከተል  መልካም ማድረግ ያስፈልጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክትም ‘እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ’ (ኤፌ. 4፤32) በማለት ይመክረናል። ብዙን ጊዜ፣ አንዳንድ ሰዎች እኔ በማንም ላይ ክፉ አላደርግም በማለት ቅዱስ ለመሆን ሲሞክሩ እናያለን። መልካም ነው፣ ለመሆኑ መልካምንስ ታደርጋለህ? ብዙ ሰዎች ክፉንም ሆነ ደግ ሳይሥሩ እንዲሁ ልዩነት የማይታይበት ለብ ያለ ግድ የለሽ ሕይወትን ይኖራሉ። ይህን የመሰለ ሕይወት የወንጌልን መልዕክት ከመቃወም በተጨማሪ የእናንተ የወጣቶችን የንቁነት፣ የስሜታዊነት እና የድፍረት ባሕሪያችሁን ይጻረራል። አንድ ነገር ዘወትር ብታስታውሱ፣ አብረንም ብንለው፣ ብንደግመው  መልካም ነው። ቅዱስ ሁርታዶ እንዲህ ይል ነበር፦ ክፉ ተግባርን አለማድረግ መልካም ነው፣ መልካምን አለማድረግ ክፉ ነው።

የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ፣ መልካምንም የምታከናውኑ እንድትሆኑ እጠይቃችኋለሁ። ክፉ ተግባርን ባለማከናወናችሁ እርካታ እንዲሰማችሁ ሳይሆን፣ ልታከናውኑ የሚገባውን መልካም ተግባር ስላላከናወናችሁ ጸጸት የሚሰማችሁ ሊትሆኑ ይገባል። አለ መጥላት ብቻውን በቂ አይደለም፣ ይቅር ማለትም ያስፈልጋል፤ ቂም አለመያዝ ብቻውን በቂ አይደለም፣ ለጠላት መጸለይ ያስፈልጋል፤ ለልዩነት ምክንያት አለ መሆን በቂ አይደለም፣ ሰላም በጠፋበት ሰላምን፣ ልዩነት ባለበት አንድነትን ማምጣት፣ ስለ ሌሎች መጥፎን አለ መናገር ሳይሆን ስለ ሌሎች መጥፎ ሲነገር ማቋረጥ ወይም እንዳይናገሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ክፋን የማንቃወም ከሆነ የበለጠ እንዲስፋፋ እናደርገዋልን። ክፋት እስከሚገኝበት ሥፍራ ሄደን ካላስቆምን በስተቀር የበለጠ እንዲስፋፋ ዕድል እንከፍትለታለን። ክፋትም የሚስፋፋው መልካምን የሚያደርግ ደፋር ክርስቲያን በሚጠፋበት ሥፍራ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች በላከው መልዕክቱ፦ ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።

ውድ ወጣቶች ሆይ! በእነዚህ ቀናት ወደ ሮም ለመድረስ ረጅም ተጉዛችኋል፣ ከዚህ ረጅም ጉዞ ልምድንም ቀስማችኋል፣ ስለዚህ እንዲህ በማለት ልመክራችሁ እወዳለሁ፦ ጉዞአችሁ የቸርነት ጉዞ ይሁን! ጉዞአችሁ የፍቅር ጉዞ ይሁን!  በሚቀጥለው ዓመት ወደሚከናወነው 15ኛው የመላው ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ ድረስ  አብረን እንጓዝ። እመ ቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እያንዳንዳችን በዕለታዊ የሕወት ጉዞአችን፣ ክፉን ለመቃወምና ለመጥላት፣ መልካምን ለማድረግ የምንችልበትን ጸጋ  ታማልድልን።         

13 August 2018, 15:49