ፈልግ

2018.08.29 Udienza Generale, Papa Francesco incontra vescovi brasiliani 2018.08.29 Udienza Generale, Papa Francesco incontra vescovi brasiliani 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ቸርነትን ለድሆች በጋራ እንመስክር”።

በዘመናችን በከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ከልብ በማገልገል፣ በሕብረተሰባችን መካከል የአቅመ ደካማ ሰዎች ስብዕና በማስከበር፣ ፍትህንና ሰላምን በማራመድ፣ በጋራ ሆነን የትንሳኤውን ክብር በጋራ እንድንመሰክር ተጠርተናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከነሐሴ 20 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ የጳጳሳት ምክር ቤት ሐዋርያዊ ጉባኤያቸውን ወይም ሲኖዶስ በማካሄድ ላይ ለሚገኙ ለቫልደስ እና ለሜቶዲስት አብያተከርስቲያናት በላኩት መልዕክታቸው ለደሆች በሚደረገ እገዛ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የእነዚህ የሁለቱ አብያተክርስቲያናት ምዕመናን የወንጌልን የምስራች፣ በተለይም ወደ ደሆች፣ ወደ ተናቁትና ወደ ተገለሉት ሰዎች ዘንድ ለማዳረስ በሚደረግ ጥረት ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጋር እንዲተባበሩ ጠይቀዋል። በሰሜን ኢጣሊያ ከተማ በሆነችው በቶሪኖ አቅራቢያ በምትገኝ ቶረ ፐሊቼ ከተማ የቤተክርስቲያን መሪዎች ዓመታዊ ሐዋርያዊ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ለሚገኙት ለቫልዴስና ለሜቶዲስት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በላኩት መልዕክታቸው፣ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወንድማዊ ግንኙነት የጠበቀ እንደሆነ ገልጸዋል።

ያለፈው እሁድ በተደረገው የጉባኤው መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያሰሙትና የጉባኤው አስተባባሪው አቶ ኤውጀኒዮ በርናርዲኒ እንደገለጹት ሁላችንም የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና ለማወጅ ተጠርተናል። ይህ አገልግሎት በሕይወታችን ሊገለጥ የሚችለው በሮቻችንን ለሚያንኳኩ በርካታ ሰዎች የእርዳታ እጆቻችንን በቸርነት ስንዘረጋላቸው ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክታቸው እንደገለጹት በዘመናችን በከባድ ችግር ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ከልብ በማገልገል፣ በሕብረተሰባችን መካከል የአቅመ ደካማ ሰዎች ስብዕና በማስከበር፣ ፍትህንና ሰላምን በማራመድ፣ በጋራ ሆነን የትንሳኤውን ክብር በጋራ እንድንመሰክር ተጠርተናል ብለዋል።

ሁለቱን አብያተ ክርስትያናት በመወከል በጉባኤው ላይ የተገኙት 180 የቤተክርስቲያን አባቶች በቀዳሚነት ከተወያዩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል፣ የቤተክርስቲያን ሚና በሕዝቦች ማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ፣ የበጎ አገልግሎትና ስብከተ ወንጌል፣ ስደት እና የአብያተ ክርስቲያናት ውሕደት የሚሉ ይገኙባቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋይ የቤተክርስቲያን አባቶች በላኩት መልዕክት በጋራ በምናቀርበው ጸሎት፣ ክርስቲያኖች በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር በሕብረት የምናደርገውን ጉዞ በታማኝነት፣ ለአንድነት ያለን ምኞት ፍሬያማ እንዲሆን መጸለይ ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን በማድረግ ብቻ የእግዚአብሔርን የአንድነት ጥሪና የወንጌል ምስክርነት ፍሬያማ በሆነ መንገድ ማከናወን እንችላለን ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት ከእነዚሁ የሐይማኖት መሪዎች ጋር በአርጀንቲና፣ በሰሜን ጣሊያን ከተማ በሆነችው በቶሪኖና በሮም ያደረጉትን ስብሰባዎች አስታውሰው ሐዋርያዊ ቡራኬ አቸውን ልከው የሐይማኖት አባቶቹ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

ከመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል ጉባኤውን በተጋባዥ እንግድነት እንዲካፈሉ የተጋበዙት በኢጣሊያ የሎዲ ሃገረስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማውሪሲዮ ማልቨስቲቲ እና በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የአብያተ ክርስቲያናት ውሕደት እና ሃይማኖታዊ ውይይቶች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ዳይረክተር የሆኑት ክቡር አባ ክርስቲያኖ በተጋ መሆናቸው ታውቋል።

በኢጣሊያ የሜቶዲስት ወንጌላዊያን ሕብረትና የባልዴሲያን ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን በ1967 ዓ. ም. ሕብረት እንደመሠረቱ ይታወቃል።  የሕብረት ጠቅላላ የምዕመናን ቁጥር 50,000 እንደሚደርሱ ሲገመት ከእነዚህም መካከል 45,000 የቫልዴስ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን አባላትና በቁጥር የሚበልጡ በኢጣሊያ፣ የተቀሩት በአርጀንቲናና በኡሩጓይ የሚገኙ ሲሆን የተቀሩት 5,000 ደግሞ የሜቶዲስት ወንጌላዊያን ሕብረት አባላት መሆናቸው ታውቋል። 

31 August 2018, 16:06