ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ፦የእግዚአብሔርን ሥራ ለመፈፀም በቅድሚያ በኢየሱስ ማመን ያስፈልጋል!

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮስ፦የእግዚአብሔርን ሥራ ለመፈፀም በቅድሚያ በኢየሱስ ማመን ያስፈልጋል!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ እንደ  ሚያደርጉ፣ ከዚያም በመቀጠል በካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ምዕመናን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማሪያም ከሚቀርቡት ጥንታዊ የመማጸኛ ጸሎቶች መከከል አንዱ የሆነውን “የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት”  የሚለውን ጸሎት ከምዕመናን ጋር በመቀባበል እንደ ሚደግሙ እና ከዚህም ጸሎት በመለጠቅ ለዓለም ሳምንታዊ መልእክት እደ ሚያስተላልፉ ይታወቃል።

በዚህ መሰረት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 29/2010 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን እና የሀገር ጎብኚዎች ያሰሙት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል (6፡25-35) ላይ ተወስዶ በተነበበው እና ኢየሱስ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” ማለቱን በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ ለመረዳት ተችሉዋል።

“አንድን ሐይማኖት ማክበር ማለት ሕግጋቶቹን ብቻ ጠብቆ መሄድ ማለት ነው ወደ ሚለው አስተሳሰብ ማውረድ ተገቢ አለመሆኑን” የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ ነገር ግን በተቃራኒው በክርስቶስ ማመን ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ በመረዳት “በቅዱስ ወንጌል መዓዛ የታወዱ መልካም ሥራዎችን ለወንድሞቻችን በጎ እና ጠቃሚ የሆኑ ተግባሮችን ማከናወን ማለት ነው” ብለዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኋይሌጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ከቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሐምሌ 29/2010 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ያሰሙትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ

በእነዚህ በመጨረሻዎቹ ቅርብ ጊዜያት ባሳለፍናቸው እለተ ሰንበቶች ውስጥ በስርዓተ አምልኮ ወቅት የተነበቡልን ምንባባት ኢየሱስ በርኅራኄ ሕዝቦቹን ለመገናኘት እና ችግሮቻቸውን ለመፍታት ወደ እነርሱ መሄዱን የሚገልጹ እንድምታዎችን አሳይተውናል። ዛሬ በተነበበልን ቅዱስ ወንጌል ውስጥ (ዮሐንስ 6፡24-35) ያለው እይታ ግን ሲለወጥ እናያለን፣ አሁን ደግሞ ኢየሱስ የመገባቸው እና ከርሃባቸው ያላቀቃቸው ሕዝቦች በፊናቸው በአዲስ መልክ ኢየሱስን ለመፈለግ እና ለመገናኘት ሲሄዱ እንሰማለን። ኢየሱስ የሚፈልገው ሰዎች እርሱን እንዲፈልጉ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሰዎች እርሱን በሚገባ እንዲያውቁት  ጭምር ይፈልጋል፡ እኛ እርሱን የምንፈልገው እና እርሱን ለመገናኘት የምናደርገው ጥረት ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን ፈጣን በሆነ መልኩ ለማርካት ካለን ፍላጎት ባሻገር እንዲሆንም የፈልጋል። እኛ ለእለታዊ ኑሮዋችን በማሰብ ምን እንበላለን፣ ምን እንለብሳለን፣ ምን እንሠራልን. . .ወዘተርፈ ከሚሉት ጭንቀቶች ይልቅ ኢየሱስ ከእነዚህ የተሻሉ ተጨማሪ ነገሮችን ሊሰጠን እና ሰፊውን የሕይወት አድማስ በምልኣት ሊከፍትልን መጥቱዋል። ለእዚህም ነው ታዲያ ኢየሱስ ወደ ሕዝቡ እየተመለከተ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም” (ዮሐንስ 6፡29) በማለት የመለሳላቸው በዚሁ ምክንያት ነው። ስለዚህ ሕዝቦቹ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመዱ፣ እርሱ በፈጸመው ተዐምር ተጠቃሚ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን ስለ ታምራቱ ምንነት ጭምር በጥልቅ እንዲያስቡ ያነሳሳቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ አምስት ትንንሽ የገብስ እንጀራና ሁለት ትንንሽ ዓሣ እንዲበዛ ተደርጎ መባረኩ አብ እና ኢየሱስ ራሱ ለሰው ልጆች የሰጡት ታላቅ ስጦታ ነው!

እርሱ ጥልቅ የሆነ አካላዊ ረሃባችንን ብቻ የሚያረካ ሳይሆን ነብሳችንን የሚያረካ መንፈሳዊ ምግባችን የሆነ እውነተኛ “የሕይወት እንጀራ” (ዮሐንስ 6፡29) ነው። ለዚህም ነው ኢየሱስ “ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ” (ዮሐንስ 6፡29) በማለት ሕዝቡን የጋበዘው በዚህ ምክንያት ነው። ይህም ኢየሱስ በየእለቱ በቃሉ፣በሥጋው እና በደሙ የሚሰጠንን ምግብ ያመለክታል። አብዛኛውን ጊዜ እኛን እንደ ሚያጋጥመን ሁሉ ሕዝቡ የኢየሱስን ጥሪ ተቀብለው የነበረ ቢሆንም ቅሉ ምን ማለት እንደ ሆነ በቅጡ አልተረዱትም ነበር፦ በዚህም ምክንያት ሕዝቡ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” (ቁ። 28) በማለት ይጠይቁታል። በወቅቱ የነበሩ የኢየሱስ አድማጮች ያሰቡት ኢየሱስ ቀደም ሲል በጥቂት ዳቦ እና ዓሳ  አምስት ሺህ ሕዝብ መመገቡን በተመለከተ ያላቸውን አስተያየት ጠይቁዋቸው ሌላ ተጨማሪ ተዐምር እንዲያሳያቸው የሚጠይቃቸው መስሉዋቸው ነበር። ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በተመለከተ በአገልጋዮች እና በጌታቸው መካከል ያለውን ልዩነት በማንጸባረቅ አገልጋዮች የጌታዎቻቸውን ቀልብ ለመሳብ ጌታቸው የሰጣቸውን ተግባራት ብቻ የግድ ማከናወን ይኖርባቸዋል የሚለውን አስተሳሰብ በማስተጋባት ሃይማኖት ከሕግጋት ጋር ብቻ የተሳሰረ አሠራርን የሚከተል ነው ወደ ሚለው አስተሳሰብ በማምጣት አሳቡን ለማጥበብ የሚደረግ የተለመደ ፈተና ነው። ይህንን ደግሞ ሁላችንም በሚገባ የምናውቀው ነገር ነው። ስለዚህ ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ምን ማድረግ እንዳለበት ከኢየሱስ ለማወቅ በመፈለግ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?”(ቁ.28) በማለት በጠይቁት ወቅት ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” (ቁ. 29) በማለት  ያልጠበቁትን መላሽ ይሰጣቸዋል። ዛሬም እነዚህ ቃላት እኛን ይመለከቱናል፣ የእግዚአብሔር ሥራ የሚሠራው "በማድረግ" ብቻ ሳይሆን ነገር ግን እርሱ በላከው "በማመን" ጭምር ሊሆን የገባል። ይህም ማለት በኢየሱስ ማመን የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ይፈቅድልናል ማለት ነው። በዚህ የፍቅር ግንኙነት እና በኢየሱስ እምነት ውስጥ ራሳችንን ለማስገባት ከፈቀድን በቅዱስ ወንጌል መልካም መዓዛ የታወደ በጎ እና መልካም የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት የወንድሞቻችንን ፍላጎቶች ለሟሟላት እንችላለን።

የእዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት ከዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ

Photogallery

ምዕመናን በሐምሌ 29/2010 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ
06 August 2018, 14:38