ፈልግ

2015.09.26 Festa delle Famiglie-Veglia, USA 2015 2015.09.26 Festa delle Famiglie-Veglia, USA 2015 

አንድሬያ ቦቼሊን በዳብሊን መዝሙር ሊያቀርብ መዘጋጀቱ አስደስቶታል።

ታዋቂው ድምጻዊ አርቲስት አንድሬያ ቦቼሊ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ በመጭው ነሐሴ 19 ቀን 2010 ዓ. ም. በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመላው ዓለም ከሚመጡት የቤተሰብ አባላት ጋር በሚገኙበት ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤ ላይ መዝሙሮችን እንደሚያቀርብ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ታዋቂው ድምጻዊ አርቲስት አንድሬያ ቦቸሊ፣ በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን፣ ኮርክ ስታዲየም ውስጥ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትና ከመቶ አገሮች በላይ ለሚመጡት የቤተሰብ አባላት መዝሙር ዝግጅት እንደሚያቀርብ የታወቀ ሲሆን ድምጻዊው ይህን የመሰለ ዝግጅት ሲያቀርብ የመጀመሪያው እንዳልሆነ፣ ከዚህ በፊትም በሰሜን አሜርካ ከተማ በሆነችው በፊላዴልፊያ በ2007 ዓ. ም. በተደረገው የቤተ ሰብ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ በመገኘት ተመሳሳይ ዝግጅት አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። ድምጻዊው ከዚህ ዝግጅት በኋላ ወደ አገሩ፣ ወደ ኢጣሊያ በመመለስ በቨሮና ከተማ፣ ለተረጂዎች የእርዳታ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እንደሚያቀብ ታውቋል። ድምጻዊው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ልዩ የቃለ ምልልስ ወቅት እንደገለጸው እምነት በሕይወቱ ውስጥ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ገልጾ፣ በአይር ላንድ፣ ዳብሊን ከተማ የሚያቀርበው የመዝሙር ዝግጅት ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ የቤተሰብ አባላት የደስታንና የፍቅር ሕይወትን እየኖሩ ምስክርነትን እንዲሰጡ ያግዛቸዋል ብሏል። ድምጻዊው በማከልም በዚህ የመንፈሳዊ ለውጥ እንዲመጣ በትጋት የሚሰብኩ ታላቅ የቤተ ክርስቲያን አባት የሆኑ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚገኙበት የቤተሰብ ጉባኤ ላይ በመገኘት ምዝሙሮቼን ሳቀርብ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል ብሏል። በማቀርባቸው መዝሙሮች አማካይነት ቤተ ሰብን የሚያንጹና የሚጠቅሙ መልዕክቶችን እንዳስተላልፍ ትልቅ ሃላፊነት ተጥሎብኛል ብሏል። ስለዚህ ከዚህ በፊትም እንዳደርኩ ሁሉ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የማስተላልፈውን መልዕክት ቤተ ሰብ ተቀብለውኝ ወደ መጡበት ስፍራ ወይም አገር የሚወስዱት መልካም ማስታወሻ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ ብሏል።

ይህን በመሰለ አጋጣሚ ለሚቀርቡት የመዝሙር ዝግጅቶች ከታዳሚዎች የሚሰጠው ምስጋና እጅግ ትልቅ በመሆኑ እኔም የዚህ ምስጋና ተቋዳሽ እንደምሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብሏል። የአይር ላንድ ሕዝብም ከዚህ በፊት ሲያከብረኝና ሲወደኝ የቆየ በመሆኑ እርጋታ እና ደስታ ይሰማኛል ብሏል። ታዋቂው ድምጻዊ አርቲስት አንድሬያ ቦቸሊ በማከልም የመዝሙር አገልግሎቴ ዋና ዓላማ ለሚሰማኝ አድማጭ ደስታንና የተረጋጋ ጊዜን በመስጠት በማንኛውም ሁኔታ የሚገኝ ሰው ለጸሎቱም ሆነ ለአስተንትኖ የሚያግዝ የመንፈስ ቅዱስ እገዛን እንዲያገኝ ነው ካለ በኋላ ቅዱስ አጎስጢኖስ የሚዘምር እጥፍ ይጸልያል ማለቱንም አስታውሶ፣ ይህ እውነት ከሆነ በሕይወት ዘመኔ ባቀረብኳቸው መዝሙሮቼ እጥፍ በመጸለዬ ደስታ ይሰማኛል ብሏል። 

በዚህ ዓለም እንደሚገኙ እንደ ማንኛውም አርቲስት፣ እንድዘምር የተሰጠኝ ድምጽ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ አምናለሁ። በዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም። በምድር ላይ የሰው ልጅ በሕይወቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ወደ ግብ ማድረስ የሚችለው ከእግዚአብሔር በሚሰጠው ስጦታ በመታገዝ ነው። ስለዚህ የግል ችሎታ ባልሆነ ሁሉ እግዚአብሔርን ከማመስገን በቀር ምንም መኩራራት አስፈላጊ አይሆንም። እምነትም የሕይወታችንን ትርጉም እንድንገነዘብ የሚረዳን ዕለታዊ ጉዞ ነው። በእምነት ሳይታገዝ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ የሚያስብ ሰው ራሱን ከወዴት እንደመጣ ሊያውቅ አይችልም። አንድን ሐውልት ማን እንደቀረጸው ሳይረዳ፣ ሐውልቱ በድንገት የመጣ ግዙፍ መሆኑን ብቻ ተረድቶ እንደሚመለስ ተመልካች ነው። ለእኔ የእምነት ሕይወት፣ ዓለማችን የተገኘው ከእኛ የማሰብ ችሎታ በላይ በሆነ ሃይል ብቻ ሳይሆን በእውነተኛ ፍቅርም ጭምር የታገዘ እንደሆነ ለማወቅ አስችሎኛል፣ ብሏል።          

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚገኙበት ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤ በአይር ላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ሊካሄድ ሁለት ሳምንታት ብቻ እንደሚቀረው የሚታወቅ ሲሆን የጉባኤ ተካፋዮችም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ የቤተሰብ አባላት፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ልጆች፣ የቤተክርስቲያን አባቶች፣ በቤተሰብ ዙሪያ ጥናት የሚያደርጉ የማሕበረ ሰብ ጠቢባን እና የአብያተ ክርስቲያናት አባቶች እንደሚሆኑ ታውቋል።  

16 August 2018, 17:31