ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 

ር. ሊ. ጳ. በረሃብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወንድሞቻችንን በዝምታ ማለፍ የለብንም

በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች፣ በረሃብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እየተመልከትን በዝምታ ማለፍ የለብንም

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ ከሚያደርጉት ከእኩለ ቀኑ የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በፊት በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖን እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በትላንትናው ዕለት ማለትም እሁድ ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓ. ም. ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1–15 በተነበበው የወንጌል ክፍል ላይ ባደረጉት አስተንትኖ እንደገለጹት፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች፣ በረሃብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እየተመልከትን በዝምታ ማለፍ የለብንም ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም ዜና አብሳሪ መሆን፣ ለድሆች፣ ረዳት ለሌላቸው አቅመ ደካሞች እና ለተናቁትም በሙሉ ቸርነትንና ደግነትን እንድናሳይ ያስገድደናል ብለዋል። በግልም ይሁን በጋራ በምናደርጋቸው መልካም ሥራዎቻች፣ የእምነታችን እውነተኛ መስካሪ መሆን የምንችልበት መንገድ ይህ ነው ብለዋል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ፣

ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6፤ 1–15 ) የተነበበው የዛሬው የወንጌል መልዕክት የሚያስታውሰን፣ ጥቂት ዳቦ እና ዓሣ ተባዝቶ ለብዙ ሕዝብ እንዲበቃ የተደረገበትን ሁኔታ ይገልጻል። ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ ቀና ብሎ አየና፣ ከሐዋርያቶቹ መካከል አንዱ የሆነውን ፊሊጶስን ‘ለዚህ ሁሉ ሰው የሚበቃ ምግብ ከየት መግዛት እንችላለን’ አለው። ኢየሱስና ሐዋርያት የያዙት በጣም ትንሽ ገንዘብ፣ ለዚህ ብዙ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሊገዛ አይችልም ነበር። ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው እና የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም፣ እንድሪያስ፣ በኮሮጆው ውስጥ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ የያዘ አንድ ልጅ ወደ ኢየሱስ ዘንድ አቀረበው፣ ይህ ልጅ ‘እኔ ያለኝ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ ስለሆነ፣ የሚጠቅማችሁ ከሆነ ልሰጣችሁ እችላለሁ’ አለ። ይህ ወጣት አንድን ነገር እንድናስታውስ አድርጎናል። ይህም፦ ስለ ወጣቶች ድፍረት ነው። ወጣቶች ደፋሮች ናቸው። ስለዚህ ይህን ድፍረታቸውን እንዲቀጥሉበት ልንረዳቸው ይገባል። ኢየሱስም ሐዋርያቶቹን፣ ሕዝቡ እንዲቀመጡ አድርጉ ካለ በኋላ እነዚያን ጥቂት ዳቦ እና ጥቂት ዓሣ አንስቶ የምስጋና ጸሎት ወደ አባቱ ዘንድ ካቀረበ በኋላ ለተቀመጡት ሰዎች እንዲያድሉ አዘዛቸው። ሁሉም እስኪጠግቡና፣ እስኪተርፋቸው ድረስ በሉ።

ይህ የዛሬው የወንጌል ንባብ፣ ባለፈው እሁድ የተነበበውን የማርቆስ ወንጌል እንድናስታውስ ያደርገናል። በዚህም የወንጌል ክፍል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይከተሉ ለነበሩ ብዙ ሰዎች እንደራራላቸው የሚያስረዳ ነበር። በዮሐንስ ወንጌልም፣ በምዕ. 6 ላይ እንደተገለጸው፣ አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ የያዘ አንድ ልጅም፣ ርህራሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ ተረድቶአል። ለራሱ ብሎ የያዘውን ምግብ በሙሉ አውጥቶ እንዲሰጥ ያስገደደው ሌላ ሳይሆን ለዚያ ተርቦ ለነበረ ብዙ ሕዝብ የነበረው የርህራሄ ልብ ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች መሠረትዊ ፍላጎቶች ምን ያህል ጥንቃቄ እንደሚያደርግና እንደሚጨነቅ ያሳየናል። ከተጨባጭ እውነታ በመነሳት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱን በማስተባበር፣ ያ የተራበው ሕዝቡ ጠግቦ በልቶ ረሃቡን እንዲያስታግስ አደረገ። ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ሕዝብ ምግብ ብቻ በማቅረብ አላበቃም። የሚጽናኑበትን ቃል በማሰማት፣ የሚድኑበትን መንገድ በማዘጋጀት፣ በመጨረሻም ሕይወቱን አሳልፎ እስከ መስጠት ደርሷል። ኢየሱስ ክርስቶስ በእርግጥ ለሰውነት የሚያስፈልገውን ምግብ ማቅረብንም አልዘነጋም። ይህን ሁሉ እያየን፣ የእርሱ ደቀ መዛሙርት የሆንን እኛ፣ ዛሬ የሰዎችን ችግር እና ስቃይ አይተን እንዳላየን፣ ወይም ሰምተን እንዳልሰማን መሆን የለብንም። በጣም ቀላል የሆኑ የሰዎች ችግሮችን ማቃለል ከቻልን፣ ቀስ በቀስ ትልቅ መስዋዕትነት እንድንከፍል የሚያደርጉ ችግሮችንም ማቃለል እንችላለን።

የእግዚአብሔር አባታዊ ፍቅር፣ የዕለት እንጀራን፣ ነጻነትን፣ ፍትህን እና ሰላምን ለሚናፍቁ፣  ከሁሉም በላይ ደግሞ መለኮታዊ ጸጋን ለሚለምኑ በሙሉ እጅግ አብዝቶ ይሰጣቸዋል እንጂ አያሳጣቸውም። ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ቢሆን የዕለት እንጀራ ለሚያስፈልጋቸው፣ የመጽናናትን ቃል ለሚፈልጉ በሙሉ በእኛ በደቀ መዛሙርቱ በኩል ሳያቋርጥ ያቀርብላቸዋል። ‘አምስት ዳቦ እና ሁለት ዓሣ ስላለኝ የሚጠቅማችሁ ከሆነ ልሰጣችሁ እችላለሁ።’ እንዳለው ወጣት፣  እኛም ደጎችና ትሁቶች እንድንሆን ወንጌል ይጋብዘናል። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች፣ በረሃብ እየተሰቃዩ የሚገኙ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እየተመልከትን በዝምታ መመልከት አንችልም። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አብሳሪነት፣ ለድሆች፣ ረዳት ለሌላቸው አቅመ ደካሞች እና ለተናቁትም በሙሉ ቸርነትንና ደግነትን እንድናሳይ ያስገድደናል። በግልም ይሁን በጋራ ለምናደርጋቸው መልካም ሥራዎቻችን በሙሉ፣ የእምነታችን ምስክርነት ውናው መገለጫ ይህ ነው።

ወደ ዛሬው የወንጌል መልዕክት ስንመለስ፣ ሕዝቡ የቀረበለትን ምግብ በልቶ ከጠገበ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ እንዲሰብስቡ አዘዛቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን ይህን ዓረፍተ ነገር በድጋሚ ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ። ‘አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ፣ የተረፈውን ምግብ ቍርስራሽ ሰብስቡ።’ ይህን የምልበት ምክንያት በዓለማችን በርካታ ሕዝብ ተርቦ ሳለ፣ እንዲሁ በከንቱ የሚጣል ብዙ ምግብ እንዳለ በማሰብ ነው። ከቁርሳችን፣ ከምሳችን፣ እንዲሁም ከእራታችን የሚተርፈውን  ምግብ ምን እናደረጋለን ብለን ማሰብ ይኖርብናል። በየቤታችሁ ‘ይህ ምግብ ትርፍ ነው’ ብላችሁ አውጥታችሁ የምትጥሉ ከሆነ እስቲ የረሃብን ምንነት የሚያውቁትን፣ ያንን ክፉ የጦርነት እና የረሃብ ጊዜን ያሳለፉ አያቶቻችሁን፣ ሲበሉ የተረፈ ምግብ ካለ ምን ያደርጉ እንደነበር እስቲ ጠይቋቸው። ለሌላ ለተራበ ጎረቤት ወይም ሰው ይሰጣል እንጂ ምግብ ፈጽሞ አይጣልም። ኢየሱስም የፈለገው፣ የተራበ ሰው ካለ ምግብ በመስጠት ተገቢው እንክብካቤ ለማድረግ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ፣ መላው የሰው ልጅ በሙሉ በምድራችን ላይ ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ከማውደም ወይም ከማጥፋት ይልቅ በመንከባከብ ለሰው ልጅ የጋራ እድገት ማዋል ያስፈልጋል።

በዓለማችን ከጥላቻ እና ከጦርነት ይልቅ ለሰው ልጆች እድገት የተወጠኑ እቅዶች፣ ከእነዚህም መካከል በቂ የዕለት እንጀራን የማቅረብ፣ ለዚህም በጋራ አብሮ የመሥራት እቅዶች ፍሬያማ እንዲሆኑ ለማድረግ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታግዘን በጸሎታችን እንማጸናታለን።

31 July 2018, 09:17