ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ. ም. በቫቲካን ያደረጉት የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ. ም. በቫቲካን ያደረጉት የብስራተ ገብርኤል ጸሎት 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ያለ ክርስቶስ ምንም ዓይነት መገለጫ ሊኖረን አይችልም

ሐዋርያት ከመጀመሪያ ተልዕኮአቸው በተመለሱ ጊዜ፣ በሄዱበት ኣካባቢ ያከናውኑትን ተግባራት እና ያስተማሩትን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነገሩት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ ከሚያደርጉት ከእኩለ ቀን የብስራተ ገብሬል ጸሎት በፊት በዕለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተመርኩዘው አስተንትኖ እንደሚያደርጉ የሚታውወቅ ሲሆን በዚህም መሠረት በትላንትናው ዕለት ማለትም እሁድ ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ. ም. ከማርቆስ ወንጌል ምዕ. 6 ከቁጥር 30 – 34  በተነበበው ወንጌል ላይ ተመርኩዘው ባደረጉት አስተንትኖ እንደ ገለጹት ያለ ክርስቶስ ምንም ዓይነት መገለጫ ሊኖረን አይችልም ማለታቸውን ለመረዳት ተችሏል። ክቡራንና ክቡራት አድማጮቻችን የዚህን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደ ምን አረፈዳችሁ፣

የዛሬው የወንጌል መልዕክት (ከማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ከቁጥር 30 – 34 ) የተነበበው የሚያስታውሰን፣ ሐዋርያት ከመጀመሪያ ተልዕኮአቸው በተመለሱ ጊዜ፣ በሄዱበት ኣካባቢ ያከናውኑትን ተግባራት እና ያስተማሩትን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነገሩት። በቅንነት፣ ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ አገልግሎታቸውን ስላበረከቱ ድካም ተሰምቶአቸው ነበርና ማረፍ ፈለጉ። ኢየሱስም ድካማቸውን ስለተረዳ፣ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው። በዚህን ጊዜ የኢየሱስን ሃሳብ በሚገባ መረዳት ያስቸግር ነበር። ምክንያቱ ሐዋሪያቱን ብቻችሁ ወደ በረሃ ሂዱ እና እረፉ በሚልበት ሰዓት በርካታ ሰዎች፣ እርሱ ከሐዋርያቱ ጋር ወደ ነበረባት ጀልባ ድረስ ይጎርፉ ነበር። 

ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ሁኔታ ሲከሰት እንመለከታለን። አንድን እቅድ ለመፈጸም ተነስተን እያለን ሌላ ቅድሚያ ሰጥተን ማከናወን ያለብል ጉዳይ ይከሰታል። ይህም በመሆኑ አስቀድመን የጀመርነውን እቅድ አስቀምጠን ወደ ሌላው እንድንሄድ እንገደዳለን። ይህን በምናደርግበት ጊዜ ልክ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ለማድረግ እንገደዳለን ማለት ነው።

በማርቆስ ወንጌል በምዕራፍ 6 ቁጥር 34 ላይ እንደተገለጸው፣ ኢየሱስም ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ እየመጡ መሆኑናቸውን በተመለከተ ጊዜ  እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ ራራላቸው። ተቀብሎአቸውም ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር። በዚህ አጭር አረፍት ነገር፣ ወንጌላዊ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን የማስተማር ዝንባሌ ከወዴት የመጣ፣ ምንን ዓላማ አድርጎ ያደረገ እንደሆነ፣ እንድመለከት እና እንድናስተውል ያግዘናል። በወንጌላዊው አገላለጽ ሦስት ግልጽ የሆኑ ቃላት ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን። እነርሱም መመልከት፣ መራራት እና ማስተማር የሚሉ ናቸው። እነዚህ ሦስቱ ቃላት የአንድን የወንጌል መልዕክተኛ የአገልግሎት መንገድ የሚገልጹ ቃላት ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ እነዚያን በርካታ ሰዎችን ያየው ወይም የተመለከታቸው በወገናዊነት፣ አስፈሪ በሆነ አስተያየት፣ ወይም በግድ የለሽነት ዓይን አልነበረም። የእርሱ አስተያየት እና አመለካከት የርህራሄ እና የፍቅር፣ ከልብም የመነጨ ነበር። ልቡም ዘወትር የሚራራ እና የሚጨነቅ፣ ሰዎች ገልጸው መናገር የማይፈልጉትንና የሰወሩትን ችግሮችን ሳይቀር የሚያውቅ እና የሚረዳ ነው። ለሰዎች ያለው የርህራሄ እና የጭንቀት ልብ ስሜታዊ ወይም ለጊዜው በሚሰማው ስሜት ተነሳስቶ ሳይሆን ከዚያ ባለፈ መልኩ፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በዘመናት መካከል ሁሉ የሚያሳየውን ጥንቃቄን እና ጥበቃን የሚያካትት ነው። ኢየሱስም ይህን የእግዚአብሔርን አለኝታ፣ በዘመናት መካከል ሁሉ ለሕዝቦቹ የሚያደርገውን ጥበቃ እና ርህራሄ በተግባር ለመግለጽ የተነሳ እንደሆነ እንገነዘባለን።

ኢየሱስም ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ መምጣታቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ፣ እንደ ራራላቸው ተመልክተናል። ይህን በማየቱ የመጀመሪያ ሥራው ተዓምራትን መሥራት ይሆናል ብለን እናስብ ይሆናል። ነግር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራትን ከማድረግ ፈንታ የመጀመሪያ ሥራው፣ የሚያጽናናቸውን፣ የሚያበረታታቸውን ቃሉን ማስተማር እና መስበክ ነበር። እኛ ሁላችንም ለመንገዳችን ብርሃን በመሆን የሚመራንን የእውነት ቃል መስማት እና ማዳመጥ እንፈልጋለን። የእውነት መንገድ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ ትክክለኛ የሕይወታችን መሪ ማግኘት አንችልም። ከዚህ እውነተኛ የሕይወታችን መሪ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የራቅን እንደሆነ ግን ወደ ተስፋ ማጣት እንደርሳለን፣ እርካታንም ልናገኝ አንችልም፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ከያዝን ግን እውነተኛ መተማመኛንን በማግኘት ፈተናዎቻችንን እናልፋለን፣ በፍቅር በመሞላት ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ባልንጀሮቻችን መቅረብ እንችላለን። ኢየሱስም ክርስቶስም ለሌሎች ደህንነት ብሎ ራሱን በመስጠት፣ ዘለዓለማዊ እና እውነተኛ በሆነው ፍቅሩ እያንዳንዳችንን ሊያገለግለን ፈልጓል።

እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ የሌሎችን ችግሮች መሸከም የምንችልበትን፣ ስቃዮቻቸውንም ለመካፈል የምንችልበትን ጉልበት እንድናገኝ ታግዘን።

22 July 2018, 16:37