ፈልግ

“ወጣቶች የመሸጋገሪያ ድልድይ ገንቢዎች እና የምሕረት መሳሪያዎች “ ሊሆኑ ይገባል

31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን በክራኮቪያ “ወጣቶች የመሸጋገሪያ ድልድይ ገንቢዎች እና የምሕረት መሳሪያዎች “ ሊሆኑ ይገባል

“ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው ምሕረትን ያገኛሉና” (ማቴ. 5፡7) በሚል መሪ ቃል የዛሬው ሁለት አመት ገደማ (በኢትዮጲያ የቀን አቆጣጠር በሐምሌ 20/2008 ዓ.ም ማለት ነው) ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን ጨምሮ ከአለም ዙሪያ የተውጣጡ ከሦስት ሚልዮን በላይ የሚገመቱ ወጣቶች በተገኙበት 31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን በፖላንድ በክራኮቪያ ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ ማለፉ ይታወሳል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ - ቫቲካን

ክራኮቪያ እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ1978-2005 ዓ.ም (ለ27 አመታት ማለት ነው) የካቶሊክ ቤተክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የትውልድ ስፍራ እንደ ሆነች የሚታወቅ ሲሆን የዛሬው ሁለት አመት ገደማ በእዚሁ ስፍራ የተካሄደው 31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን ትኩረቱን አድርጎ የነበረው  “ወጣቶች የመሸጋገሪያ ድልድይ ገንቢዎች እና የምሕረት መሳሪያዎች ሊሆኑ ይገባል” በሚል ጭብጥ ዙሪያ የተካሄደ የወጣቶች ቀን እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በተለይም ደግሞ አዲሱ ትውልድ “ብዝሃነታቸውን ከግምት ባስገባ መልኩ መንፈሳዊ ለውጥ” በአለም ውስጥ እንዲመጣ የራሳቸውን አሻራ ጥለው እንዲያልፉ የመከረ እና የዘከረ አለማቀፍ የወጣቶች ቀን እንደ ነበረ ይታወሳል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዛሬ ሁለት አመት በዚሁ 31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለመሳተፍ ክራኮቪያ በደረሱ በማግስቱ በዚያው በሚገኘው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ስም በተሰየመው ታዋቂ እና ጥንታዊ ቤተመቅደስ ተገኝተው የፓላንድ ሕዝብ የካቶሊክን እምነት በይፋ የተቀበለበት 1050ኛው አመት በተዘከረበት ቀን መስዋዕተ ቅዳሴን ማሳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከ500ሺ በላይ ምዕመናን መሳተፋቸው ይታወሳል።

ቅድስት ፋውስቲና የመልኮታዊ ምሕረት ሐዋሪያ ናት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዛሬ ሁለት አመት ይህንኑ 31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን መሳተፍ በጀመሩበት በሁለተኛው ቀን የነበረውን የቅዳሜ ዕለት “የምሕረት ቀን” ብለው ሰይመውት እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን ይህንን የምሕረት ቀን ለመዘከር በክራኮቪያ በሚገኘው በእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ስም በተሰየመው መልኮታዊ ምሕረት በመባል በሚታወቀው ቤተመቅደስ ተገኝተው ጸሎት ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህ ቤተመቅደስ “የመለኮታዊ ምሕረት ሐዋሪያ” በመባል የምትታወቀው ቅድስት ፋውስቲና ቅዱስ የሆነው ቅሪት አካሉዋ የሚገኝበት ቤተመቅደስ እንደ ሆነ ይታወቃል፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዚያው ስፍራ ተገኝተው በቅድስት ፋውስቲና መካነ መቃብር አጠገበ በተሰቀለው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊ ምሕረት በሚያሳየው ምስል ስር ተንበርክከው ጸሎት ማድረሳቸው የሚታወስ ሲሆን ቅድስት ፋውስቲና በሕይወት በነበሩበት ወቅት አብዛኛውን ጊዜ በዚሁ “የኢየሱስን መለኮታዊ ምሕረት” በሚያመለክተው ምስል ሥር ተንበርክከው “ኢየሱስ ሆይ! በአንተ እታመናለሁ!” በማለት ይጸልዩ እንደ ነበረ ከሕይወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሉዋል።

ቅዱስ ወንጌል “የሕይወት መንገዳችንን በትክክል እንድንራመድ ያደርገናል”!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዛሬ ሁለት አመት በዚሁ 31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን ማጠናቀቂያ ላይ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቅዱስነታቸው ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት በዚሁ በ31ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶች ወደ መጡበት ሥፋር በሚመለሱበት ወቅት “የምሕረት ሐዋሪያ እና የእግዚኣብሔር ምሕረት መስካሪዎች በመሆን” ወደ መጡበት እንዲመለሱ ቅዱስነታቸው ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ሁል ጊዜም ቢሆን “በሕይወታችሁ መንገድ ላይ በትክክል መራመድ እንድተችሉ፣ የሕይወታችሁ መንገድ አቅጣጫውን ጠብቆ እንዲሄድ የሚያደርገውን ቅዱስ ወንጌልን በመርህነት መጠቀም እንዳትረሱ”  በማለት ለተሳታፊ ወጣቶች ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

መጪው 32ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን እ.አ.አ በ2019 በፓናማ ይከበራል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የዛሬ ሁለት አመት በዚሁ 31ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን ማብቂያ ላይ ካሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በመቀጠል ለወጣቶች ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት መጪው 32ኛው አለማቀፍ የወጣቶች ቀን እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ2019 ዓ.ም በፓናማ እንደ ሚከበር መገለጻቸው የሚታወስ ሲሆን ወጣቶች በያሉበት ቦታ ሁሉ የክርስቶስ ብርሃን እንዲበራ የራቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል የሚል ይዘት ያለው መልእክት ካስተላለፉ በኋላ 31ኛውን የአለም ወጣቶች ቀን  አጠናቀው ወደ ቫቲካን መመለሳቸው ይታወሳል።

28 July 2018, 11:50