ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ. ፍራንቸስኮ 16/6/2010 ዓ.ም. 52ኛ የመገናኛ ብዙሃን ቀን ያስተላለፉትን ምልእክት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጥር 16/2010 ዓ.ም. በሉርድ በተካሄደው 52ኛ ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ቀን ጉባሄ ላይ ያስተላለፉትን ምልእክት “እውነት ነጻ ያወጣችኃል” (ዩሐንስ 8፡32) “የውሸት ዜና እና ጋዜጠኛ ለሰላም”

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጥር 16/2010 ዓ.ም. በሉርድ በተካሄደው  52ኛ ዓለማቀፍ  የመገናኛ ብዙሃን ቀን ጉባሄ ላይ ያስተላለፉትን ምልእክት

“እውነት ነጻ ያወጣችኃል” (ዩሐንስ 8፡32)

“የውሸት ዜና እና ጋዜጠኛ ለሰላም”

 

ከጥር 16-18/2010 ዓ.ም. ደረስ በቅድስት መንበር የመገናኛ ብዙሃን ጽሕፈት ቤት እና የፈረንሳይ የካቶሊክ የመገናኛ ብዙሃን ማሕበር በጋራ ያዘጋጁት 52ኛው ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ቀን በፈረንሳይ ሀገር ሉርድ በሚባል ስፍራ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩ ይታወሳል።። ይህ 52ኛው ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ቀን “የመገናኛ ብዙሃን እና እውነት” በሚል አርእስት ከተለያየ ሀገር የተውጣቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በተገኙበት ተከብሮ ማለፉ የተገለጸ ሲሆን የቀድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ጴትሮ ፓሮሊን በስፍራው ተገኝተው ይህንን ለሁለት ቀናት ያህል የቆየውን ጉባሄ ተስትፈዋል።

በእዚህ 52ኛ ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ቀን መጀመሪያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ መልእክት ማስተላለፋቸው የተዋቀ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ያስተላለፉት መልእክት “እውነት ነጻ ያወጣችኃል” (ዩሐንስ 8:32) በሚል አርእስት የቀረበ ሲሆን “የውሸት ዜና እና ጋዜጠኝነት ለሰላም”  የሚል መልእክት ያዘለ መሆኑም ተገልጹዋል።

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ታዳሚዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በጥር 16/2010 ዓ.ም. በሉርድ በተካሄደው 52ኛ ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ቀን ጉባሄ ላይ ያስተላለፉትን ምልእክት ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እናግብዛለን።

 

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ

መገናኘት እግዚአብሔር ለእኛ ያለው እቅድ አንዱ አካል ሲሆን ኅብረትን የመፍጠሪያ ወሳኝ መንገድ ነው። በፈጣሪያችን መልክ እና አምሳል በመፈጠራችን የተነሳ፣ እውነት የሆነውን፣ መልካምና ውብ የሆነውን ሁሉ መግለጽና ማጋራት ያስችለናል። የራሳችንን እና በዙሪያችን ያለውን ዓለም ለመግለፅ እንችላለን፣ በዚህም ታሪካዊ ትውስታዎችን እና ክስተቶችን ለመረዳት ያስችለናል። ነገር ግን ለራሳችን ኩራት እና ራስ ወዳድነት ስንጠቀምበት፣ ግንኙነት የምንፍጥርበት ችሎታችንን የምንጠቀምበትን መንገድ የተዛባ ያደርጋል። ይህንንም በጥንት ጊዜያት ውስጥ የተከሰቱትን የቃየል እና የአቤል ታሪክ (ኦርት ዘፍጥረት 4፡4-16) እንዲሁም ስለ ባቢሎን (ኦርት ዘፍጥረት 11፡1-9) በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተጻፉት ታሪኮች ውስጥ ሊታይ ይችላል። እውነትን የመጠምዘዝ  አቅም በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰባችን ውስጥ የእኛ ሁኔታ መገለጫ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ለእግዚኣብሔር እቅድ ታማኝ ስንሆን የመገናኛ ብዙሃንን ለእውነት ለመፈለግ እና መልካም የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ውጤታማ በሆነ መልኩ በኃላፊነት እንድንፈልግ ያደርገናል።

በፍጥነት እያደገ በሚገኘው ዓለማችን ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየተንሰራፋ የመጣው የመገናኛ ብዙሃን እና የረቀቁ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች “ሐሰት የሆኑ መረጃዎችን” በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። ይህም አንድ ጊዜ ቆም ብለን እንድናስብ ያደርገናል፣ እኔም ብሆን ለእዚህ ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ቀን ይህንን መልእክት ለማስተላለፍ የተነሳሳሁት ከእዚህ ቀደም ከእኔ በፊት ከነበሩት ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ 6ኛ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1972 ዓ.ም. “የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለእውነት ጥብቅና መቆም” እንዳለባቸው በማሳሰብ ከጻፉት ቃለ ምዳን አንስቶ በተደጋጋሚ የተነሳ እውነትን የመዘገብ ጥያቄ አደጋ ላይ የወደቀ ጉዳይ በመሆኑ የተነሳ ነው። በእዚህ መንገድ እኔም ብሆን ይህንን በአሁኑ ወቅት እየተሰራጨ ያለውን የሐሰት ዜና ለመዋጋት  የራሴን አዎንታዊ አስተዋጾ ለማደርግ በማሰብ እና የጋዜጠኝነት መልካም እሴቶች በድጋሚ እንዲለመልሙ ለማድረግ እንዲሁም እውነትን መዘገብ የጋዜጠኞች ግላዊ ኃላፊነት መሆኑን ለመገልጽ ነው።

1. የውሸት ዜናዎች ውስጥ “ውሸት” የሆነው ነገር ምንድነው?

ይህ “የውሸት ዜና” የሚለው ሀረግ በጣም ሰፊ ውይይት እና ክርክር የተደረገበት አርእስት ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በማኅበራዊ የመገናኛ መስመሮች ላይ ወይም ልማዳዊ በሆኑ የመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የተሳሳተ መረጃ ማስተላለፍን ያመለክታል። አንባቢውን ለማታለል እና  ለማደናገር ሲባል ሆን ተብሎ ወይም በተዛባ መረጃ ላይ የተመሠረተ የሐሰት መረጃ ጋር የተያያዘ ነው። የውሸት ዜናዎችን ማሰራጨት የተወሰኑ ግቦችን ለማሳካት፣ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ለመጫን እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማስከበር ሊያግዝ ይችላል ይሆናል።

የውሸት ዜና ውጤታማ የሚሆኑበት  ዋነኛው ምክንያት እውነተኛ ዜናን በመኮረጅ አሳማኝ በሆኖ መልኩ ለመቅረብ በመቻሉ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ይህ የተሳሳተ ግን ሊታመን የሚችል ዜና "ማራኪ" በሆነ መልኩ የሚቀርብ በመሆኑ ነው፣ ይህም ለትክክለኛነቱ የተለያዩ ማኅበራዊ ሐሳቦችን በማንሳት እና የተለመዱ ማህበራዊ ቅድመ-ውሳኔዎችን በማቅረብ፣  እንደ ጭንቀት፣ ንቀት፣ ቁጣ እና ብስጭት የመሳሰሉ ስሜቶች ፈጥኖ በመፍጠር ሰዎች ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡት ያደርጋል።

እንደነዚህ ያሉ የሐሰት ዜናዎችን የማሰራጨት ችሎታ ብዙውን ጊዜ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች አጠቃቀም እና በአጠቃላይ በሚሰሩበት መንገድ ላይ ይመሰረታል። እነዚህ በውሸት ላይ የተመረኮዙ ዜናዎች በፍጥነት በመሰራጨት የሚዛመቱ ሲሆን እንዲያውም የሚመለከተው አካል የሚሰጠው ማሰተባበያ ይህ የውሸት ዜና የሚያደርሰውን ጥፋት መቋቋም ያቅተዋል።

የውሸት ዜናን ማጋለጥ እና ማስወገድ አስቸጋሪ የሚሆንበት ምክንያት በጣም ብዙ ሰዎች በተለያየ ጽንሰ-ሐሳቦችን እና አስተያየቶችን በመስጠት በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች አማክይነት መስተጋብር በመፍጠራቸው የተነሳ ጉዳዩን አስቸጋሪ ያደርገዋል። የውሸት መረጃ በፍጥነት የሚንሰራፋበት ዋንኛው ምክንያት ተሰራጨው  ዘገባ ውሸት ይሁን ወይም እውነት የሚለውን ከሌላ ትክክለኛ ከሆነ መረጃ ጋር ለማመሳከር ካለመፈለግ የመነጨ ሲሆን በውስጡ አወንታዊ መድረክ ለመፍጠር ከሚያስችሉ ሌሎች የመረጃ ምንጮች ጋር ጤነኛ የሆነ ንጽጽር በሌለበት ሁኔታ የተሳሳተ መረጃ በሚገባ ውጤታማ ይሆናል። በተቃራኒው ግን ሰላማዊ ያልሆኑ እና መሠረተ ቢስ ሀሳቦችን በማስፋፋት ህዝቡን ወደ እኩይ ተግባርት ውስጥ በመክተት ግጭቶችን በሚገባ ሊፈጥር ይችላል። የተሳሳቱ መረጃዎች አሳዛኝ ጉዳዮችን ይፈጥራሉ፣ ሰውን ለማሳሳት እና ግጭትን ለመፍጠር ያስችላቸው ዘንድ ሌሎች ሰዎችን በጠላትነት በመፈረጅ ግጭትን ይፈጥራሉ።

የሐሰት ዜናዎች የጽንፈኝነት እና ተንጠልጣይ የሆነ ባህሪያት አላቸው። እብሪትን እና ጥላቻን ማስፋፋት ይወዳሉ። ይህ ውሸት የመጨረሻ ውጤት ነው።

2. የሐሰት ዜናዎችን እንዴት ለይተን ማወቅ እንችላለን?

ማንኛችንም ብንሆን እነዚህን ውሸቶች የመቃወም ግዴታ እንዳለብን ይሰማናል። የተጣራ እና እውነት የሆነ መረጃ ብዙውን ጊዜ ሆን ተብሎ በተሳሳተ ሁኔታ እና በተዘዋዋሪ በሚያሳዝን መልኩ በማታለል እና አንዳንድ ጊዜ የተራቀቁ የስነ-ልቦናዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ተመሰርቶ ሐሰት በሆነ መልኩ ሰለ ሚቀርብ ይህንን መለየት ቀላል የሆነ ስራ አይደለም።

ሰዎች በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ የሐሰት ዜናዎች ጋር ከመተባበር እና እነዚህን የሐሰት ዜናዎችን ከማሰታጨት ይልቅ፣ መረጃዎችን በሚገባ በመተንተን፣ መረጃዎች በግባቡ እንዲተረጉሙ እና እንዲገመግሙ፣ ውሸትን እንዲያስተባብሉ እና እንዲያጋልጡ በእዚህም ረገድ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስተማር የሚረዱ የትምህርት ፕሮግራሞችን ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህንን ክስተት ለመግታት ያስችል ዘንድ ችግሩን የሚመለከቱ ደንቦችን ለማቋቋም የሚረዱ ተቋማዊ እና ሕጋዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ፣ የቴክኖሎጂ እና የብዙኃን መገናኛ ተቋማት ኩባንያዎች መስፈርቶችን በማስቀመጥ በእጃቸው የሚገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዲጂታል የግለሰብ የግል መገለጫ መለያዎችን ተጠቅመው ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያግዙ ሥራዎችን እያከናወኑ ባለመሆናቸው በጣም ያስደንቃል።

ሆኖም ግን የተዛባ መረጃን መከላከል እና ለይቶ ማወቁ ጥልቅ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የማስተዋል ሂደት ይጠይቃል። “የእባብ ዘዴ” በመባል የሚታወቀውን ዘዴ በመጠቀም  በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ ላይ እርምጃን ለመውሰድ እና ለማጥቅት ዝግጁ የሆኑትን ሰዎች እኛ ለይተን ማወቅ እና ማጋለጥ ይኖርብናል። ይህ “የሰይጣን የማጭበርበር ችሎታ” በመጽሐፍ ቅዱሳችን በዘፍጥረት መጽሃፍ ውስጥ በሰው ልጆች ታሪክ አጀማመር ላይ የመጀመሪያውን የሐሰት ዜና ፈጠረ (ዘፍ 3 1-15)፣ በሰው ልጆች ኃጢአት አሳዛኝ ታሪክ የጀመረው፣ የሰው ልጅ የገዛ ወንድሙን መግደል በጀመረው (ዘፍጥረት 4)፣ በእግዚአብሔር፣ በጎረቤት፣ በማህበረሰቡ እና በፍጥረታትም ላይ ሳይቀር  በሚሰሩት ስፍር ቁጥር የሌሎች ክፉ ድርጊቶች ላይ የሰው ልጆች እንዲሰማሩ አደረገ። የዚህ የተዋጣለት "የውሸቶች ሁሉ አባት" የሆነ የእባቡ ዕቅድ (ዮሐ 8:44) ከእዚህ ጋር በጣም የሚመሰሳል ሲሆን በስውር የሚሰራ ተንኮል፣ በማባበል፣ ልብን በማሞቅ ወደ ውስጥ የሚገባ ውሸት እና ክርክር በጣም አደገኛ ነው።

በመጀመሪያው የኃጢያት ታሪክ ውስጥ ፈታኙ ወደ ሴቲቱዋ በመቅረብ “በእርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?”(ኦ. ዘፍጥረት 3፡1) በማለት ለእሷ ደኅንነት የተጨነቀ  እና ለእርሷ የሚያስብ ጓደኛ በመምሰል በከፊል ትክክለኛውን ነገር በመናገር በጀመረበት ወቅት፣ ሴቲቱም “ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ። (ኦ.ዘፍ.2፡17) የሚለውን የእግዚኣብሔር ቃል በማስታወስ የእባቡን ሐሳብ ታርማለች። ነገር ግን ሴቲቱ በየዋህነት መንፈስ  በእባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሎአል።” (ኦ.ዘፍ.3፡2) በማለት ትመልስለታለች። ይህ የሴቲቱ መልስ ሕጋዊ መሰረት የነበረው እና በአሉታዊ ቃላቶች የተሞላ ነው፣ የእባቡን መልስ ካዳመጠች በኋላ እና አታላዩ በፈጠረው እውነት በሚመስሉ መልሶች፣ በእዚህም በመሳብ ሰቲቱ ተታለለች። ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሴቲቱ የእባቡ ያቀረበውን መረጃ እውነተኛ መሆኑን /አለመሆኑን ማረጋገጫ በመሻት “ ይህንን ከበለን አንሞትም ወይ? ብላ ጥያቄ ታቀርባለች።

 “ፍሬውን በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር  እንደምት ሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” (ኦ.ዘፍ. 3፡5)ብሎ በመመለስ በእዚህም ተግባሩ ፈተኙ “አፍራሽ” ተግባሩን  እውነታን የተላበሰ በሚመስል መልኩ ያቀርባል። እግዚአብሔር የሰጣቸው የአባትነት ትዕዛዝ ለእነሱ በጎ በማሰብ የነበረ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን በጠላት የማታለል ተግባር የተነሳ  “ሴቲቱም የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ” (ኦ.ዘፍ. 3፡6) በእዚህም ምክንያት የእግዚኣብሔር ትዕዛዝ ዋጋ ቢስ ሆነ። ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ታሪክ አሁን ላነሳነው ሐሳብ መሰረታዊ የሆነ አስተንትኖ እንድናደርግ አስፈላጊ የሆነውን ነገር በማሳየት፣ የተዛባ መረጃ በጣም ጎጂ የሆነ ነገር እንደ ሆነ በማሳየት፣ በተቃራኒው ደግሞ የተዛባ ወይም ሐሰት የሆኑ መረጃዎችን ማመን የሚያስከትለውን አስከፊ የሆነ ውጤት እንድንረዳ ያደርገናል። ሌላው ቀርቶ ትንሽ የተዛባ እውነቱ በራሱ እንኳን አደገኛ የሆነ ውጤት ሊያስከትል ይችላል።

እዚህ አደጋ ላይ የሚጥለን ራስ ወዳድነታችን ወይም ደግሞ ስግብግብነታችን ነው። የሐሰት ዜናዎች ብዙውን ጊዜ በብዙዎቹ ይታያሉ፣ በፍጥነት በመሰራጨታቸውም የተነሳ እነርሱን ማስቆም በጣም ከባድ ነው፣ ይህም የሚሆንበት ምክንያት እነሱን ማሰራጨት በራሱ የማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮችን ያበረታታል በሚል ሕሳቤ ሳይሆን፣ ነገር ግን በሰው ልጆች ውስጥ በቀላሉ ሊሰርጽ በሚችለው የስግብግብነት መንፈስ ምክንያት ነው። የተንሰራፋው የኢኮኖሚያዊ የማጭበርበሪያ ተግባሮች እነዚህን የሐሰት መረጃዎችን በማሰራጭት ለስልጣን ያላቸውን ጥማት፣ ሐብትን ለማጋበስ እና ለመደሰት መሻትን ያመጣል፣ ይህም ይበልጥ አሳዛኝ የሆነ ነገርን በመፍጠር ተጠቂዎች እንድንሆን ያደርገናል፣ ከእዚህም በከፋ መልኩ ውስጣዊ ነፃነታችንን ሊያሳጡን ከሚችሉ ውሸቶች በባሰ ሁኔታ  ከአንዱ ውሸት ወደ ሌላ ውሸት በመሄድ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንድናማራ ያደርጋሉ፣ ይህም በጣም አሳዛኝ የሆነ ነገርን በመፍጠር ጭንቀት ውስጥ ይከታል። ሰዎች ክፉን ከደጉ በመለየት መልካም የሆኑ ውሳኔዎችን ማድርግ እንድችሉ፣ የኛን ጥልቅ ምኞቶች እና ዝንባሌዎች እንዴት ማስተካከል እንደ ሚገባ፣ ነገሮችን በሚግባ እንዲገመግሙ እና ፍላጎቶቻችንን እና ዝንባሌዎቻችንን በሚገባ እንዲረዱ፣ መልካም ለሆኑ ነገሮች ዓይናቸውን እንዲከፍቱ እና ማንኛውም ፈተና ማለፍ ይችሉ ዘንድ፣ ትምህርት እውነታን ለይቶ ለማወቅ አስፍላጊ ነው የምንለው በእዚሁ ምክንያት ነው።

3. “እውነት ነጻ ያወጣችኃል” (ዩሐንስ 8፡32)

በተንኮል አዘል ቋንቋ የሚደረጉ ባለማቋረጥ የሚነዙ ዘኔዎች  የኛን ውስጣዊ ህይወት በመበከል ሕይወታችንን ያጨልሙታል። ደስታዬውስኪ (እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1821-1881 ዓ.ም. የኖረ የራሻ ሀገር ተወላጅ የሆነ አጫጭር ታሪኮችን፣ ልብ ወለዶችን በመጻፍ የሚታወቅ ጸሐፊ የነበረ እና በ59 አመቱ ከእዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሰው ነበር) በዚህ ረገድ ደስታዬውስኪ የነበረው ግምገማ የሚይስደምም ነበር። እንዲህም ይል ነበር “ለራሳቸው የሚዋሹ እና የራሳቸውን ውሸቶች የሚያዳምጡ ሰዎች በእውነተኛው ዓለም ውስጥ ወይም በዙሪያቸው ያሉትን እውነቶች መለየት አይችሉም፣ በእዚህም የተነሳ ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ያላቸውን አክብሮት ለይተው ማወቅ በፍጹም አይችሉም። አክብሮት ከሌላቸው ደግሞ ማፍቀር ያቆማሉ፣ ፍቅር በማጣታቸው የተነሳ ደግሞ ይረበሻሉ፣ ከእዚህ የመረበሽ ስሜት ለወጣት ደግሞ የተለያዩ ዓለማዊ የሆኑ ፍላጎቶችን እና ጊዜያዊ የሆኑ ደስታዎችን ያድናሉ፣ በእዚህም  ምክንያት እንስሳዊ በሆነ መልኩ በክፉ ነገሮች ውስጥ ይዘፈቃሉ፣ ራሳቸውን እና ሌሎችን የመዋሸት ተግባራቸውን አጠናክረው ይቀጣላሉ(ደስታዬውስኪ የካራማዞቭ ወንድም ከሚለው አርእስት ከጻፈው መጽሐፍ ክፍል 2 ቁጥር 2 ላይ የተወሰደ)። 

ታዲያ እንዴት ራሳችንን መከላከል እንችላለን? የሐሰት ዜናዎች ከሚፍጥሩብን በሽታዎች ለመፈወስ የሚያግዘን ፍትሁን የሆነው መድኃኒት በእውነቱ መንጻት ነው። በክርስትና እምነት እውነት ማለት ጽንሰ-ሀሳባዊ በሆነ መልኩ ነገሮች እውነት ይሁኑ ወይም ደግሞ ሐሰት መሆናቸውን ወይም አለመሆናቸውን ለመለየት የሚረዳ ውሳኔ ማድርግ ብቻ ማለት አይደለም። እውነት ማለት ተደብቀው የቆዩ ነገሮችን “ማጋለጥ” ማለት ብቻ አይደለም። እውነት መላው ሕይወታችንን ይመለከታል። እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የድጋፍ፣ የሕብረት እና የመተማመን ምልክት በመሆን የኃይማኖት መግለጫው ምንጭ የሚል ስሜት አለው። እውነት ማለት እንዳንወድቅ የሚረዳን ምርኩዛችን ነው። በዚህ አንጻራዊ ግንኙነት ብቸኛው፣ አስተማማኝ እና እምነት የሚጣልበት እውነት አንድና አንድ ነው--በእርሱም ላይ እምነት መጣል እንችላለን እርሱ እግዚኣብሔር ብቻ ነው። ለእዚህም ነው ኢየሱስ “እኔ እውነት ነኝ” (ዩሐንስ 14፡6) ያለውም በእዚሁ ምክንያት ነው። እውነትን በተደጋጋሚ ማግኘት የምንችለው በራሳችን ሕይወት ውስጥ በታማኝነት ስንለማመደው እና በአንዱ በሚወደን ስንታመን ብቻ ነው። “እውነት ነጻ ያወጣችኃል” (ዩሐንስ 8፡32) እንደ ሚለው ነጻ ሊያወጣን የሚችለው ይህ ብቻ ነው።

ቅላቶቻችን እና ተግባሮቻችን እውነት፣ ትክክለኛ እና የታመኑ ከሆኑ ከሐሰት ነገሮች ነጻ መሆን እና መልካም ግንኙነት ለመፍጠር መሞከር የሚሉት እነዚህ ሁለት የሕይወት ንጥረ ነገሮችን እናገኛለን። እውነትን ለይተን ለማወቅ ሕብረት ለመፍጠር የሚያስችሉንን ማንኛቸውንም ነገሮች በቅድሚያ ማበረታታት እና መልካም ስነ-ምጋባራትን በማስተዋወቅ ሊከፋፍለን፣ ብቻችንን ሊያደርገን እና ሊቃወሙን የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ ለመዋጋት እንችላለን።  ሰለእዚህም እውነት ውጫዊ በሆኑ ጫናዎች የሚገኝ ነገር ሳይሆን ነገር ግን በሰዎች መካከል ከሚደረግ ነጻ ግንኙነት እና እርስ በርስ ከመደማመጥ ሊመጣ ይገባል።

እውነትንም መፈለጋችንን መቼም ቢሆን ልናቆም አንችልም፣ ነገር ግን እውነታዎችን ለመግለጽ ስንሞክር እንኳን ውሸት ሁልጊዜ ወደ ውስጥ ሊገባ ይችል ይሆናል። በእርግጥ እንከን የሌለበት ሙግት ሊካድ ወደ ማይችል እውነታዎች ውስጥ ሊጥል ይችላል፣ ነገር ግን ሌላውን ለመጉዳት እና ሌሎችን ለማዋረድ ጥቅም ላይ ቢውል ግን ትክክል ሆኖ ይታይ ይሆናል ነገር ግን እውነት አይደለም። የአንድን አረፈተ ነገር እውነታነት ከፍሬው መመልከት ይችላል፣ ጥልን የማይፍጥር ከሆነ፣ ልዩነትን የማያባብስ፣ ሰው ሥራ እንዲፈታ የማያበረታታ ከሆነ ወይም ደግሞ በሌላ በኩል ገንቢ የሆነ እና የዳበሩ አስተሳሰባቸውን ወደ ገንቢ ውይይትና መልካም ውጤቶችን የሚቀይሩ እና ውጤታማ የሆነ ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርጉ ከሆነ እነዚህን በመመልከት ብቻ የአንድ ዐረፍተ ነገር እውነተኛነትን ማረጋገጥ ይችላል።

4. ሰላም እውነተኛ ዜና ነው

የሐሰት ዘገባዎችን በተሻለ መልኩ ለመዋጋት የምይስችለን የመከላከያ ዘዴዎችና ስልቶች በመቀየስ ውጤታማ አያደርግም፣ ነገር ግን ሰዎችን መጠቀም ያስፈልጋል። እነዚህ ሰዎች ስግብግብ ያልሆኑ፣ ነገር ግን ለማዳመጥ ዝግጁ የሆኑ፣ እውነትን ከልብ ለማመንጨት ጥረት ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች፣ መልካም በሆኑ ነገሮች የሚማረኩ ሰዎች እና ለሚጠቀሙበት ቋንቋ ኃላፊነት መውሰድ የሚችሉ ሰዎች መሆን ይገባቸዋል።  የሐሰት ዜናን መስፋፋት ለማስቆም መልሱ ኃላፊነት መውሰድ ከሆነ፣ እንግዲያውስ ይህ ከባድ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ሰዎች መሆን የሚገባቸው መረጃን የሚሰጡትን ማለትም ጋዜጠኞችን፣ የዜና አውታሮችን የሚቆጣጠር ኃላፊ የሆኑ ሰዎች ትከሻ ላይ ነው ማለት ነው። በዛሬው ዓለም የእነርሱ ተግባር ሥራን መስራት ብቻ ሳይሆን ተልዕኮም ጭምር ነው። ዋናው ዓላማ  ዜናን በፍጥነት ለማስራጨት መጨናነቅ ሳይሆን መሆን ያለበት፣ ነገር ግን ማስታወስ የሚገባቸው ነገር የአንድ መረጃ ዋናው ቁምነገር መረጃን በፍጥነት ማድረስ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች መሆን ይኖርባቸዋል። መረጃን ተደራሽ ማድረግ ማለት ሰዎችን ማነጽ ማለት ነው፣ ከሰዎች ሕይወት ጋር መገናኘት ማለት ነው። ለእዚያም ነው እንግዲህ የመረጃ ምንጮችን በትክክል ማረጋገጥ እና ማነኛውንም የመገናኛ አውታር ከጥቃት መከላከል ማለት በጎ የሆኑ ነገሮችን ማስተዋወቅ ማለት ነው፣ መተማመንን መፍጠር ማለት ነው፣ የመገናኛ አውታሮችን ክፍት በማድረግ ለሰላም መጠቀም ማለት ነው ይምንለው።

ስለዚህ ሁሉም ሰው ልጆች የሰላም ጋዜጠኞች ይሆኑ ዘንድ ልጋብዛቸው እወዳለሁ። ነገር ግን ይህንን ስል ልክ እንደ ስኳር ጣፋጭ ለመሆን በመፈለግ ከባድ ችግሮች እየተፈጠሩ እያለ ለመቀበል አሻፈረኝ የሚል ዓይነት ጋዜጠኛ ወይም ደግሞ ለምንም ነገር ስሜት የማይሰጠው ጋዜጠኛ ማለቴ አይደለም። ነገር ግን በተቃራኒው እውነትን ያነገበ እና የሐሰት ዜናዎችን የሚቃወም፣ የንግግር ዘይቤዎች የማይጠቀሙ እና ስሜታዊ የሆኑ አርእስቶችን የማይጠቀሙትን ጋዜጠኞች መለቴ ነው። ጋዜጠኛ የተፈጠረው በሕዝቡ እና ለሕዝቡ አገልግሎት ነው፣ ለሁሉም አገልግሎት የሚሰጥ በተለይ ደግሞ በዓለም ውስጥ ድምጽ ለሌላቸው ብዙኃን ሕዝብ ድምጽ መሆን ይኖርባቸዋል። በሰበር ዜናዎች ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደርገ ጋዜጠኝነት ሳይሆን የግጭቶች መንስሄ ነቅሶ በማውጣት፣ ሰዎች መግባባት ይችሉ ዘንድ የበኩሉን ጥረት በማድረግ ለችግሮች መፍትሄ ይበጅ ዘንድ ቅን የሆኑ ሂደቶች እንዲጀመሩ የበኩሉን ድርሻ የሚጫወት ጋዜጠኛ ያስፈልጋል። ጋዜጠኝነት በጩኸት እና በቃላት ላይ የሚፈጸሙ የከረረ ግጭቶች አስወግዶ አማራጮችን ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል።

በመጨረሻም ወደ እውነተኛ መንገድ እንመለስ ዘንድ እና ለእውነት ለመቆም እንችል ዘንድ የቅዱስ ፍራንቸስኮን ጸሎት በጋራ እንድገም።

“ጌታ ሆይ የሰላም መሳሪያ አድርገኝ፣ ጥል ባለበት ፍቅር፣ መጠራጠር ባለበት እመንት፣ ተስፋ መቁረጥ ባለበት ተስፋ፣ ጨለማ ባለበት ብርሃን፣ ሐዘን ባለበት ደስታ፣ እንድዘራ አድርግኝ። አሜን!

ጥር 18/2010 ዓ.ም.

ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ

06 February 2018, 11:08