ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለእኛ ቅርብ እና ተስፋ ሰጪ የሆነው አምላክ እንዲያጽናናን እንፍቀድለት አሉ!

ዛሬ ሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ዛሬ ሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የቀይ መስቀል እና የግማሽ ጨረቃ የግብረ ሰናይ አገልግሎት የሚሰጡ ማሕበራትን ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው ማስታወሳቸው የተገለጸ ሲሆን በእነዚያ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩትን በጣም ጥሩ እና በጎ ተግባራት እግዚአብሔር እንዲባርክ የተማጸኑ ሲሆን ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት ጌታ ሁል ጊዜ በቅርበት፣ በእውነት እና ተስፋን በመስጠት እንደሚያፅናናን ቅዱስነታቸው አጽኖት ሰጥተው ተናግሯል።

የቫቲካን ዜና

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት ወቅት አራተኛው የፋሲካ ሳምንት ዐርብ ቀን ላይ ሲሆን በዕለቱ የፖንፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አመታዊ በዓል በመከበር ላይ እንደ ነበረ ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን በከፍተኛ ደረጃ በመውረር ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያበቃ ዘንድ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘፖንፔይ አማላጅነቷን መማጸናቸው ተገልጿል። ቅዱስነታቸው ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት በሥርዓተ አምልኮ መግቢያ ላይ በዛሬው ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመከበር ላይ የሚገኘውን የቀይ መስቀል እና የግማሽ ጨረቃ ቀን በጸሎት በማሰብ እና የሚከተለውን በመናገር ነበር. . .

ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቀይ መስቀል እና የግማሽ ጨረቃ ቀን እየተከበረ ይገኛል። በእነዚህ አስፈላጊ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩትን ሰዎች እግዚአብሔር ይህንን እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ተግባራቸውን እና እነርሱንም ጭምር እንዲባርክ እንፀልይላቸው።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ያደረጉ ስብከት በወቅቱ ከዮሐንስ ወንጌል ላይ ተወሰዶ በተነበበው ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ማበረታታቱን እና ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ እርሱ መሆኑ በሚገልጸው በሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር።

“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ። መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሐ 14 1-6) ።

“በኢየሱስ እና በደቀ መዛሙርቱ መካከል የተደረገው ይህ ንግግር በመጨረሻው እራት ወቅት “ኢየሱስ እና ሁሉም አዝነው በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል በማለት በተናገረበት ወቅት የተደረገ ንግግር እንደ ነበረ” በማስታወስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ነገር ግን በተመሳሳይ ጊዜ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ማፅናናት እንደ ጀመረ ጨምረው ገልጸዋል።  “ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ያጽናናቸዋል እናም የኢየሱስን የማፅናናት መንገድ እንዴት እንደ ሆነ እንመልከት። ጌታ እኛን እንዴት ነው የሚያጽናናን? ይህንን ማወቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እኛም በሕይወታችን ውስጥ የሀዘን ጊዜዎችን ማለፍ ስለሚኖርብን ነው።እውነተኛ የጌታ መጽናናት ምን እንደ ሆነ ለመገንዘብ እርሱ እንዴት እንደ ሚያጽናና መማር ይኖርብናል” በማለት ቅዱስነታቸው አክለው ገልጿል።

"በዚህ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ውስጥ ጌታ ሁል ጊዜ በእውነት፣ በተስፋ እና በቅርበት እንደሚያፅናና እናያለን፣ እነዚህ የጌታ ማጽናኛ ሦስቱ ባህሪዎች ናቸው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጌታ ከእኛ የራቀ አይደለም ለእኛ ቅርብ ነው ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ ”በማለት ውብ በሆነ መልኩ ኢየሱስ መናገሩን ጨምረው ገልጸዋል።   

ሁለተኛው የኢየሱስ “የማጽናኛ መንገድ እውነት” ነው ኢየሱስ ራሱ እውነተኛ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እኛም እውነተኛ እንድንሆን ኢየሱስ እንደሚያስተምረን ገልጸው በእውነት መንገድ ላይ መጓዝ ይኖርብናል ብለዋል።

“ሦስተኛው የኢየሱስ ማጽናኛ ባሕርይ ተስፋ ነው ፡፡ አዎን ፣ መጥፎ በሆነ ጊዜ ውስጥ ብትገቡ እንኳን ልባችሁ አይሸበር፣ አትደንግጡ፣ በእኔ እመኑ፣ ምክንያቱም በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪ አለ። እኔ ቦታ እዘጋጃለሁ” ብሎ ኢየሱስ መናገሩን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው እርሱ ሊወስደን ወደሚፈልግበት የዚያን ቤት በሮች በመጀመሪያ ይከፍታል  “እንደገና እመጣለሁ፣ ከእኔን ጋር እወስዳችኋለሁ ይለናል ብለዋል።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ “ብዙ ጊዜ፣ ​​በመጥፎ የሆኑ ጊዜያት ሲገጥሙን ፣ በጌታ ላይ እንቆጣለን እንጂ በዚያን ወቅት እንዲቀርበን፣ በገርነት ፣ በዚህ እውነት እና በዚህ ተስፋ አማካኝነት ለእኛ እንዲናገር አንፈቅድለትም” ማለታቸው የተገለጸ ሲሆን ጌታ እንዴት እንደ ሚያጽናናን ለማወቅ እንችል ዘንድ እርሱ እድያስተምረን ጸጋውን እንጠይቅ ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

08 May 2020, 12:53
ሁሉንም ያንብቡ >