ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ግትርነት ባለበት ስፍራ የእግዚአብሔር መንፈስ የለም አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግንቦት 07/2012 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የቤተሰብ ቀን እንዲከበር ማወጁን አስታውሰው በዚህም መሰረት በዕለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለቤተሰብ ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል። በዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቅዱስነታቸው ባደረጉት ስብከት በኢየሱስ ማመን ደስታ እና ነፃነት እንደሚያመጣ ገልጸው ግትርነት ግን ብጥብጥ ያስከትላል፣  ግትርነት ባለበት ስፍራ የእግዚአብሔር መንፈስ የለም ብሏል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በአሁኑ ወቅት የምንገኘው በአምስተኛው የፋሲካ ሳምንት ዛሬ ግንቦት 07/2012 ዓ.ም አርብ ቀን ለዕለቱ በተዘጋጀው ሥርዓተ አምልኮ ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር፤ ቅዱስነታቸው በመስዋዕተ ቅዳሴው መግቢያ ላይ ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ በቤተሰብ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን የሚከተለውን ተናግሯል ፡፡

ዛሬ የአለም የቤተሰብ ቀን ነው -የጌታ መንፈስ በቤተሰቦች ውስጥ የፍቅር ፣ የመከባበር እና የነፃነት መንፈስ እንዲያድግ እንዲረዳቸው ለቤተሰቦች እንጸልይ ፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ያደረጉት ስብከት መሰረቱን አድርጎ የነበረው “ጳውሎስና በርንባስ  አረማዊያን በእግዚአብሔር ያምኑ ዘንድ ላማድረግ ወደ አንጾኪያ ተላኩ፣ አንዳንድ ሰዎች ያለ ፈቃድ ወጥተው በንግግራቸው ልባችሁን እንዳወኩና እንዳናወጧችሁ ሰምተናል በማለት ተናገሩ። ስለዚህ ጥቂት ሰዎች መርጠን ከተወዳጆቹ ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር ወደ እናንተ ለመላክ ሁላችንም ተስማምተናል፤ ለጣዖት ከተሠዋ ነገር፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋ እንዲሁም ከዝሙት ርኵሰት እንድትርቁ ነው። ከእነዚህ ዐይነት ነገሮች ብትርቁ ለእናንተ መልካም ነው። የክርስትና እመነት የተቀበሉ አንዳንድ ፈሪሳውያን እንዳሉት በሙሴ ሕግ መሠረት የመገረዝ ግዴታ እንደሌለባቸው ሐዋርያት አዲሶቹን ደቀመዛሙርቶች የሚያበረታታ እና የሚያስደስት ደብዳቤ ይዘው መሄዳቸውን” በሚገልጸው (ሐዋ 15፡ 22 31) ላይ በተጠቀሰው የዕለቱ የመጀመሪያ ምንባብ ላይ መሰረቱን ያደረገ ስብከት ነበር።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ “በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እንደ ተጠቀሰው በመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ቤተክርስቲያ ውስጥ ሰላም እንደ ነበረ እንመለከታለን፤ ነገር ግን የስደት እና የሁከት ጊዜም ነበር” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የዛሬው የመጀመሪያ ንባብ የሚያስረዳን የረብሻ ጊዜ እንደ ነበረ ያሳያል ብለው ከአረማዊነት ወደ ክርስቲያንነት የተለወጡ ክርስቲያኖች “በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ተጠምቀው ደስተኛ ነበሩ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ፡፡ ከአረማዊነት ወደ ክርስቲያንነት ያለአንዳች ከልካይነት ተሸጋገሩ” ብለዋል።

ነገር ግን “የአይሁዳዊ መንፈስ የተጠናወታቸው ክርስቲያኖችም ነበሩ፣ አረማዊያን ወደ ክርስትና እመንት በቀጥታ መሻገር የለባቸውም በማለት ይህ ሊከናወን እንደማይችል የሚናገሩ ነበሩ ። አንድ ሰው አረማዊ ከሆነ በመጀመሪያ እሱ አይሁዳዊ፣ ጥሩ አይሁዳዊ መሆን ይኖርበታል፣ከዚያም በኋላ ነው ክርስቲያን መሆን የሚችሉት በማለት ይናገሩ ነበር። ከአረማዊ ወደ ክርስትና እምነት የተለወጡ ክርስቲያኖች ይህንን አልተረዱም- ‘ለምንድነው እሱ ሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች የምንሆነው? ከአረማውያን እምነት በቀጥታ ወደ ክርስትና መሄድ አንችልም ወይ?’ በማለት ጥያቄ ያነሱ ነበር።  እነሱ የክርስቶስ ትንሣኤ የጥንቱን ህግ ወደ ታላቅ ሙላት ያመጣ ይሆን ወይ ብለው ይገረሙ ነበር ፡፡ እነሱ ተጨንቀው እና በመካከላቸው ብዙ ውይይቶች ነበሩ” ብለዋል።

“ይሁዲዎች” ሐሳባቸውን ለማጠናከር በማሰብ “ሐዋርያዊ ተልዕኮን ሰበብ በማደረግ እና ሥነ-መለኮታዊ ክርክሮችን በማንሳት፣ በተወሰኑ ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮች እንኳን ሳይቀር” ጽሁፎቻቸውን ይደግፉ ነበር፣ እናም ይህ የመንፈስ ቅዱስን በነጻነት መንቀሳቀስ፣ በክርስቶስ ትንሳኤ እና ፀጋ ላይ ጭምር ጥያቄ ያነሳ  ጉዳይ እንደ ነበር” ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

“እነሱ ስልታዊ እና ግትር እንደ ነበሩ” በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው  ኢየሱስ እነዚህን የሕግ መምህራን ሕዝቡ በሕግጋት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ እንዲኖር ይመክሩ ስለነበረ እነሱን አስቀድሞ ገሥጿቸው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ቀኖናዊ ከመሆን ይልቅ “ርዕዮተ ዓለማዊ የነበሩት እነዚህ ሰዎች” ሕጉን እና ቀኖናውን ወደ ርዕዮተ ዓለም በመቀየር ዝቅ ሲያደርጉት ይታያሉ፣ ሐያማኖትን ወደ ሕግጋት ደረጃ በማውረድ ደረጃውን እንዲቀንስ አድርገዋል፣ እናም በእዚህ ተግባራቸው የመንፈስ ቅዱስን እንቅስቃሴ ገድበውታል ብለዋል። ተከታዮቻቸው የወንጌልን ደስታ የማያውቁ “ግትር ሰዎች” ነበሩ በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስን ለመከተል የሚያስችለው ፍጹም የሆነው መንገድ ግትርነት ነው ብለው ያምኑ ነበር፣ እነዚህ የሕግ መምህራን የተከታዮቻቸውን ሕሊና ተጭነው ነበር፣ ተከታዮቻቸውም ግትር እንዲሆኑ ያስገድዷቸው ነበር ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህንን በድጋሜ ሲናገሩ “ግትርነት ጥሩ መንፈስ አይደለም ፣ ምክንያቱም የመበዤት ነፃነትን እና በነጻ የተሰጠንን የክርስቶስን ትንሳኤን ስለሚገድብ ነው። ይህ ደግሞ በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ሁሉ ውስጥ ተደጋግሞ የሚከሰት ነገር ነው። በእኛ ጊዜ ውስጥ እንኳን በጥሩ ሁኔታ የተደራጁ የሚመስሉ የተወሰኑ ሐዋርያዊ ማዕከላት አይተናል ፣ በደንብ የሚሰሩ የሚመስሉ ነገር ግን ሁሉም ግትር ናቸው በአሰራራቸው ውስጥ እንኳን ስለነበረው ሙስና አውቀናል” ብለዋል።

“ግትርነት ባለበት ስፍራ ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በእዚያ አይኖርም፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ነፃ ነውና” እናም እነዚህ ሰዎች “የእግዚአብሔር መንፈስ ነጻነት እና የመበዤት ነጻነትን” ገድበዋል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ጽድቅ፣  የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ሁሉ በነፃ የተሰጡን ጉዳዮች ናቸው አይከፈልባቸውም፣ አንገዛቸውም፣ በነጻ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ብለዋል።

“ሐዋርያት በዚህ ሸንጎ ተሰብስበው በመጨረሻው ላይ እንዲህ የሚጀምር ደብዳቤ ጻፉ ‘እኛ በእናንተ ላይ ሌላ ግዴታ እንዳንጥል በእርግጥ መንፈስ ቅዱስ ተገልጦ ነግሮናል’” የሚል መልዕክት መላካቸውን ቅዱስነታቸው ያስታወሱ ሲሆን ሥነ-ምግባርን የተመለከቱ አንዳንድ ግዴታዎችን በማስቀመጥ ክርስትና በአረማውያን እምነት እንዳይደናቀፍ ማድረጋቸውን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

በመጨረሻም  ከአረማዊነት ወደ ክርስቲያንነት የተለውጡት  እነዚህ የተቸገሩ ክርስቲያኖች ተሰብስበው የተላከላቸውን ደብዳቤ ተቀብለው “የምእመናኑን ጉባኤ በአንድነት ሰብስበው ደብዳቤውን ሕዝቡም ካነበቡት በኋላ አበረታታች በሆነው ቃሉ ደስ ተሰኙ” በማለት በስብከታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው ስሜታቸው ከረብሻ ወደ ደስታ እንደ ተሸጋገረ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። የግትርነት መንፈስ ሁል ጊዜ ያስቆጣል: - በምትኩ  የወንጌላዊ የሆነ ነፃ መንፈስ መንፈስን ወደ ደስታ ይመራል ፣ ምክንያቱም ኢየሱስ በትንሳኤው ያደረገው ይህንኑ ነው ደስታን ለሁላችን አምጥቷል፣ ኪየሱስ ጋር ያለን ግንኙነት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ይህንን ስጠኝ፣ እኔ ያንን እሰጥኋለሁ የሚል የአንድ ነጋዴ እና የሻጭ ግንኙነት ዓይነት እንዳልሆነ ገልጸው ወንጌላዊ ያልሆኑትን ፍሬዎችን ለይተን እንድናውቅ እና የግትርነትን መንፈስ እንድናስወግድ ከማንኛውም የስጋት ጭንቀት ነፃ እንድንሆን ጌታን ጸጋውን እንዲሰጠን እንለምን ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

15 May 2020, 10:02
ሁሉንም ያንብቡ >