ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ ግንቦት 03/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ የጸሎት ሀሳባቸውን ያደረጉት በእዚህ አሁን በመላው ዓለም በስፋት በሚታየው ከባድ የሆነ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስራቸውን ላጡ ሰዎች ጸሎት በማደረግ ሲሆን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ልኮልን በሕይወት ጉዟችን አብሮን እንዲጓዝ እና እንዲንከባከብን እንዳደረገ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያደረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የፋሲካ አምስተኛው ሳምን ሰኞ ዕለት ለዕለቱ በተዘጋጀው ሥርዓተ አምልኮ ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን በስርዓተ አምልኮ መግቢያው ላይ ቅዱስነታቸው በእዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ሥራቸውን ላጡ ሰዎች የሚከተለውን ጸሎት በማደረግ ነበር።

“በእነዚህ ቀናት ብዙ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የገለጹ ሲሆን  ብዙዎች እንደገና አልተቀጠሩም ብለዋል። “በስራ እጥረት የተነሳ እየተሰቃዩ ላሉት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንጸልያለን” ብለዋል ፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ያደረጉት ስብከት በዕለቱ ከዮሐንስ ወንጌል ላይ ተወስዶ በተነበበው “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። “አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤ አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ 14፡21-26)  በሚለው የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር። በእዚህ የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ባደርገው ስብከታቸው ቅዱንሰታቸው እንደ ገለጹት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መቼም ቢሆን ብቻቸውን እንደማይተዋቸው በመጨረሻው እራት ላይ ገልጾላቸው እንደ ነበረ ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

መንፈስ ቅዱስ በጭራሽ አይተወንም

መንፈስ ቅዱስ “ጴርቅሊጦስ ወይም ጠበቃ ይባላል - ምክንያቱም እሱ ስለሚደግፈን፣  እንዳንወድቅ አብሮን በመጓዝ ስለሚደግፈን” እናም ጌታ ይህንን ድጋፍ እንደ ሚሰጠን ቃል ገብቶልናል ብለዋል።

“መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ምን ያደርጋል?” ሲሉ ቅዱስነታቸው ጥያቄ አንስተዋል። “መንፈስ ቅዱስ ወደ እምነት ምስጢር እንድንገባ ያስተምረናል፣ ምስጢር የሆነውን የኢየሱስን አስተምህሮ እንድንረዳ እና ስህተት ሳንፈጽም እምነታችንን እንድንገነዘብ ይረዳናል” ብለዋል ፡፡

መንፈስ ቅዱስ እንድናድግ ፣ እንድናስተውል፣ እንድናስታውስ ያስተምረናል

ስለ ምስጢሩ ያለን ግንዛቤ ለመረዳት “ዛፎች በሚያድጉበት ሁኔታ ማደግ ይኖርብናል፣ ዛፎች ሲያድጉ ማንነታቸውን አይቀይሩም ነገር ግን ሁሌም እያደጉ፣ እየሰፉ፣ የረዘሙ እና ብዙ ፍሬ እያፈሩ ይሄዳሉ፣ ነገር ግን በተመሳሳይ መልኩ ሁልጊዜ ያው ናቸው ማንነታቸውን አይቀይሩም” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ “የእምነት አስተምህሮው የማይንቀሳቀስ ነገር አይደልም፣ ነገር ግን ያድጋል ፣ አስተምህሮ እንዳይቀለበስ የሚያግደው መንፈስ ቅዱስ ነው ፣ እናም ኢየሱስ ያስተማረንን ትምህርቶች በውስጣችን እንዲያድግ የሚያደርገው ይሄው መንፈስ ቅዱስ ነው” ብለዋል።

መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ የተናገረውን ነገሮች በሙሉ እንድናስታውስ ያደርገናል “እሱ ልክ እንደ ትውስታ ነው፣ እሱ ይነቃናል፣ የጌታ የሆኑትን ነገሮች ብቻ እንድናከናውን ያነሳሳናል፣ የራሳችንን ህይወት እንድናስታውስ ይረዳናል ” ብለዋል።

እናም ይህንን ጭብጥ የበለጠ ለማዳበር በማሰብ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ “እንዴት እንደ ተበዤን ማስታወሳችን፣ የሕይወት ጉዞ ትውስታን ያመጣል” ብለዋል። መንፈስ ቅዱስ አሁን ምን ማድረግ እንዳለብን፣ ትክክለኛውን መንገድ ከተሳሳተው ለይተን እንድናውቅ እና እንድንገነዘብ ይረዳናል ፣ መመሪያ ይሰጠናል ብለዋል።

መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው

“መንፈስ ቅዱስ አስታዋሽ ሁነን በዚህ መንገድ ላይ እንድንራመድ ይመራናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው “ትልቅ እና ትንሽ የዕለት ተዕለት ውሳኔዎችን እንድንወስን ይረዳናል። እሱ ሁሉንም ነገር ያስተምረናል ፣ ምስጢራዊ የሆኑ ነገሮችን ያስተዋውቀናል ፣ እንድናስታውስ ፣ እንድንረዳ እና እንድናድግም ያደርገናል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት መንፈስ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ስጦታ” መሆኑን የገለጹ ሲሆን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እንደ ተጠቀሰው “ብቻችሁን አልተዋችሁም፣ መቼም ቢሆን እናንተን ፈጽሞ የማይተው እና ሊረዳችሁ የሚችለውን፣ እንድታስተውሉ እና እንድታድጉ የሚያደርጋችሁን አጽናኙን ጴራቂሊጦስ እልክላችኋለሁ” ብሎ መናገሩን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። “በጥምቀታችን ወቅት የተቀበልነውን ይህንን ስጦታ ጠብቀን ማቆየት እንችል ዘንድ ጌታ እንዲረዳን ከጸለዩ” በኋላ ቅዱስነታቸው ለዕለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህንን ዝግጅት ከእዚህ በታች ያለውን ተጫወት የሚለውን ምልክት በመጫን ማዳመጥ ትችላላችሁ!
11 May 2020, 11:14
ሁሉንም ያንብቡ >