ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቤተሰብ ውስጥ ሰላም፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ደግሞ አንድነት እንዲኖር ጸለዩ!

በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ዛሬ ሚያዝያ 26/2012 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ላይ ቅዱስነታቸው በአሁኑ ወቅት መላውን ዓለም በማሽበር ላይ በሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት መውጣት ያልቻሉ ቤተሰቦችን በማሰብ ጸሎት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን በእዚህ ወቅት በቤተሰብ መካከል አመጽ እና ግጭት ተወግዶ በአንጻሩ ሰላም፣ ፍቅር  እና ትዕግስት ይሰፍን ዘንድ ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል። በዕለቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቅዱስነታቸው ባሰሙት ስብከት በትህትና እና በመከባበር ላይ የተመሰረት አንድነት በቤተክርስቲያን ውስጥ ይኖር ዘንድ ኢየሱስ እንደ ሚፈልግ የገለጹ ሲሆን የመከፋፈል ፈተናዎችን ማሸነፍ አለብን ብለዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት ለቤተሰብ ጸሎት በማድረግ እና እንዲህ በማለት ነበር . . .

ዛሬ ለሁሉም ቤተሰብ እንጸልይ: - ተገልለን በቤታችን ውስጥ ተዘግተን እንድንቀመጥ በተገደድንበት በአሁኑ ወቅት ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለማድረግ ፣ ከልጆቻችሁ ጋር ብዙ አዳዲስ የፈጠራ ችሎታዎቻችሁን በማዳበር ወደ ፊት ለመጓዝ ሞክሩ። እንዲሁም ሌላ አሳሳቢ ነገር አለ፣ አንዳንድ ጊዜ የቤት ውስጥ ብጥብጥ ሊከሰት ይችላል። በእዚህ ተገልለን በቤታችን ውስጥ ተዘግተን እንድንኖር በተገደድንበት በአሁኑ ወቅት ቤተሰብ በትዕግስት እና በሰላም ይኖር ዘንድ ለቤተሰብ እንጸልይ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያደረጉት ስብከት ትኩረቱን አድርጎ የነበረው በእለቱ በቀዳሚነት ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ (ሐዋ. 11፡1-18) ላይ ተወስዶ በተነበበው የእግዚአብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በሙሴ ሕግ ባለተፈቀደ መልኩ “ወዳልተገረዙ ሰዎች ቤት ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ” በማለት “ከተገረዙት ወገን የነበሩ አማኞች”ሐዋርያው  ጴጥሮስን በነቀፉት ወቅት እርሱ በሰጠው በሚከተለው ምላሽ ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር . . .

“ጴጥሮስ ግን እንዲህ ሲል ነገሩን በቅደም ተከተል ያስረዳቸው ጀመር፤ “በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ በተመስጦ ውስጥ እያለሁ ራእይ አየሁ፤ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር፣ በአራት ማእዘን ተይዞ ከሰማይ እኔ ወደ ነበርሁበት ቦታ ሲወርድ አየሁ። አተኵሬም ይህን ነገር ስመለከት አራት እግር ያላቸው እንስሳት፣ የዱር አራዊት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በሰማይ የሚበሩ አዕዋፍ አየሁ። በዚህ ጊዜ፣ ‘ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣና ዐርደህ ብላ’ የሚለኝን ድምፅ ሰማሁ። “እኔም፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ርኩስ ወይም ያልተቀደሰ ነገር ፈጽሞ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልሁ። “ያም ድምፅ ዳግመኛ፣ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኩስ አትቍጠረው’ ሲል ከሰማይ ተናገረኝ። ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ከዚያ ሁሉም እንደ ገና ወደ ሰማይ ተወሰደ” (የሐዋርያት ሥራ 11፡ 4 10)።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከእዚህ በላይ በተጠቀሰው የእግዚአብሔር ቃል ተመርኩዘው እንደ ገለጹት ሐዋርያው ጴጥሮስ  ይህንን ተግባር የፈጸመው መንፈስ ቅዱስ ስለመራው ነው ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ “በተመሳሳይ መልኩ በቤተክርስቲያን ውስጥ  እራስን ጻድቅ አድርጎ መቁጠር እና ሌሎችን ደግሞ ኃጢያተኞች እንደ ሆኑ አድርጎ የመፈረጅ እና የመከፋፈል አባዜ እንዳለ” ቅዱስነታቸው ገልጸው በእዚህ ምክንያት እንደ እርኩስ የተቆጠሩ ሰዎች መኖራቸው እንደ ሚያሳስባቸው ጨምረው ገልጸዋል። “ይህ ከርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ ወይም ደግሞ ከሐይማኖት ተቋማት የሚመነጭ የቤተክርስቲያን በሽታ ነው” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው  በእዚህ መልክ ህጉን መተርጎም ደግሞ ዓለማዊ የሆነ አስተሳሰብ ነው ብለዋል። የእዚህ ዓይነት አስተሳሰቦች ደግሞ አንድነትን እና ሕብረትን ከመፍጠር ይልቅ መከፋፈል እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሐስተሳሰቦች እንደ ሆኑ በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው መከፋፈል ከአንድነት የተሻለ ነገር ነው በማለት የሚነዙ አሉታዊ አስተሳሰቦች ናቸው፣ የእኔ ሀሳብ እኛን ከሚመራን ከመንፈስ ቅዱስ የበለጠ አስፈላጊ ነው በማለት የሚታበዮ ሰዎች አስተሳሰብ ነው፣ ጌታ የሚፈልገው ግን አንድነትን ነው ብለዋል።

በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ” (ማቴ 10፡14-16) በማለት ኢየሱስ መናገሩን ያስታወሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ኢየሱስ  ትልቅ እና ትንሽ ፣ ሀብታም እና ድሃ ፣ ጥሩ እና መጥፎ ሳይለይ፣ ለሁሉም የመጣ የሁሉም መልካም እረኛ ነው ብለዋል። በእርሱ ለማያምኑ ወይም ከሌላ የሃይማኖት ተቋማት ለመጡ ሰዎች እንኳን ሳይቀር እርሱ ለሁሉም ነው የመጣው፣ ለሁሉም ነው የሞተው፣ እኛ አንድ ቤዛ ብቻ አለን፣ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ብለዋል። ነገር ግን እኔ ከእዚህ ወገን ነኝ፣ እርሱ ደግሞ ከእዚያ ወገን ነው የሚል ፈተና እንደ ሚገጥመን የገለጹት ቅዱስነታቸው ልዩነቶቹ ህጋዊ የሆነ መሰረት አላቸው፣ ነገር ግን ልዩነቶች በቤተክርስቲያ አንድነት ጥላ ሥር ሊታዩ የገባቸዋል ብለዋል። ሁላችንም አንድ እረኛ አለን፣ እርሱም ጌታ ኢየሱስ ነው በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጌታ ከመከፋፈል  ስነ-ልቦና ነፃ እንዲያወጣን እና ሁላችንም በእርሱ ውስጥ ወንድማማቾች መሆናችንን እንድንገነዘብ ይርዳን ብለው ከጸለዩ በኋላ ቅዱስነታቸው የዕለቱን ስብከት አጠናቀዋል።

ይህን ዝግጅት ለማዳመጥ ከእዚህ ቀጥሎ ያለውን "ተጫወት" የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
04 May 2020, 11:17
ሁሉንም ያንብቡ >