ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ከወረርሽኙ ነጻ ለመውጣት በወንድማማችነት መንፈስ አብረን እንጸልይ አሉ!

ዛሬ ግንቦት 06/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መስዋዕተ ቅዳሴ ማሳረጋቸው ተገልጿል። በጥር 26/2011 ዓ.ም  “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በአቡ ዳቢ ተካሂዶ በነበረው የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ስብስባ ላይ “በእግዚአብሔር ላይ እያንዳንዳችን ያለን እምነት ኅበረት እንዲኖረን ያደርጋል እንጂ አይከፋፍለንም” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ቅዱስነታቸው በተገኙበት አንድ ስብሰባ ተካሂዶ እንደ ነበረ መዘገባችን ይታወሳል። በዚህም መሰረት ይህንን “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በዓለም ዙሪያ ለማስፋፋት እና ሁሉም የሐይማኖት ተቋማት የሰላም እና የወንድማማችነት መንፈስ በዓለም ዙሪያ እንዲመጣ በጋራ ለመሥራት ተስማምተው አንድ የጋራ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ይታወሳል። የእዚህ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” ማሕበር የበላይ ኃላፊዎች ዛሬ ግንቦት 06/2012 ዓ.ም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከዓለማችን ይወገድ ዘንድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ የሐማኖት ተቋማት አባላት የሆኑ ምዕመናን ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

የቫቲካን ዜና

ይህ “ሰብዓዊ ወንድማማችነት” የተሰኘው ማሕበር የኮሮና ወረርሽኝ ከአለማችን እንዲወገድ ዛሬ ግንቦት 06/2012 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጸሎት እንዲደረግ ባቀረበው ጥሪ መሰረት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ በእዚህ ጥሪ ላይ የተመረኮዘ ሲሆን በዚህም መሰረት  ይህ የኮሮና ቫይረስ ከዓለማችን ይወገድ ዘንድ ከወረርሽኙ ነጻ ለመውጣት እንደ ወንድማማቾች አብረን በጋራ እንጸልይ በሚለው የጸሎት ሐሳብ ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ እንደ ነበረ ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባደረጉት ስብከት ላይ እንደ ረሀብ እና ጦርነቱ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ የሚገኙ እና ሞት የሚያስከትሉ ሌሎች ወረርሽኞች መኖራቸውን በማስታወስ፣ ሰዎች እግዚአብሔር እንዲባርከን እና እንዲረዳን እንዲለምኑ ጥሪ አቅርቧል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በዕለቱ ያሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በአሁኑ ወቅት የምንገኘው በአምስተኛው የፋሲካ ሳምንት ዛሬ ግንቦት 06/2012 ዓ.ም ሐሙስ ዕለት ላይ በተከበረው በዩሁዳ ቦታ የተመረጠው እና ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ በድፍረት በመሰከረው የሐዋርያው ቅዱስ ማቲያስ (የሐዋ 1፡1-26) ዓመታዊ በዓል ተክብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ለዚሁ ዓመታዊ በዓል ለዕለቱ በተዘጋጀው የሥርዓተ አምልኮ ላይ መሰረቱን ያደረገ መስዋዕተ ቅዳሴ አሳርገዋል።  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ በመግቢያው ላይ የሰብአዊ ወንድማማችነት ማሕበር ከፍተኛ ኮሚቴ ለዛሬ ግንቦት 06/2012 ዓ.ም የጸሎት፣ የጾም እና የበጎ አድራጎት ሥራዎች መፈጸሚያ ቀን እንዲሆን መወሰኑን በማስታወስ ሁሉም ሰው እንደ ወንድማማች አንድ በመሆን እግዚአብሔር ከዚህ ወረርሽኝ ነፃ እንዲያወጣን እንዲጠይቁ ሕዝቡን አበረታቷል። ቅዱስነታቸው ይህንን በተመለከተ ሲናገሩም የሚከተለውን ብለዋል . . .

ይህ አደገኛ ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ አሳዛኝ ወቅት የእግዚአብሄርን ምህረትን እና ርኅራኄ ለመጠየቅ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ማሕበር ከፍተኛ ኮሚቴ ዛሬ የጸሎት ቀን እንዲሆን ጥሪ አቀረበ።  ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። የአዚዚው ቅዱስ ፍራንቸስኮስ “ሁሉም ወንድማማቾች” ናቸው ብሎ ተናግሮ ነበር። ለዚህ ደግሞ የተለያየ የሐይማኖት ተቋማት ተከታዮች እና የተለያየ እምነት የሚከተሉ ሰዎች ሁሉ ዛሬ ከዚህ ወረርሽኝ የመፈወስን ጸጋ ይሰጠን ዘንድ ለመጠየቅ በጸሎትና በንስሐ በአንድ ልብ ሁነን ጸሎታችንን እናቀርባለን።

በትንቢተ ዮናስ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰውን እና የነነዌ ሕዝቦች በፈጸሙት ኃጢአት ምክንያት ከተማቸውን ከጥፋት እና ከመከራ ለመታደግ ማቅ ለብሰው ጾም ጸሎት ማድረጋቸውን በማስታወስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በእዚህ የሕዝቡ ተግባር ምክንያት የነነዌ ከተማ ተለወጠች፣ ከተማዋ ከጥፋት ወረርሽኝ ምናልባትም ከሥነ ምግባር እጦት ወረርሽኝ ተጠብቃለች ብለዋል። እናም ዛሬ አሉ - ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ - “እኛ የተለያየ እምነት የምንከተል ወንድሞች እና እህቶች ሁላችንም በዚህ የህመም ጊዜ ውስጥ አንድ በሚያደርገን የወንድማማችነት አንድነት በመፍጠር እና በመተባበር ይህ ወረርሽኝ እንዲወገድ እንጸልያለን” ብለዋል።

“እኛ ይህንን ወረርሽኝ አልጠበቅንም፣ እናም ብዙ ሰዎች ምንም ነገር ማድረግ ባለመቻላቸው ይሞታሉ፣ ብቻቸውን ይሞታሉ። ወደፊት ለሚከሰተው ኢኮኖሚያዊ ድቀት በማሰብ እንጨነቃለን። ሁላችንም ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ። አንዳንዶች ምናልባት ይህ ‘ሃይማኖታዊ ንፅፅር’ ነው ሊሉ ይችሉ ይሆናል። እንደዚያ ግን አይደለም። ሁሉም ሰው አቅሙ በፈቀደ መጠን ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ። እኛ እንደ ወንድማማቾች አንድ ነን ፣ በባህላችን እና በሃይማኖታችን መሠረት እየጸለይ። እግዚአብሔር ይህንን ወረርሽኝ ያስቆምልን ዘንድ ስለ ኃጢአታችን ከእግዚአብሔር ይቅርታን እንጠይቅ። ዛሬ የወንድማማችነት ቀን ነው። ይህ የመጸጸት እና የጸሎት ቀን ነው። ወረርሽኙ እንደ ጎርፍ ሆኖ መጥቷል። ነገር ግን ሌሎች ብዙ ወረርሽኞች አሉ፣ እኛ ግን አላስተዋልናቸውም፣ ልንመለከታቸውም አልፈለግንም። ለሌሎች አሳዛኝ ክስተቶች ግድየለሾች ነን። በዚህ ዓመት የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ውስጥ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በረሃብ ሞተዋል -የረሃብ ወረርሽኝ አለ። እኛም ሌሎች ወረርሽኞችን ማሰብ አለብን - የጦርት፣ ረሀብ እና ሌሎች ወረርሽኞችን እናስብ። ዛሬ እንደየራሳችን ባህል በጸሎት፣  ጾምና በልግስና መንፈስ አንድ ላይ መጸለያችን አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር የነነዌ ሕዝቦች ከገቡበት የኃጢያት ወረርሽኝ መውጣታቸውን ባየ ጊዜ ምሕረት አደረገላቸው። እግዚአብሔር ሁላችንንም እንዲባርከን እና ምህረት እንዲያደርግልን እንጸልይ።

14 May 2020, 09:09
ሁሉንም ያንብቡ >