ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮሮና ወረርሽኝ ያረፉትን ነፍሳት በጸሎት አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 27/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በኮሮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የሚረዳቸውን አጥተው በብቸኝነት ተሰቃይተው የሞቱትን በሙሉ አስታውሰው እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲሰጣቸው ለምነዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት ስብከት በኢየሱስ ክርስቶስ መንጋ መካከል እንዳንሆን የሚያደርጉ አንዳንድ እንቅፋቶች፥ ለሃብት መገዛት ፣ ግትርነት ፣ ቤተክህነታዊ ገናናነት እና ዓለማዊነት ናቸው ብለው ከእነዚህ ነጻ ካልወጣን በቀር ወደ ኢየሱስ መቅረብ አንችልም ብለዋል።    

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን 

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የብርሃነ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል በተከበረ በአራተኛ ሳምንት በዋለው በዛሬው ዕለት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሞቱትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በወረርሽኙ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል አስታማሚ ረዳት ያልነበራቸው፣ ብቻቸውን ተሰቃይተው የሞቱትን፣ ቀባሪ ቤተሰብ ወይም ዘመድ ያልነበራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰው እግዚአብሔር በመንግሥቱ በክብር ይቀበላቸው በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። 

ከዮሐ. 10:22-30 ተወስዶ በተነበበው የዕለቱ ንባብ ላይ በማተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዚህ የወንጌል ክፍል አይሁዳውያን ኢየሱስን “እስከ መቼ በጥርጣሬ ታቆየናልህ? አንተ መሲህ እንደሆንክ በግልጽ ንገረን” ብለው መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ ኢየሱስም “እኔ፥ ነግሬአችኋለሁ፤ እናንተ ግን አታምኑም፤ በአባቴ ስም የምሠራው ሥራ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተ ግን ከበጎቼ መንጋ ስላልሆናችሁ አታምኑም” ማለቱን አስታውሰው፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ መንጋዎች መካከል እንዳንሆን የሚያደርጉን፣ ወደ ቤቱ እንዳንገባ ከበር የሚያስቀሩ እንቅፋቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ እንቅፋቶች መካከል የመጀመሪያው ለሃብት መገዛት ወይም የገንዘብ ባሪያዎች መሆን ነው ብለው ይህ እንቅፋት የኢየሱስ ክርስቶስ መንጋ የሆኑትንም እንደሚያደናቅፍ፣ እግዚአብሔርን ለማወቅ በምናደርገው ጉዞ ላይ እንቅፋት እንደሚሆንብን አስረድተዋል። “በድህነት ሕይወት መሰቃየት የለብንም፤ በሌላ ወገንም የሃብት ተገዢዎች፣ ለገንዘብ የምንኖር መሆንም የለብንም” ብለው፣ “ለገንዘብ የምንኖር ከሆነ በገንዘብ እንመራለን፤ ገንዘብን የዚህ ዓለም ገዥ ካደረግን እግዚአብሔርን ማገልገል አንችልም፤ ለሁለት ጌቶች ልንገዛ አንችልም” ብለዋል።

በመንፈሳዊ ሕይወታችን ወደ ፊት እንዳንጓዝ፣ ኢየሱስን እንዳናውቅ እና ከመንጋው እንዳንሆን የሚያደረገን ሁለተኛው እንቅፋት የልብ ግትርነት መሆኑን አስረድተዋል። የልብ ግትርነትን በማስመልከት እንደገለጹት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈሪሳውያን እና ለሕግ አዋቂዎች ብዙ ጊዜ ይናገራቸው ነበር ብለው፣ ግትርነት ማለት ታማኝነት ማለት አለመሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ታማኝነት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን አስረድተው ግትርነት ግን የግል ደህንነትን ብቻ ለመጠበቅ የሚደረግ ተግባር ነው ብለዋል። በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ በምዕመናን መካከል የግትርነትን ባሕሪይ የሚያሳዩ ወገኖች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ግትርነት የሰው ልጅ ነጻነት የሚገፍ መሆኑን አስረድተዋል። ግትርነት የኢየሱስ ክርስቶስን ጥበብ ለመማር ያለንን ነጻነት እደሚወስድብን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ብዙ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ምዕመናንን በግትርነት እንዲያድጉ በማድረግ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ቤት ለመግባት ያላቸውን ነጻነት እንዲያጡ ያደርጋሉ ብለዋል።

በሕይወታችን ውስጥ ኢየሱስን እንዳናውቅ፣ ከእርሱ መንጋ መካከል እንዳንሆን የሚያደረገን ሦስተኛው እንቅፋት የቤተክህነት ገናናነት መሆኑን የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህም የቤተክህነት ወገን የሆኑት ራሳቸውን በኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ላይ በማስቀመጥ ፈላጭ ቆራጭ እንደሚሆኑ አስረድተው ይህም የምዕመናንን ነጻነት የሚወስድ መሆኑን ገልጸዋል። የቤተክህነት ገናናነት በቤተክርስቲያን ውስጥ መልካም ሥፍራ እንደሌለው፣ ለብዙዎችም እንቅፋት እንደሚሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

ኢየሱስን እንዳናውቅ የሚያደርግ ሌላው እንቅፋት፣ በምዕመና ሕይወት ውስጥ የሚታይ የዓለማዊነት መንፈስ መሆኑን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ይህ መንፈስ የሚታወቀው ክርስቲያናዊ ተግባራትን ማከናወን ስናቆም እና ሁለመናችን ለዓለማዊ መንፈስ ስናስገዛ መሆኑን አስረድተዋል። ምዕመናን ለአንዳንድ የቤተክርስቲያን ምስጢራት የሚሰጡትን ትርጉም እና ክብር በምናይበት ጊዜ በቅዱሳት ምስጢራት ውስጥ የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት፣ ጸጋውንም በደንብ ያልተረዱ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በእነዚህ ተግባራ መካከል ነጻነት የሚጎድል መሆኑን ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነጻነት ከሌለ ኢየሱስን መከተል አይቻልም ብለው፣ ከገደብ ካለፈ ደግሞ ተንሸራትቶ መውደቅን እንደሚያስከትን ገልጸው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የምናደርገውን ጉዞ ከመጀመራችን በፊት ተንሸራትተን የምንወድቅ ከሆነ ጉዳቱ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው አስረድተዋል።

ይህን ዜና በድምጽ ማድመጥ ከፈለጉ የተጫወት ምልክትን ይጫኑ፣
05 May 2020, 17:26
ሁሉንም ያንብቡ >