ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት መስዋዕተ ቅዳሴ ባሳረጉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ አውሮፓዊያን ያላቸውን ሕብረት እና አንድነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጸሎት አደረጉ

የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ምዕመናን ዘንድ በሚያዝያ 21/2012 ዓ.ም የአውሮፓ አህጉር ጠባቂ እንደ ሆነች የምትታመነው የቅድስት ካትሪን ዘሲዬና አመታዊ በዓል ተከብሮ ማለፉ ተገልጿል። በወቅቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው የቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በእዚህ አሁን ባለንበት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰፊው በሚታይበት ወቅት የአውሮፓ አህጉር ከእዚህ ቀደም የነበረውን አንድነት እና ህብረት አጠናክረው ወደ ፊት ይጓዙ ዘንድ ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል። ቅዱስነታቸው በወቅቱ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት እግዚአብሔር በትህትና እና በየዋህነት መንፈስ ተጨባጭ በሆነ መልኩ ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ እና በዚህም መልኩ የእርሱን ይቅርታ ለማግኘት እንችል ዘንድ ጌታ ጸጋውን ይሰጠን ዘንድ ልንማጸነው እንደ ሚገባ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በዕለቱ ያደረጉት ስብከት “በብርሃን መመላለስ” በሚል ጭብጥ ዙሪያ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ ከጻፈው በሚከተለው መልዕክት ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር . . .

“ከእርሱ የሰማነው ለእናንተም የምንነግራችሁ መልእክት፣ እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም፤ የሚል ነው። በጨለማ እየተመላለስን ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል እንዋሻለን፤ እውነትንም አንኖረውም። ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል። ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። ኀጢአት አልሠራንም ብንል፣ እርሱን ሐሰተኛ እናደርገዋለን፤ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም። ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም” (1ዮሐንስ 1፡ 5-2፡2) ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ባደረገው ስብከታቸው ሐዋርያው ዮሐንስ እግዚአብሔር አምላክ ብርሃን መሆኑን እና እኛም ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን የምንል ከሆነ፣ እኛም እርስ በእርሳችን ሕብረት መፍጠር እንደ ሚገባን በመግለጹ የተነሳ እኛም ክርስትያኖች በእዚሁ መልክ ልንጓዝ ይገባል ብለዋል። እርስ በእርሳችን ኅብረት የምንፈጥር ከሆነ ኅብረታችንን የመኝ የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ኃጢአታችንን ሁሉ ይቅር እንደ ሚልልን ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን ሲቀጥሉ “ኀጢአት የለብንም ብንል፣ ራሳችንን እናስታለን፤ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም” በማለት በአጽኖት በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ነገር  ግን ኃጢአተኛ መሆኑን አምኖ ኃጢአቱን የሚናዘዝ ሰው ከእግዚአብሔር ይቅርታን እንደ ሚያገኝ እና ከኃጢአቱ ሁሉ እንደ ሚነጻ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ሐዋርያው ዮሐንስ ተጨባጭ እና እውነተኛ የሆኑ ነገሮች ላይ እንድናተኩር እንደ ሚጋብዘን በማስታወስ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው በጨለማ እና በብርሃን ውስጥ በተመሳሳይ ወቅት ወይም ሰዓት መመላለስ እንደማንችል ተናግሯል። በተቃራኒው ደግሞ አንድ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እውቅና የሚሰጥ ከሆነ፣  እውነት ተጨባጭ በመሆኗ እና ውሸት ደግሞ ምድራዊ የሆኑ ነገር በመሆኑ የተነሳ በእዚህ ምክንያት ኃጢአትን በግልፅ መናዘዝ ብቻ በቂ እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን ነገር ግን ተጨባጭ በሆነ መንገድ በኃጢአታችን መጸጸታችንን መመስከር ያስፈልጋል ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብከታቸውን ሲቀጥሉ በዕለቱ ከማቴዎስ ወንጌል ላይ ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ውስጥ በተጠቀሰው “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድህ ሆኖ ተገኝቶአልና” (ማቴዎስ 11፡ 25-30) በሚለው የኢየሱስ ቃል ላይ መሰረቱን ያደርገ ነበር።  “ሕጻናት ልጆች” አሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አፅንኦት በመስጠት “ኃጢአታቸውን በቅንነት በመናዘዝ፣ ተጨባጭ የሆኑ ነገሮችን ይናገራሉ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሰጣቸው የቅንነት መንፈስ በውስጣቸው ስላለ ነው” ብለዋል። እኛም እንዲሁ ልክ እንደ ሕጻናት ቅን እና ተጨባጭ መሆን አለብን፣ ተጨባጭ በሆነ መልኩ በኃጢያታችን በማፈር ኃጢያታችንን መናዘዝ እንደ ሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው ተጨባጭ መሆናችን ደግሞ ወደ ትሕትና እንድናመራ ያደርገናል ብለዋል። ጌታ ይቅር ባይ ስለሆነ ኃጢአቶቻችንን ተጨባጭ በሆነ መልኩ ልንሰይማቸው ይገባል፣ ኃጢአቶቻችንን ለመደበቅ ብልጣብልጥ በሆነ እና ረቂቅ በሚመስል መልኩ ኃጢአቶቻችንን የምንናዘዝ ከሆንን አሁንም በጨለማ ውስጥ እንገኛለን ብለዋል።

“ኃጢአቶቻንን በምንናዘዝበት ወቅት እጅግ አስፈላጊው ነገር አሉ” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ነጻ ሁነን ኃጢአቶቻችንን ምንም ሳንደብቅ በግልጽ ለጌታ መናገር ይኖርብናል፣ ተጨባጭ በሆነ መልኩ ኃጢአትን የመናዘዝ ጥበብ ያስፈልገናል፣ ምክንያቱም ዲያቢሎስ ነጭም ሆነ ጥቁር ያልሆነ፣ ነገር ግን ግራጫ የሆነ ኑሮ እንድንኖር ስለሚፈልግ ኃጢአቶቻችንን እንድንደብቅ ይገፋፋናልና ነው” ብለዋል።  “ጌታ ሙቅ ወይም ቀዝቃዛ ያልሆኑ፣ መኸል ሰፋሪ የሆኑ ለብ ያሉ ሰዎችን አይወድም” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ መንፈሳዊ ሕይወት ቀለል ባለ መልኩ በቅንነት የሚኖር ሕይወት ነው፣ ነገር ግን መንፈሳዊ ሕይወት ውስብስብ እንዲሆን የምናደርገው እኛው ራሳችን ነን ብለዋል።  ቅን፣ ግልፅ፣ ነገሮችን በነፃነት የመናገር እና ኃጢአቶቻችንን እንዳለ በግልጽ በደንብ በእግዚአብሔር ፊት ማመን እንችል ዘንድ፣ ድክመቶቻችንን አምነን መቀበል እንችል ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን ጌታን ልንጠይቀው የገባል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለዕለቱ ያዘጋጁትን ስብከት አጠናቀዋል።

29 April 2020, 19:56
ሁሉንም ያንብቡ >