ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጸሎት አደረጉ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዛሬ በሚያዝያ 19/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ውስጥ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ያቀረቡት የጸሎት ሐሳብ ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ያላቸውን የጥበብ እና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ሕዝቡን በማዝናናት ላይ ለሚገኙ በኪነ- ጥበብ መስክ ለተሰማሩ ሰዎች ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያሳረጉትን መስዋዕተ ቅዳሴ የጀመሩት ቀደም ሲል እንደ ገለጽነው በኪነ ጥበብ መስክ ለተሰማሩ ሰዎች ጸሎት በማደረግ ሲሆን “ዛሬ በፈጠራ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ተዋኒያን እና የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች እንጸልይላቸው” በማለት እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን የተለያዩ የፈጠራ ተግባራትን በመጠቀም ለእኛ የውበት መንገድ ስለሚያሳዩን እንጸልይላቸው፣ በእዚህ አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ጌታ የፈጠራ ችሎታ እንዲሰጠን ጸጋውን እንጠይቅ” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዕለቱ ያደርጉት ስብከት “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም። ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በእርሱ ላይ አትሞአልና” (ዮሐ 6፡22-29) በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ነበረ ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በስብከታቸው ወቅት እንደ ተናገሩት ሕዝቡ ኢየሱስን “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” ብለው ጠይቀውት እንደ ነበረ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው የኢሱስም “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል እንደ መለሰላቸው አክለው ገልጸዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ህዝቡ ኢየሱስን “ሳይታክቱ ያዳምጡት እንደ ነበረ” የገለጹ ሲሆን ከእዚያን በኋላ ለቃሉ የነበራቸውን በመጀመሪያውን ቅንዓት ዘንግተው ንጉሳቸው ሊያደርጉት አሰቡ ብለዋል።
ከኢየሱስ ጋር የተደረገውን የመጀመሪያ ግንኙነት ማስታወስ
ስለእዚህ ሕዝቡ ጌታን የተገናኙበት የመጀመሪያውን እለት እንዲያስታውሱ ኢየሱስ እንደ ጋበዛቸው በስብከታቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው እናም ሕዝቡ “ወንጌላዊ ከሆነ መንገድ ይልቅ የመረጡትን ዓለማዊ መንገድ እንዲያስተካክሉ ኢየሱስ እንዳደረገ” ጨምረው ገልጸዋል።
ከቅዱስ ወንጌል መንገድ በምንርቅበት ጊዜ እና ከጌታ ቃል ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኘንበት ወቅት የነበረንን ቅንዓት በምንዘነጋበት ወቅት ተመሳሳይ የሆነ ነገር በእኛም ላይ እንደ ሚከሰት የገለጹት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ግን ወደ መጀመሪያው ከእርሱ ጋር ወደ ተገናኘንበት ሁኔታ እንድንመለስ ይጠይቀናል ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ይህ ፈተና መልካም የሆነ የጸጋ አጋጣሚዎችን ይከፍትልናል ብለዋል።
እናም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ኢየሱስ በፍቅር ተመልክቶን ወደ ጠራን ወደ እዚያ የመጀመሪያው ቀን” መመለስ እንደ ሚገባ የገለጹ ሲሆን ይህ ተግባራችን ደግሞ ጸጋን እንደ ሚያጎናጽፈን “እያንዳንዳችንን ኢየሱስ“ ተከተለኝ” ብሎ የጠራንን ከእርሱ ጋር የተገናኘንበትን የመጀመሪያውን እለት ማስታወስ ይገባል ብለዋል።
ወደ ገሊላ መመለስ
ከኢየሱስ ጋር በተገናኘንበት ወቅት ወደ ነበረን የመጀመሪያው ተሞክሮ እንመለስ ዘንድ ጌታ ጸጋውን እንዲሰጠን ልንማጸነው እንደ ሚገባ የገለጹት ቅዱስነታቸው ጎህ ሲቀድ ኢየሱስ ወደ ተቀበረበት መካነ መቃብሩ ሥፋራ የሄዱት ሴቶች ሁኔታውን ከተመለከቱ በኋላ ሄደው ለደቀ-መዛሙርቱ “አትፍሩ፤ ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ በዚያ ያዩኛል” (ማቴዎስ 28፡10 ይመልከቱ) ብሎ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ደቀ-መዛምሙርቱ ከኢየሱስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት ሥፍራ ገሊላ በመሆኑ የተነሳ ነው ብሏል ፡፡
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ ገሊላ በውስጣችን አለን” በማለት የተናገሩ ሲሆን ኢየሱስ ወደ እኛ ቀርቦ በፍቅር ተመልክቶን እና ተከተለኝ ብሎ ጥሪ ያቀረበልንን እለት ማስታወስ ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው የእለቱን ስብከት አጠናቀዋል።