ፈልግ

ቅዱስነታቸው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ፥ ቅዱስነታቸው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ፥ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የኮሮና ቫይረስ ያስከተለውን ችግር ለማስወገድ የሚደክሙትን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ዛሬ መጋቢት 25/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ችግር ከማኅበረሰቡ ለማስወገድ በተለያያዩ ሃላፊነት ተሰማርተው የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን በሙሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ዛሬ ባሰሙት ስብከታቸውም ሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በማስታወስ እናታችን በመሆኗ ልናመሰግናት ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓርብ ዕለት እንዲሆን በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሃሳባቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሁንም ሆነ ወደፊት የሚያስከትላቸውን ማኅበራዊ ችግሮች፣ ከእነዚህም መካከል ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና ረሃብን ለማሸነፍ መፍትሄን በማፈላለግ ጥረት የሚያደርጉትን ሁሉ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለው ማኅበራዊ ችግር እንድንወጣ ዛሬ የተቻላቸውን እገዛ የሚያደርጉትን እና መጭውን አስቸጋሪ ወቅትን በማሰብ መልካም የመፍትህሄ ሃስቦችን የሚያቀርቡ ግለ ሰቦችን በጸሎታችን እንድናስታውሳቸው አደራ ብለውናል። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሐዘን በሚያስታውሰን እና የኢየሱስ ክርስቶስ የስቃይ ዕለት በሚታወስበት ዕለተ ዓርብ ሐዘንተኛይቱ እመቤታችን ማርያምን ማስታወስ መልካም እንደሆነ ገልጸው ቅድስት ድንግል ማርያም እናታችን ለመሆን ፈቃደኛ ሆና ስለ ተገኘች ልናመሰግናት ይገባል ብለዋል።              

ሰባቱ የእመቤታችን ማርያም የሐዘን ጊዜያት፣

ምዕመናን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን አክብሮት በሚገልጹበት ጊዜ ሰባት የሐዘን ገጠመኞቿንም ያስታውሳሉ ያሉት ርዕሠ ሊቃን ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የመጀመሪያ ሐዘኗ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በአርባ ቀኑ እናቱ ማርያም በኢየሩስሌም ወደ ቤተ መቅደስ ባቀረበችው ጊዜ ስምዖን “ያንቺን ልብ የሐዘን ሰይፍ ሰንጥቆ ያልፋል” ማለቱ፣ ሁለተኛው ሐዘኗ ልጇን ይዛ ወደ ግብጽ በመሸሽ ከሞት ለማትረፍ ማሰቧ፣ ሦስተኛ ሐዘኗ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልጅነቱ ከእናቱ ተለይቶ በቤተመቅደስ በቀረ ጊዜ ለሦስት ቀናት በሙሉ የተሰማት ሐዘን፣ አራተኛው እና አምስተኛው ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ተፈርዶበት ወደሚሰቀልበት ቦታ ሲሄድ እና በመስቀል ላይ መሞቱን ስትመለከት የተሰማት ሐዘን፣ ስድስተኛው እና ሰባተኛው ኢየሱስን ከመስቀል አውርደው ሲሰጧት የተሰማት ሐዘን እና በተቀበረ ጊዜ የተሰማት ሐዘን መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። በየማታው በሚያቀርቡት የእግዚአብሔር መልአክ ጸሎታቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተክርስቲያን እናት መሆኗን የሚያስታውሱ መሆኑን ገልጸው ቅድስት ድንግል ማርያም በብዙ ስቃዮችዋ የቤተክርስቲያን ልጆች እንድንሆን አድርጋናለች ብለዋል።              

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለራሷ የሚሆን ምንም ነገር አልጠየቀችም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እርሷ የወደደችው ለእኛ እናት መሆንን ብቻ ነው ብለዋል። ቅዱስ ወንጌል እንደሚነግረን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሌሎች ሴቶች፣ የቅርብ ጓደኞቿ እና ደቀ መዛሙርት ጋር በመሆን ኢየሱስን ትከተለው እና ታደምጠው ነበር ብለዋል። ቅድስት ድንግል ማርያምን እናታችን በማለት እንድናከብራት ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው የእናትነት ክብርን እና ማዕረግን ያገኘችው ከልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልጇን ማዕረግ መቀበል አልፈለገችም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ከልጇ የተቀበለችው እናት የመሆን ስጦታን እና የእኛ እናት ሆና መገኘትን ብቻ ነው ብለው የማዳን ስልጣን ሆነ አጋርነትን አልጠየቀችም ብለዋል። አዳኛችን አንዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ብለው ይህ መለኮታዊ ኃይል ለሌላ ተላልፎ የሚሰጥ ማዕረግ አይደለም ብለዋል።      

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያሳረጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ከመፈጸማቸው በፊት ባቀረቡት የቅዱስ ቁርባ ቡራኬ ጸሎትን፥

ኢየሱስ ሆይ! በቅዱስ ቁርባን ውስጥ በእውነት እንደምትገኝ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ አብልጬ እወድሃለሁ፣ በነፍሴ ውስጥ እንድትገኝ እመኛለሁ። አሁን በምገኝበት ሁኔታ ቅዱስ ስጋህን እና ቅዱስ ደምህን መቀበል ባልችልም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በልቤ ውስጥ ግባ። ካንተ ጋር መሆንን እፈልጋለሁና ዘወትር ካንተ እንዳልለይ አድርገኝ፤ አሜን።      

ቅዱስነታቸው ቀጥለውም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ባቀረቡት ጸሎታቸው፥ ‘የሰማያት ንግሥት፣ የመላዕክት እመቤት እና የምሕረት ምንጭ የሆንሽ እናታችን ሆይ ብርሃንሽ በዓለም ሁሉ ይብራ፤ ከሴቶች ሁሉ በላይ የምትወደጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ለምኚልን’ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ይህን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ፣
03 April 2020, 16:11
ሁሉንም ያንብቡ >