ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣                ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ፍትሃዊ ባልሆነ ፍርድ ስቃይ የሚደርስባቸውን በጸሎታቸው አስታወሱ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ መጋቢት 29/2012 ዓ. ም. በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ፍትሃዊ ባልሆነ ፍርድ ለስቃይ የሚዳረጉትን በርካታ ሰዎች በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እግዚአብሔር የሚጠራን ሌሎችን ለማገልገል መሆኑንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን                  

ቅዱስነታቸው ዛሬ በተነበቡት ቅዱሳት መጽሐፍት ላይ በማስተንተን ባቀረቡት ስብከት በዓለማችን ውስጥ የሐሰት ክስ የሚመሠረትባቸው፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ የሚሰጣቸው ፣ ቀጥሎም ለእስራት፣ ለመከራ እና ስቃይ የሚዳረጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው እነዚህን ሰዎች በጸሎታቸው የሚያስታውሷቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ እንደገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ዓይነት ጥፋት ሳይገኝበት በሕግ አዋቂዎች በኩል በተሰጠው ፍትሃዊ ያልሆነ ፍርድ ለስቃይ መብቃቱን አስረድተዋል።   

እኛ ሁላችን የተጠራንበት ዓለማ አለን፣

ትንቢተ ኢሳ. 49: 1-6 ላይ እንደተጻፈው እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው የገለጹት ቅዱስነታቸው በዚህ ጥቅስ እግዚአብሔር ነብዩ ኢሳይያስን ገና በእናቱ ማሕጸን ውስጥ እያለ እንደመረጠው አስታውሰዋል። በተመሳሳይ መንገድም እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን ገና ሳንወለድ እንደመረጠን እና ይህ ጥሪም ሌሎችን ለማገልገል መሆኑን አስረድተዋል። ገና ስንወለድ ዓላማ እና ግብ አለን ያሉት ቅዱስነታቸው  ወደዚህ ዓለም የመጣነው በእግዚአብሔር ጥሪ መሠረት ነው ብለዋል። “ከመወለዴ አስቀድሞ እግዚአብሔር መርጦኛል፤ የተመረጥኩትም እርሱን ለማገልገል ነው” ብለዋል።         

የአገልግሎት ጥሪ፣

“ሌሎችን ስናገለግል ለትርፍ ወይም ለጥቅም መሆን የለበትም” ያሉት ቅዱስነታቸው የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ሆኖልናል ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር የተገለጸው እስከ ሞት ድረስ በማገልገሉ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ አድርጎ ማገልገሉ ሽንፈት ቢመስልም የአገልግሎቱ መገለጫ ነው ብለዋል። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ራሳቸውን ከአገልግሎት መንገድ በሚያርቁበት ጊዜ ወደ ክህደት ያመራሉ ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህም ከእግዚአብሔር ይልቅ ሌላ ነገርን እንዲያፈቅሩ፣ ጣኦትን እንዲያመልኩ እና ከእግዚአብሔር የቀረበላቸውን ጥሪ እንዲያጡ ያደርጋቸዋል ብለዋል።     

ንስሐ የመግባት ዝንባሌ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው እንደገለጹት አስፈላጊው እና መጓደል የሌለበት ነገር ቢኖር እኛን ለጠራን እና አገልጋዮቹ አድርጎ ለቀባን እግዚአብሔር የምናሳየው ቅን ፍላጎት ነው ብለዋል። ከእመቤታችን እና ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር እኛ ሁላችንም ውድቀት አጋጥሞናል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያው ጴጥሮስን እንደ ምሳሌ ጠቅሰው፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ኢየሱስን እንደካደው አስታውሰው ጴጥሮስም በዚህ ሥራው መራራ ልቅሶ ማልቀሱን አስታውሰዋል።(ማቴ. 26፡75) ይህም አንድ አገልጋይ በጥሪው መካከል ውድቀት ሲያጋጥመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን ለማግኘት የሚያደርገው ጸጸት መሆኑን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። የእግዚአብሔር አገልጋይ ውድቀት ሲያጋጥመው ልቡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ወደ ጣኦት አምልኮ ይመለሳል ብለው፣ ይሁዳን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ ይሁዳ ልቡን ክፍት አድርጎ የሰጠው ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለሰይጣን ነው ብለዋል።  

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት ስብከት በአገልግሎቱ ታማኝ ሆኖ የተገኘውን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስታወስ አለብን ብለው፣ እግዚአብሔር እኛን የጠራን ሌሎችን ለማገልገል እንጂ ከቤተክርስቲያን በተሰጠን ሥልጣን ጥቅምን ለማግኘት አለመሆኑን አስረድተው በአገልግሎታችን መካከል ውድቀት ሲያጋጥመን እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ አልቅሰን ንስሐ በመግባት ምሕረትን የምንለምንበትን ብርታት እግዚአብሔር ይስጠን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

07 April 2020, 18:41
ሁሉንም ያንብቡ >